ይህ ረድፍ የአንድ አካባቢ ወይም ቦታ ለምን እንደተባለ የሚገለጽበት ንዑስ ዓምድ ነው። በአገራችን ውስጥ የሚገኙ ቦታዎችን እናስተዋውቃለን። እነዚህ ቦታዎች ለምን እንደተባሉ ከታሪክ ሰነድ አጣቅሰን ምላሽ እንሰጣለን። ለምን ተባለ ከአዲስ አበባ በምዕራብ በር እንውጣ፡፡ 28 ኪሎ ሜትር እንደተጓዝን ሆሎታን እናገኛለን፡፡ ሆሎታ በተለይም በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በተከፈተው ? የጦር ማሰልጠኛ (ሚሊተሪ አካዳሚ) ትታወቃለች፡፡ በዚህ ብቻ አይደለም፤ አሁንም በዚያው በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የእርሻ ምርምር ማዕከል በሆሎታ ተከፍቷል፡፡ ሆሎታ አሁንም በግብርና ምርምር ትታወቃለች፡፡
ሆሎታ ለምን ተባለ? ስሟ እውነትም የግብርና ምርምር ቦታ መሆኗን ይነግረናል፡፡ ‹‹ሆሎታ›› ማለት በኦሮምኛ ‹‹እርጥብ፣ ለምለም ሳር›› ማለት ነው፡፡ ቢሾፍቱ አሁን ደግሞ ከአዲስ አበባ በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ እንውጣ፡፡ 48 ኪሎ ሜትር ከተጓዝን ቢሾፍቱን እንናገኛለን፡፡
ቢሾፍቱ የቱሪስት መዳራሻ እና የእንግዳ ማረፊያ ከተማ ናት፡፡ ስብሰባዎች ይደረጉባታል፤ ሀብታሞች ልጆቻቸውን ማዝናናት ሲፈልጉ ቢሾፍቱን ይመርጧታል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም ውብና ማራኪ በመሆኗ ነው፡፡ ቢሾፍቱ ለምን ተባለ? ‹‹ስምን መላክ ያወጣዋል›› ልንል ነው፡፡ ቢሾፍቱ ማለት ‹‹ቢሻን›› የሚለው የኦሮምኛ ቃል ርቢ ነው፡፡ ውሃማ፣ ረግረግ፣ ለምለም ማለት ነው፡፡ ከተማዋም እንደ ስሟ በበርካታ ሐይቆች የታደለች ናት፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19/2011