‹‹ስደት ለወሬ ያመቻል›› የሚለው አባባል ወደ ውጭ አገር የመሄድ ምኞቴን እየጨመረብኝ ነው:: ምንም እንኳን ብዙ ሰው ወደ ውጭ አገር የመሄድ ምኞት ቢኖረውም የእኔ ግን ይለያል:: ‹‹ስደት ለወሬ ያመቻል›› እንደሚባለው ለወሬ እንዳመቸኝ ብዬ ነው:: ማለቴ የአገሬን ሁኔታ ሳወራ ‹‹አውሮፓ አገር እንዲህ ነው፣ ኤስያ እንዲህ ነው፣ አሜሪካ ቢሆን ኖሮ…›› እያልኩ ለማጣቀስ ብዬ ነው:: በእርግጥ ከሚሰሙትና ከመገናኛ ብዙኃን አውታር ከሚያገኙት በመነሳት ብቻ ኢትዮጵያን ከሌሎች አገሮች ጋር የሚያነጻጽሩ አሉ:: ቆይ ግን ሳያነጻጽሩ አይወራም እንዴ? ኢትዮጵያ ውስጥ የመብት ነገር ግርም ይለኛል:: አንድ አስቂኝ ገጠመኝ ልንገራችሁ::
ከመገናኛ ወደ ኮተቤ በታክሲ እየሄድን ነው:: ላምበረት አካባቢ ሲንደርስ ልክ አደባባይ መዞሪያ ላይ አንዲት ወጣት ‹‹ወራጅ አለ›› አለች:: ለወትሮው ‹‹እዚህ አይቻልም›› ይሉ ነበር ረዳቶች:: ይሄኛው ሰልችቶት ይሁን አጠያየቋ በጣም ስላበሳጨው ይሁን አላውቅም ሰምቶ ዝም አላት:: መንገዱ የተዘጋጋ ስለሆነ በፍጥነት አይሄድምና አሁንም በአደባባዩ ዙሪያ ነው:: ድምጿን ከፍ አድርጋ በቁጣ ‹‹ወራጅ አለ እያልኩህ እኮነው!›› አለችው:: ደግነቱ ከረዳቱ ቁጣ በፊት ታክሲው ውስጥ ያለው ሰው መሳቅ ጀመረ:: ረዳቱ የተሳፋሪውን ሳቅ ለህጋዊነቱ መተማመኛ አድርጎ ይመስላል በምፀት ዞር ብሎ አይቷት ‹‹አይ ቆይ አደባባዩ ውስጥ ላስገባሽ ብዬ ነው!›› አላት::
ከረዳቱ የምጸት ንግግር ይልቅ የተሳፋሪው ሳቅ አንጀቷን አቃጥሎታል:: ካፈርኩ አይመልሰኝ እንዲሉ የምንተፍረቷን ‹‹መብቴ ነው›› አለች፤ ይሄኔ የባሰ ተሳቀባት:: እግረ መንገዱን ብዙ ነገር ስላስታወሰኝ እንጂ የልጅቷ ገጠመኝ ተራ ገጠመኝ ነው:: ዳሩ ግን የብዙ ሰዎችን ስህተት ይነግረናል:: በተለይ ይሄ ‹‹መብቴ ነው›› የሚባል ቃል የሚገባባቸውን ቦታዎች ስናይ የመብት ነገር ምን እንደሆነ ይጠፋብናል:: እዚህ አገር መብቴ ነው የምንለው ነገር ሌላውን መጉዳት ነው:: ለምሳሌ ልጅቷ መብቴ ነው ያለችው ህግ ጥሳ ነው:: መሆን የሌለበት ቦታ ላይ ካልሆነ ብላ ነው:: እኔ ግን ሳስበው መብት ብርቅ ሆኖብን ይመስለኛል:: ከአስተዳደጋችን ጀምሮ ስንኖርም መብቶቻችን የሚረገጡባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው::
ለዚያም ነው ቃሉ ራሱ ብርቅ ሆኖ በጣም ሲደጋገም የምንሰማው:: በአስተዳደጋችን ውስጥ የቤተሰብ ጫና አለ:: ይሄ ነገር ገጠር ብቻ እንዳይመስላችሁ፤ የአዲስ አበባ ልጆች ብዙ የቤተሰብ ቁጥጥር አለባቸው:: መረን ለቀው ይደጉ እያልኩ አይደለም፤ ዳሩ ግን የቁጥጥሩ ይይነት ይለያያል:: ከቤተሰብ ከወጣን በኋላም ይሄው ነው:: ፖለቲካችን ሁልጊዜም የሚዘመርለት የመብትና ግዴታ እያየ ነው:: ከትምህርት ቤት ጀምሮ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ:: የሳይንስ ምልክቶች፣ የሒሳብ ቀመሮች፣ የአገራት ካርታ… የመሳሰሉት ትምህርታዊ ነገሮች ከውጭ በኩል የሚለጠፉ ሲሆን ከክፍል ውስጥ የሚለጠፈው ‹‹የተማሪው መብትና ግዴታ›› የሚል ነው::
በተለይም ‹‹የተማሪው ግዴታ›› በሚለው ሥር ያለው መዘርዝር ይበዛና ‹‹መብት›› ላይ ያለው አነስ ያለ ይሆናል:: ስለዚህ ለምን መብት ብርቅ አይሆንብን? ‹‹ለምን ሆነ›› አልልም፤ ስነ ምግባራችንም እንደዚሁ ነው:: በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያሉ ነገሮችን ከመጠቀም ይልቅ ማበላሸት ላይ ስለምናተኩር ግዴታዎች በዙ:: ይሄ ነገር አብሮን ያድግና ከትምህርት ቤት ያልፋል:: ከቀበሌ ጀምሮየአገሪቱ የሥልጣን ቁንጮ እስካለበት ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ድረስ ‹‹ክልክል ነው›› የሚል ጽሑፍ ነው የምናየው::
ከግል ንግድ ቤቶች ጀምሮ እስከ መንግሥት ተቋማት ድረስ የሚከለከሉ ነገሮች ይበዛሉ:: ይሄ ማለት እንግዲህ ካልተከለከልን እናጠፋለን ማለት ነው:: ‹‹ክልክል ነው›› የሚል ጽሑፍ ማየት በጣም የተሰለቸ ነው:: ታዲያ ለዚህ ይሆን መብት ብርቅ የሆነብን? የተማሩ ናቸው የሚባሉ፤ አገር ለመምራት የሚወዳደሩ፤ ትልልቅ የምንላቸውን ሰዎች ልብ በሉ:: ስብሰባዎችንና ውይይቶችን አስተውሉ:: የሚወራው ስለመብትና ግዴታ ነው:: ይሄ ‹‹መብቴ ነው›› የሚባል ነገር ይሉኝታም እያሳጣን ነው:: ኧረ ሰው አይሰደብም፤ ‹‹በገዛ ስልኬ መብቴ ነው›› ይሄ እኮ ለሰው ፀያፍ ነው መንገድ ላይ አይጣልም፤ ‹‹መብቴ ነው››፣ ይሄ እኮ ሌላ ሰው ይወጋል መንገድ ላይ አይደረግም፤ ‹‹መብቴ ነው››… ታዲያ መብት ብርቅ አልሆነብንም? አንዳንዱ መብቴ ነው ደግሞ ያስቃል::
ራሱ ላይ ጉዳት የሚያደርስን ነገር ሲከለከል(ሲመከር) ‹‹መብቴ ነው›› ይላል:: መድሃኒት እየወሰዱ እኮ አልኮል አይጠጣም ሲባል፤ ‹‹መብቴ ነው››፣ ይሄ መጠጥ እንዲህ ስለሆነ ቢቀርብህ፤ ‹‹መብቴ ነው››፣ ይሄ ነገር መጥፎ ሱስ ነው፤ ለጤናም እንዲህ ዓይነት ጉዳት አለው ቢቀርብህ ‹‹መብቴ ነው›› ይሄ ልብስ እኮ የደም ዝውውርህን እንዲህ ያደርገዋል፤ ‹‹መብቴ ነው››፣ ብርድ ስለሆነ እንዲህ ባትለብሽ ‹‹መብቴ ነው››፤ ትልልቅ ሰዎች ጋ ስለሆነ የምትሄጂው እንዲህ ባትራቆች ‹‹መብቴ ነው››፣ ይሄ እንዲህ ነውና ባትቀቢው ‹‹መብቴ ነው››… እንዲህ ሆነናል እንግዲህ! ነገሮችን ሁሉ ለምን ከመብትና ግዴታ አንጻር ብቻ እንለካቸዋለን?
ራቁትህን አትሂድ የተባለ ሰው መተው ያለበት ግብረገባዊነትን ወይም ሳይንሳዊ ጉዳቱን አመዛዝኖ ነው ወይስ ስላልተከለከለ ብቻ ነው? አንዳንዶቹ እኮ ገና ማንም ሳይናገራቸው ‹‹እስኪ ዛሬ ምን ምናባቱ እንደሚለኝ አያለሁ!›› ብለው ይፎክራሉ:: ከእነዚህ ተራ ገጠመኞች ወጣ ያለ ደግሞ አንድ ላስታወሳችሁ:: ከአንድ ዓመት በላይ ሳይሆነው አይቀርም:: በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የምትሠራ አንዲት ሠራተኛ ከቤተ መጽሐፉ ጥበቃ ጋር ተጣላች:: የተጣላችው ‹‹አግባብ ያልሆነ ልብስ ለብሰሻል›› ተብላ ነው::
ከዚያ ወጥታ ያዙኝ ልቀቁኝ አለች:: ጉዳዩም በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ መከራከሪያ ነበር:: ሁሉም ሃሳብ ሰጪዎች ሲሉ የነበረው ‹‹መብቷ ነው›› ነው:: ልክ ናት አይደለችም አልልም:: ግን ልክ ከሆነችም ከልካዩ የሚጠየቅበት አግባብ ይኖረዋል:: እሷ ልክ ካልሆነች ያልሆነችበትን ማብራራት ሲገባ ‹‹መብቴ ነው›› በሚል ብቻ ተጣሉ:: ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲው ቤተ መጻሕፍት በጣም አጭር የሆነ ቀሚስ መልበስ ክልክል ከሆነ ሴትዮዋ መከራከር የነበረባት ህጉ ትክክል አይደለም፤ መስተካከል አለበት፣ ራቁትም መግባት ይቻላል ካለች ያንን የሚያስችል ህግ መኖር አለበት ብላ መከራከር ነው::
ህጉ እያለ ግን ‹‹መብቴ ነው›› እንዴት ይሆናል? እንዲህ መብት ብርቅ የሆነብንን ያህል ግዴታ ብርቅ ቢሆንብን የት በደረስን ነበር:: ለማንኛውም ‹‹መብቴ ነው›› ስንል ቢያንስ ቢያንስ ግብረ ገብነትንና ሳይንሳዊ ጉዳትን እንኳን ከግምት ውስጥ እናስገባም! ጉዳት የሚያደርስብንን ነገር ስላልተከለከልን ብቻ እናድርገው ካልን ይሄ ሰውነት ሳይሆን እንስሳነት ነው፤ ስላልተከለከልን ብቻ ነውር የሆነን ነገር ማድረግ ይሄ ብልግና ነው!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19/2011
ዋለልኝ አየለ