እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ፣ ምናልባት ይህን ስም ሲጠራ የሰማ ሰው አንዲት ገዳም ገብተው የመነኮሱ፣ ዓለማዊ ሕይወት በቃኝ ብለው የመነኑ ሴት ስለመሆናቸው ብቻ ያስብ ይሆናል። እርግጥ ነው እንዲህ ቢታሰብ ስህተት አይደለም፡፡ ነገር ግን እማሆይ ጽጌ ማርያም ከዚህም፣ ከሚባለውም ሆነ ከተባለው በላይ የረቀቁ የተለዩ መነኩሲት ናቸው። የግላቸው ብቻ የሆነና እሳቸው ብቻ የኖሩት የተለየ የሕይወት ዘይቤን ተከትለው ያለፉ፣ ለብዙ ነገሮች የመጀመሪያዋ ሴት መሆን የቻሉ ድንቅ ኢትዮጵያዊት ናቸው።
አንዲት ዓለም በቃኝ ብለው የመነኑ መነኩሲትን ከሙዚቃ መሳሪያ ፊት ስንመለከት ያልተለመደ ነገር በመሆኑ ግራ ሊገባን አሊያም ግርምትን ሊያጭርብን ይችላል። ነገር ግን እማሆይ ጽጌ ማርያም የኖሩት ሕይወት ነው። ብርቱዋ መነኩሴ ብዙ የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን ሆነውና ኖረው አሳይተዋል። ለመሆኑ እኚህ ሴት ማናቸው? አንዲት መነኩሲትና ሙዚቃስ እንዴት ተዋወቁ? የእኚህን ሴት ዝና ከብዙ በጥቂቱ እናውጋ።
እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ከምንም በላይ የኢትዮጵያ የረቂቅ ሙዚቃዎች እናት ናቸው። 1916 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ከእናታቸው ወይዘሮ ካስዬ የለምቱና ከአባታቸው ከንቲባ ገብሩ ተወለዱ። አባታቸው ገብሩ የጎንደር ከተማ ከንቲባ ነበሩ። እማሆይ በወቅቱ የባለስልጣን ልጅ እንደመሆናቸው በልጅነታቸው እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልጅ ሆነው ቢያድጉም፣ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልጅ የኑሮ ችግርና መከራን ቀምሰዋል ለማለት አያስደፍርም። ምክንያቱ ደግሞ ሁሉ ነገር ሞልቶ ከተትረፈረፈበት ቤተሰብ ውስጥ ነበር ተወልደው ያደጉት። መቼስ የሰው ልጅ ሁሉን አያድለውምና የሚወዷት ሙዚቃ ከወቅቱና ከጊዜው ሁኔታ አንጻር አልጋ በአልጋ ልትሆንላቸው አልቻለችም ነበር። እሳቸው በቻሉት አቅም ሁሉ በእጃቸው ጭምር እየዳሁ የሙዚቃን የቀሚስ ጫፍ ለመያዝ ሲታገሉ በተቃራኒው ሙዚቃ እየሸሸቻቸው ብዙ ውጣ ውረድን አይተውባታል። ቢሆንም ግን ሸሽታ ልትሰወርባቸው አልፈለገችም ነበርና እሳቸው በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው እንኳን ዳግም እየመጣች ትቀሰቅሳቸዋለች። እንደገና ሌላ የተስፋ ብርሃን ታሳያቸውና አሁንም እንዲከተሏት ታደርጋቸዋለች። የሙዚቃ ሕይወታቸው ሙሉ በመውደቅ መነሳት የታጨቀች ነበረች። በዚህ ሁሉ መሃል እማሆይ ምናልባትም የታላቁ የሙዚቃ ጥበበኛ የያሬድን ታሪክ ሳያስታውሱ አይቀሩም። ሙዚቃ በመውደቅ መነሳት፣ እንደገናም መውደቅ ደግሞም የመነሳት ውጣውረዶች ውስጥ በብዙ ትዕግስት የምትገኝ ጣፋጭ ፍሬ ናትና።
የእማሆይ የሙዚቃ ጉዞ የሚጀምረው መነኩሲት ከመሆናቸው ብዙ አመታትን ቀደም ብሎ ገና የስድስት አመት ልጅ ሆነው ነበር። የስድስት አመት ልጅ ሆነው የዘመናዊ ትምህርት ለመከታተል ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ በባቡር አቀኑ። ጅቡቲ ከደረሱ በኋላም የጉዞ መስመራቸውን ከሃዲድ ወደ ባህር በመቀየር በመርከብ ተሳፍረው እያቆራረጡ የሲውዘርላንድ ምድር ላይ አረፉ። እዚያም የአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ በመግባት የዘመናዊ ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ። በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ሳሉ የምዕራቡን ዓለም የክላሲካል ወይንም በሙዚቃ መሳሪያ ብቻ የተቀናበረ ሙዚቃ በተደጋጋሚ ከጆራቸው ይገባ ነበር። እናም እለት እለት በሰሙት ቁጥር የልባቸውን አጥር እየነቀነቀ የሙዚቃው አፍቃሪ ሆነው ቀሩ። ከማፍቀርም አልፈው የሙዚቃ መሳሪያው ባለበት ሁሉ እያሳደዱ በልባቸው ያለውን ፍቅር በጣቶቻቸው መደርደር ጀመሩ። የሙዚቃ ፍቅራቸው እየጨመረ፣ የማወቅ ጉጉታቸውም እየነጎደ ሄደና ሳያስቡት ከሙዚቃ ከተማ ውስጥ ራሳቸውን አገኙት። ከዚህ በመሳሪያ ብቻ የተቀናበረ (ክላሲካል) ሙዚቃ ጋርም ተዋወቁ። ከሀገራቸው የዘመናዊ ትምህርትን ለመከታተል ወደ ሲውዘርላንድ የሄዱት እማሆይ ጽጌ ማርያም የሰብዓዊ ትምህርትን ያጠኑ ሲሆን ከሙዚቃው ጋር በነበራቸው ቆይታ ደግሞ ቫዮሊንን መጫወት ቻሉ። ከመጫወትም አልፈው ገና የዘጠኝ አመት ልጅ ሳሉ አንድ ትርኢት ላይ በመሳተፍ ችሎታቸውን ለማሳየት ችለዋል።
ገና በለጋ የልጅነት እድሜያቸው ከኢትዮጵያ የወጡት እማሆይ የነበራቸውን የሲውዘርላንድ ቆይታ አጠናቀው ውብ ኮረዳ ልጃገረድ ሆነው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ የሙዚቃ ፍቅር ለሚያናውዛቸው ለእኚህ ሴት ብዙ ሁኔታዎች ጥሩ አልነበሩም። በዚያን ጊዜ ሴት ልጅ ሙዚቃ ለመጫወት አይደለም በቅጡ እንደፈለገች ከቤት ወጥታ ለመግባትም ሆነ የዘመናዊ ትምህርት ለመከታተል ይናፍቃት ነበር። የዚያን ጊዜ ሙዚቃ በሴቷ አይደለም በወንዱም እጅ የማያምርና ለማህበረሰቡ ጆሮ የማይጥም ጉዳይ ነበር። እማሆይም ይህንን ተቋቁመው እድል አግኝተው የሙዚቃ ጥማቸውን ለማርካት ትልቅ እንቅፋት ሆነባቸው። በማይሆን ጊዜ በሙዚቃ ፍቅር ወደቁና ከማይሆን የሙዚቃ በረሃ ንዳድ ጋር ትግል ገጠሙ። እንደ ውሃ ጥም ከሚቃጠሉበት በረሃ አምልጠው ለመውጣት ብዙ ትግል ቢያደርጉም አሸዋው እያንሸራተተ መልሶ ይጥላቸው ጀመር። ከሙዚቃው ፍትጊያ ባሻገርም ሌላ የሕይወት ቀውስ ሰተት ብሎ ወደ እሳቸው መጣ። ጊዜው የጣሊያኑ ፋሽስት ኃይል ኢትዮጵያን ለመውረር ትግል የገጠመበት ነበር። እማሆይም ከመላ ቤተሰባቸው ጋር በመሰደድ የጥቁር አንበሳ ጦርን ተቀላቀሉ። በጦርነቱም በሽምቅ ውጊያ ሲፋለሙ የነበሩት ሶስት ወንድሞቻቸው ተገደሉ። ጦርነቱ ሲፋፋምም ቤተሰባቸው በሙሉ ተግዘው ወደ ኔፕልስ፣ ጣሊያን በግዞት ተወሰዱ። ኋላም ኢትዮጵያ አሸንፋ ከጦርነቱ ወላፈን ሀገር ምድሩ ቀዝቀዝ ሲል ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደረገ።
ከዚህ በኋላም ቢሆን የሙዚቃ ፍቅሩ ያልበረደላቸው እማሆይ ጽጌ ማርያም በሀገር ውስጥ አልሆን ቢላቸው ጊዜ ወደ ውጭ ሄደው የሚማሩበትን ሌላ እድል የማግኛ መንገድ ሲያሰላስሉ ቆዩና በመጨረሻም የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጸሐፊ ሆነው ተቀጠሩ። የሙዚቃን መግቢያ በር በዚህ አገኛለሁ ብለው የገቡበት መንገድም ሳይሳካ ቀረ። ለስራ ሳይሆን ሙዚቃን ፍለጋ ነበርና የገቡት፣ ይሄኔ ላይ ታቹን ቢያዩ ምንም ጠብ የሚል ነገር ጠፋ። ከሀገር ውጭ ወጥተው ሙዚቃ ለመማር የሚያስችላቸውን የይለፍ ፈቃድ ተከለከሉ። ከዚያ የራሱ ጉዳይ ሲሉ ስራውን ለቀው ወጡ። ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ተስፋን መቁረጥ የተሳናቸው እኚህ ሴት እንደምንም ብለው አባታቸውን በማሳመን በ21 አመታቸው ከያኔው ታዋቂ ቫዮሊን ተጫዋች አሌክሳንደር ኮንትሮዚ ስር ሙዚቃን ለመማር ወደ ግብጿ ካይሮ ከተማ በማቅናት የሙዚቃ ትምህርታቸውን ቀጠሉ። የሙዚቃ ሕይወት እማሆይን የምትፈትነው እያስተማረች ቢሆንም ፈተናው ግን ማብቂያ አነበረውም። ከካይሮ ከትመው የሙዚቃ ትምህርታቸውን ገና ከመጀመራቸው የጤና እክል ገጠማቸውና አቋርጠው በድጋሚ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ተገደዱ።
አሁን ግን እኚህ ታላቅ ሴት ትግላቸውን የምርም ለማቆም የወሰኑ ይመስላሉ። ሁለተኛው የሕይወት ምርጫቸውም የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው። 1940 ዓም በወቅቱ የ25 አመት ኮረዳ ነበሩ። የዛኔ ስማቸው እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ አልነበረም። የውብዳር ገብሩ ተብለው ነበር የሚጠሩት። ከዚያ ሁሉ ውጣውረድ ተላቀው ቀሪውን የሕይወት ዘመን ለፈጣሪያቸው ለመስጠት ወሰኑ። ሁሉንም ተውና ወደ ግሸን ማርያም ገዳም መነኑ። ከሁለት አመታት በኋላም አዲስ ማንነትን ይዘው በአዲስ የምናኔ ስም መጡ። በዚያው የግሸን ማርያም ውስጥ የውብዳር የሚለውን የዓለም ስማቸውን ገፈው ወደ ጽጌ ማርያም ቀየሩ።
በንጉሥ ኃይለሥላሴ ዘመን እማሆይ ጽጌ ማርያም የከንቲባ ልጅ እንደመሆናቸው የተለያዩ ትላልቅ ዝግጅቶች በሚኖርበት ወቅት ይጠሩ ነበር። ብዙ ጊዜም ንጉሡ ፊት እየቀረቡ ያንጎራጉሩላቸው ነበር። እማሆይ ከመነኑ ከአመታት በኋላ ወላጅ አባታቸው በጠና መታመማቸውን ሰምተው ቢመጡም ከንቲባ ገብሩን ግን በሕይወቱ አላገኟቸውም። ንጉሡም እማሆይን በማስጠራት ምን እንደሚፈልጉ ጠየቋቸው። እማሆይም ከእናታቸው ጋር አብረው ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንደሚፈልጉ ገለጹላቸው። ከእናታቸውም ጋር ወደዚያው በማቅናት ቆይታቸውን በቤተክርስቲያንና በገዳማት አደረጉ። በቤተክርስቲያን ውስጥም በአስተርጓሚነት ያገለግሉ ነበር። ኑራቸውንም አንዴ ኢትዮጵያ አንዴ እስራኤል ሀገር እያሉ ቢቆዩም ከ1975 ዓ.ም ወዲህ ግን ወደ ኢትዮጵያ አልተመለሱም ነበር።
እማሆይ ጽጌ ማርያም በ1959 ዓ.ም በጀርመን ሀገር ሆነው የመጀመሪያውን የሀገራችንን የፒያኖ የረቂቅ ሙዚቃ ሸክላ አሳትመዋል። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በሸክላ ያስቀረጹት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሲሆኑ፣ እማሆይ ፅጌ ማርያም ደግሞ የኢትዮጵያን ክላሲካል ሙዚቃዎችን በሲዲ በማስቀረጽ ለዓለም ሕዝብ ያስተዋወቁ የመጀመሪያዋ እንስት ሆነዋል። እንዲያው እሳቸው በሁሉም ነገር የመጀመሪያዋ ሴት መሆን አይታክታቸውምና ከሙዚቃው ሌላም በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ለመስራት እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በይፋ መዝሙርን የዘመሩ የመጀመሪያዋም ሴት ጭምር ናቸው። እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ፣ ዕብራይስጥኛ፣ አማርኛና ግዕዝን ጨምሮ ወደ 7 የሚጠጉ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው የሚናገሩ ሲሆን እድሜያቸው ገፍቶ ካረጁ በኋላ እንኳን መኪና ማሽከርከርና ፈረስ መጋለብ ያዘወትሩ ነበር። የተለያዩ የሙዚቃ ስራዎቻቸውንም በተለያዩ ኮንሰርቶች ላይ በማቅረብ የሚገኘውንም ገንዘብ ለድሆች መርጃ አውለዋል። ከእነዚህም አንዱ የ1966 ዓ.ም በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች መርጃ እንዲውል ‘ደ ፋሚን ዲዛስተር’ የተሰኘው የሙዚቃ ስራቸው ነው። በፈረንጆቹ ሚያዚያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም የ93 አመት አዛውንት ስለነበሩት እማሆይ ጽጌ ማርያም ዘጋርዲያን ‘ቤት-አልባዋ ከርታቴ’ በሚል አርዕስት ሰፊ ሀተታ ይዞ ወጥቶ ነበር። በሀተታውም የልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ስለሆኑት ስለ እኚህ የ93 አመት አዛውንት በደንብ አድርጎ ከትቦላቸዋል።
የረቂቅና ጥዑም ሙዚቃ እናት የነበሩት እማሆይ ጽጌ ማርያም በርከት ያሉ የረቂቅ ሙዚቃ አልበሞችን አሳትመዋል። ‘ኢትዮ ፒክ’ የተሰኘው አልበምም ከቀድሞ ቅንብራቸው የተመረጡ ስራዎች የተካተቱበት የመጨረሻው አልበማቸው ነበር። ከመነኮሱ በኋላ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በእግዚአብሔር ቤትና በኢየሩሳሌም ያሳለፉ ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት ኮንሰርቶችን ከማዘጋጀት አልቦዘኑም ነበር። የሚያቀርቧቸው ስራዎችም በፒያኖና ቫዮሊን አማካኝነት ሲሆን አስቀድመው በቂ ዝግጅት በማድረግ በተጠና መልኩም ነበር። ጆሮውን ከፍቶ ሙዚቃቸውን ለሚያደምጥም በችሎታቸው እጅን በአፍ የሚያስጭኑ ድንቅ የሙዚቃ እናት ነበሩ።
የሙዚቃ ሕይወታቸው እጅጉን ፈተና የበዛባትና በውጣ ውረዶች የተሞላች ባትሆን ኖሮ ምናልባትም ከነሞዛርት እኩል ዛሬ ዓለም በሙዚቃው ከምታወድሳቸው ሰዎች መሃከል አንዷ እማሆይ ጽጌ ማርያም በሆኑ ነበር። ያም ሆነ ይህ ግን ዛሬም ሊወደሱ የሚገባቸው ታላቅ የሙዚቃ እናት ናቸው። የሙዚቃን ጉዞ ገና በስድስት አመታቸው ጀምረው እየወደቁና እየተነሱ ለ94 አመታት ተከተሏት። እድሜያቸው አንድ መቶ አመት ሲደፍን ሞት ጥላውን አጠላባቸውና ሁሉንም ጉዞ አቆሙ። የአንድ ክፍለ ዘመን ሩጫቸውም ከሰሞኑ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም ተቀጨ። የኢትዮጵያ የረቂቅ ሙዚቃ እናት አረፉ። አፈሩን ያቅልልላቸው።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም