አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ በሚገኙ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከሚሰሩ 193 ፕሮፌሰሮች መካከል አራቱ ብቻ ሴቶች መሆናቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ከ193ቱ ፕሮፌሰሮቸ መካከል ደግሞ 104 የሚገኙት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው።
በሳይንና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የፖሊሲ ዕቅድ፣ክትትልና ግምገማ ዳይሬ ክተር አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በሚኒስቴሩ ስር ካሉት 45 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰሩ 193 ሙሉ ፕሮፌሰሮች ይገኛሉ። ከዚህ ውስጥ 189 ወንዶች ሲሆኑ አራቱ ብቻ ሴቶች መሆናቸው ሲታይ የፆታ ስብጥሩ ላይ ብዙ ስራ እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ይቻላል።
እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ፤ ካሉት
አራት ሴት ፕሮፌሰሮች መካከል ሶስቱ የሚገኙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን አንዷ ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እየሰሩ ይገኛሉ። የሴት ፕሮፌሰሮች ቁጥር ይህን ያህል ያነሰው ቀድሞ ለሴቶች ከሚሰጠው አነስተኛ ድጋፍ እና ወደ ጥናትና ምርምር ስራ የማዘንበሉ ልምድ አነስተኛ ከመሆኑ የመነጨ ነው። የቀድሞውን ደካማ ድጋፍና የምርምር ልምዱን ለመቀየር እየተሰራ በመሆኑ በቀጣይ ጊዜያት በምርምር ውጤታቸው እና በጥናታዊ ጽሁፍ ህትመታቸው የተመረጡ ሴቶች ወደ ሙሉ ፕሮፌሰርነት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅተ 277 ሴቶች በመሪ ተመራማሪነት ደረጃ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ደሳለኝ፤ ሴቶች በምርምር እንዲሳተፉ ልዩ ስልጠና እና ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። በዓመት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርምር እና ጥናት በአጠቃላይ አንድ ቢሊዮን ብር እንደሚመደብም ተናግረዋል። አንድም ፕሮፌሰር የሌላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ቢኖሩም እንደ አመሰራረት ቆይታው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ፕሮፌሰሮችን መያዙን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ 104 በሙሉ ፕሮፌሰርነት የሚሰሩ ይገኛሉ። ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል በፕሮፌሰሮች ብዛት ከፍተኛው ቁጥር ቢሆንም ለዩኒቨርሲቲው ግን በቂ ነው ተብሎ አይገመትም። ምክንያቱም ካለው 3ሺ 34 የመምህራን ቁጥር አንጻር ሶስት ነጥብ አምስት በመቶው ብቻ ናቸው ፕሮፌሰሮቹ። 40 በመቶቹ ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ወደ ፕሮፌሰርነት ደረጃ እንዲያድጉ ምርምሮች ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም
ጌትነት ተስፋማርያም