አዲስ አበባ፡- ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ ነፃነት ቢታይም የሕትመት ዋጋ መወደድ ለፕሬስ ውጤቶች ማነቆ እንደሆነ ተገለጸ።
የአዲስ ዘይቤ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ አቤል ዋቤላ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ መንግሥት የፕሬስ አፈናን ቢያስቀርም አሠራሩን ግን አላሻሻለም፤ የወረቀት ዋጋ 30 በመቶ ጨምሯል።
የፕሬስ ኢንዱስትሪ እንደ ሽንኩርትና ቲማቲም ገበያ መሆን የለበትም፤ ፕሬሱን እንደ መንግሥት አካል አላየውም። የወረቀት ዋጋ መወደድ የማተሚያ ዋጋ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጓል ብለዋል።
አዲስ ዘይቤ ጋዜጣም የተቋረጠችው በዚሁ ችግር እንደሆነ የገለጹት አቶ አቤል፤መንግስት ይህን ችግር እስካልቀረፈ ድረስ የፕሬስ ነፃነትን አስጠብቄያለሁ ማለት እንደማይቻል ጠቅሰው፣ በዚህ ሁኔታ አዳዲስ የህትመት ውጤቶች ወደ ገበያ ሊመጡ አይችሉም ብለዋል።
አሁን ከሕመት ውጭ የሆነው የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ በበኩላቸው፣ የሕትመት ዋጋ መናር የፕሬስ ኢንዱስትሪውን እየጎዳ እንደሆነ ይገልጻሉ። የታሰሩ ጋዜጠኞች መለቀቃቸው፣ የተዘጉ የህትመት ውጤቶችና ድረ ገጾች መከፈታቸው በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የታየ ለውጥ ቢሆንም የህትመት ዋጋና የማተሚያ ቤት ችግር ፕሬሱን እያቀጨጨው መሆኑን አመልክተዋል።
‹‹በአገሪቱ ውስጥ አንድ ለእናቱ የሆነው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም›› የሚሉት አቶ ፍሬው፣ ጋዜጦችን ከሚወጡበት ቀን እያዘገየ በብቸኝነት መቆጣጠሩ ጋዜጦችን ለኪሳራ እንዳጋለጠ ይናገራሉ። በዕለታቸው ባለመውጣታቸው ከደንበኞቻቸው ጋር እንዲቆራረጡ ያደርጋል ብለዋል።
የወረቀት ዋጋ መሻሻል ሲገባው በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ የህትመት ውጤቶች ሥራቸውን ለማቋረጥ እያስገደደ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍሬው፣መንግስት በወረቀት ዋጋ ላይ የተሻለ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ያሳስባሉ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምክትል ሥራ እስኪያጅ አቶ ወንድም ተክሉ በበኩላቸው፣ የህትመት ዋጋ መናር በድርጅቱ የህትመት ውጤቶች ሥርጭት ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል። ዕለታዊ የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ እስከ 12 ሺህ 500 ኮፒ ይታተም ነበር፤ በሕትመት ዋጋ መጨመር ምክንያት ግን ወደ 12 ሺህ ኮፒ ብቻ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። በመላ አገሪቱ የሚሰራጭ ይህ ብሔራዊ ጋዜጣ የኮፒ ብዛቱ ከዚህ በላይ ከፍ ማለት ሲገባው ዝቅ ማለቱ የችግሩን አሳሳቢነት እንደሚያሳይ ነው ምክትል ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት።
የአቶ ፍሬውን ሃሳብ የሚጋሩት አቶ ወንድም፣ የማተሚያ ቤት ችግርም ሌላው የህትመት ውጤቶች ማነቆ ነው። የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጋዜጦችን ማዘግየት ብቻ ሳይሆን ዘግይቶም ጥራቱን ያልጠበቀ ህትመት ነው የሚያወጣው። በዕለቱ ባለመውጣቱና ጥራቱን ባለመጠበቁ ውል ያቋረጡ የማስታወቂያ ደንበኞች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬ ክተር አቶ ዳንኤል ሃይለ እንደሚሉት፣ የማተሚያ ዋጋ የጨመረው የወረቀት ዋጋ ስለጨመረ ነው። የወረቀት ዋጋ ብቻ ሳይሆን ለማተሚያ የሚያስፈልጉ ሌሎች መሳሪያዎችና ኬሚካሎች ዋጋቸው እያሻቀበ መጥቷል። የጋዜጣ ወረቀት ሙሉ በሙሉ ከውጭ ነው የሚመጣው፤ ይህም የውጭ ምንዛሬ ይጠይቃል። በዓለም ገበያ የጋዜጣ ዋጋ 46 በመቶ ነው የጨመረው። በዚህም ምክንያት ብርሃንና ሰላም በደንበኞቹ ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ ተገዷል። እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ ማተሚያ ቤቱ ማህበራዊ ኃላፊነት ስላለበት 16 በመቶውን በራሱ ወጪ ሸፍኖ በደንበኞቹ ላይ የ30 በመቶ ጭማሪ ነው ያደረገው።
የወረቀትና ሌሎች ማተሚያ ቁሳቁስ ዋጋ መጨመር በአሳታሚዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በማተሚያ ቤቱ ላይም ኪሳራ እያመጣ እንደሆነ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። ብርሃንና ሰላም ገቢው ከአሳታሚዎች ነው፤ በዋጋ መወደድ ምክንያት ጋዜጦችና መጽሔቶች ሲቋረጡ በዚያው መጠን የማተሚያ ቤቱ ገቢ ይቀንሳል ማለት ነው ። መንግስት የወረቀትና የማተሚያ ቁሳቁስ ከቀረጥ ነጻ ማስገባትና ሌሎች ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዳለበት ያሳስባሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም
ዋለልኝ አየለ