አዲስ አበባ፦ ከቻይናው የ«ቤልትና ሮድ» ጉባኤ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከተለያዩ የቻይና ኩባንያዎች ጋር አራት የመግባቢያ ሰነዶችን በመፈራረሙ ፋብሪካቹ በኢትዮጵያ እንደሚሠሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ፤ አራት የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ፋብሪካ ከፍተው ለመሥራት ትናንትና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚ ሽን ጋር ስምምነት ፈርመዋል።
በስምምነቱ ቴይሰን ቡድንና ግሪን ዳይመንድ የተባሉት ኩባንያዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ በዓመት እስከ አንድ ሚሊየን ቶን ወረቀት ለሚያመርት የቀርከሀ ወረቀት ፋብሪካ ለመገንባት አቅደዋል። ፋብሪካው በኢትዮጵያ ያለውን የወረቀት እጥረት በመቅረፍ የቀርከሃ ሀብትን ወደ ገቢ ምንጭነት መቀየር እንደሚያስችል ይጠበቃል።
አሚቲ የተባለው የህትመት ተቋም በበኩሉ በኢትዮጵያ ማተሚያ ቤት ለመክፈት ስምምነት አድርጓል። ሲ.ጂ.ሲ.ኦ.ሲ ቡድን ደግሞ በዓመት እስከ ሦስት መቶ ሺ ከብትና ሦስት ሚሊዮን በጎች ለገበያ የሚያቀርብ ቄራ ለመገንባትም ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ዜንዴ የተባለው የሕክምና ውጤቶች አምራች ደግሞ በቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ የሕክምና መገልገያዎች ማምረቻ፣ የቁስል ማከሚያ፣ የቀዶ ህክምና ማካሄጃ እና ሌሎች የሕክምና ቋሚ መገልገያዎችን ለማምረት ተስማምቷል።
በሌላ በኩል የ«ቤልትና ሮድ»ጉባኤ ቻይና የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢ.ቲ.አር.ኤስ.ኤስ-1 የተሰኘው ባለዘርፈ ብዙ የርቀት የሕዋ ሳተላይት በቻይናው የሕዋ ቴክኖሎጂ አካዳሚ ተገኝተው ጎብኝተዋል::
በኢትዮጵያ የሕዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት (ኢ.ኤስ.ኤስ.ቲ.አይ) ሥር ሳተላይትን በማደራጀት በቻይና መንግሥት ዕርዳታ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ወደ ጠፈር ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል:: ሳተላይቱ ከመጠቀ በኋላ ለግብርና ዝግጅት፣ ለድርቅ ቅድመ ጥንቃቄና ለደን ጥበቃና አስተዳደር እንዲሁም ለአየር ንብረት ሁኔታ ትንበያ አገልግሎት እንደሚውል የጽሕፈት ቤቱ መረጃ አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም
በጋዜጣው ሪፖርተር