አዲስ አበባ፡- የአንድ አብራክ ክፋይ የሆኑት ሦስቱ ሕፃናት በዓለም ዝነኛ የፎቶግራፍ ባለሙያ (ፎቶ ግራፈር) ለመሆን የጀመሩት ጥረት አንድ ቀን ዓለምን አጃዒብ ሊያሰኝ እንደሚችል ከወዲሁ ተስፋ አድርገዋል።
ሕፃን ኤሊያታ ዳንኤል የ10 ዓመት ታዳጊ ሲሆን፤ ከሦስት ዓመቱ ጀምሮ አነጋጋሪ ፎቶ ሲያነሳ ቆይቷል፡፡ ታናሽ እህቱ ማራማዊት ዳንኤል ደግሞ ስምንት ዓመቷ ነው፤ እርሷም ከሦስት ዓመቷ ጀምሮ የፎቶ ጥበብን ተክናለች። የስድስት ዓመቷ ታናሽ እህታቸው ሲፓራ ዳንኤልም ከሁለቱ ታላላቆቿ በመቀጠል ከማን አንሼ በሚል እልህ እንደ ፓፓራዚ ፎቶ ማ ደን ጀምራለች፡፡
የካሜራ አዳኞቹ አባት አቶ ዳንኤል እንደሚሉት፤ የመጀመሪያ ልጃቸው ኤሊያታ የሦስት ዓመት ሕፃን ሳለ በሞባይል የሚያነሳቸው አስገራሚ ፎቶዎች እርሳቸውንና ባለቤታቸውን በእጅጉ ስላስደመማቸው ፍላጎቱን በመረዳት እገዛ አድረገውለታል። የሦስት ዓመት ሕፃን ሳለም ዲጅታል ካሜራ ገዝተውለታል። በሕፃንነቱም የበርካቶችን ቀልብ የገዙ ፎቶ ግራፎችን ማንሳቱን ጠቁመዋል። ሁለቱ ታናናሽ እህቶቹም የእርሱን ፈለግ ተከትለው ፎቶ ማንሳትን ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል።
የፎቶግራፈሮቹ እናት ወይዘሮ ዓይዳ ሠለሞን በበኩላቸው፤ ልጆቻቸው ያለ ማንም አጋዥና አስተማሪ የሰለጠኑ ባለሙያዎች የማያነሷቸውን ፎቶግራፎች በብዛት በማንሳታቸው በርካታ ሠዎች እየተደነቁባቸው መሆኑን አብራርተዋል።
ትልቁ ልጃቸው ኤሊያታ እስከአሁን 5ሺ ፎቶግራፎችን ያነሳ ሲሆን፤ ሁለቱ ሴቶች ደግሞ እያንዳንዳቸው ከ5 መቶ እስከ 6 መቶ የሚደርሱ አስደናቂ ፎቶግራፎች በካሜራቸው ማስቀረታቸውን ገልጸዋል። ፎቶ ግራፎቹ በአገር ውስጥ እና በባህር ማዶ የተነሱ ናቸው።
ምንም እንኳን ልጆቹ በፎቶ ማንሳት የተካኑ ቢሆንም፤ የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ የሚያዘጋጁ አካላት እነዚህን ልጆች የማሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው አብራርተዋል። ቀደም ሲልም የፎቶ ዓውደ ርዕይ በማዘጋጀት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 15 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ፕሮፖዛል ቢዘጋጅም፤የሚመለከታቸው አካላት ቅንነት ጉድለት እቅዱ አለመሳካቱን አስታውሰዋል።
ሕፃን ኤሊያታ በ19ኛው፣ በ21ኛው እና በ28ኛው የአፍሪካ መሪዎች መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት ፎቶዎችን አንስቷል። በተጨማሪም በአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ በመገኘት መረጃዎችን በካሜራው ማስቀረቱን የሚያሳዩ መረጃዎች በእጁ ላይ ይገኛሉ። ታናሽ እህቱ ማራማዊትም በ28ኛው የአፍሪካ መሪዎች መደበኛ ስብሰባ ሁነቶችን በካሜራዋ አስቀርታለች።
ወላጆቻቸው የራሳቸውን ፎቶ ጋላሪ በመኖሪያ ቤታቸው የከፈቱላቸው ሲሆን፤ በሂደት ራሳቸውን ችለው ጋለሪ እንዲኖራቸው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡ ፡አጋዥ አካላት ከተገኙም በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም
ክፍለዮሐንስ አንበርብር