ሁለቱን ወራት በጾምጸሎት ያሳለፈው ህዝበ ክርስቲያን የፋሲካን በዓል ለመቀበል ዝግጅቱን ከወዲሁ ጀምሯል። በዛሬዋ የቅዳም ሹር ዕለት ደግሞ የበዓሉ ድባብ ይበልጥ ይደምቃል። ከትላንትናው የስነስቅለትና የስግደት ውሎ በኋላም ዛሬን ለነገው ፋሲካ የሚያውሉት በርካቶች ዓውደ ዓመቱን እንደየአቅማቸው ለማክበር ደፋቀናውን ተያይዘውታል።
የጎዳናው ግርግርና የገበያው ውሎ ከወትሮው ለየት ብሏል። በእጃቸው ዶሮ አንጠልጥለው፣ ሙክት በጎች የሚጎትቱ፣ ለምለም ቄጤማ ታቅፈው የስጦታ ዕቃዎች የያዙ፣ በአዳዲስ ልብሶች ደምቀው ለነገው በዓል የሚዘጋጁ ጥቂቶች አይደሉም። መንገዱ በበዓላት ሙዚቃ፣ በገዢና ሻጮች ግርግር ደምቋል። ወሬና ጭውውቱ ሁሉ በታላቁ ዓውደ ዓመት በዓለ ፋሲካ ላይ አተኩሯል።
በብዙዎች ጓዳ የነገው ፋሲካ በተለየ ሙላት እየተሰናዳ ነው። የዶሮ ወጡ፣ የቅርጫ ስጋው፣ የጠላና ዳቦው ዝግጅትም አስቀድሞ ተጠናቋል። በበርካቶች ዘንድ የተለየ ግምት የሚሰጠውን የፋሲካ በዓል ተከትሎ የዳግም ትንሳኤው መሰናዶ ይቀጥላል። ይህ ቀን ወዳጅ ከዘመድ ተገናኝቶ አብሮነቱን የሚያጸናበት ነው። የዕለተ- ፋሲካ እርሾም ቀጣዮቹን ሁለት ወራት በፍስክ አክርሞ ወደ ክረምቱ ያሸጋግራል።
በእነ ወይዘሮ አዘነጋሽ ገላሆዴ ቤት ግን ይህ ሁሉ መሰናዶ አይታወቅም። ወይዘሮዋ ሁለት ወራትን በጾም ጸሎት አሳልፋ ለቀኑ ዋዜማ ደርሳለች። በነገው ዕለትም ታላቁ የፋሲካ በዓል እንደሚከበር አይጠፋትም። ይሁን እንጂ እንደሌሎቹ ሴቶች ዘንቢሏን አንጠልጥላ ገበያ አልወጣችም። እንደብዙዎቹም ከቤቷ ጓሮ የዶሮና በግ ድምፅ አልተሰማም። አዘነጋሽ ሁለቱ ልጆቿ ለበዓሉ አዲስ ልብስ እንድትገዛ እየወተወቷት ነው። እሷ ግን ይህን የማድረጉን አቅም አላገኘችም።
ዛሬ ላይ ግን አዘነጋሽ ደርሶ ሆድ ይብሳት ይዟል። ሰዎች ስለ አውደዓመት ሲያወሩም ዕንባ እያነቀ ይከፋት ጀምሯል። የልጆቿን የልብስ ግዢ ፍላጎት ያለመመለሷ ደግሞ ይበልጥ እያስጨነቃት ነው። ባለፉት ዓውደ ዓመቶች እሷን ያስታወሱ ወዳጅ ዘመዶቿ ካላቸው ቆንጥረው ከቀመሱት ሲያቃምሷት ቆይተዋል። እሷም ብትሆን የላስቲክ ጎጆዋን በፈንዲሻና በቡና ጭስ ዓውዳ እንግዶቿን በምስጋና ስትሸኝ ነበር።
አሁን ላይ ግን ከማንም «የእንኳን አደረሰሽ» ምኞት አልደረሳትም። ሁኔታው መዘግየቱ እያስከፋት ቢሆንም ልጆቿን ከአቻዎቻቸው ላለማሳነስ የአቅሟን ለማድረግ ተዘጋጅታለች። የድሮና ዘንድሮ ልዩነቷ ቢሰፋም ዛሬም ለጎደለ ጎጆዋ ሩጫዋን አታቆምም። ይህን ስታስብ ደግሞ በአንገቷ የሚወርደውን ትኩስ ዕንባ ደጋግማ ትጠርጋለች። ነገን በተስፋ አቅዳም የፊቷን በጎነት ታልማለች።
ወይዘሮ ሲሳይ አሰፋ የአስራአንድ ዓመት ልጇን እንዳዘለች ከወዲያ ወዲህ እያለች ነው። ሕፃን የአብስራ የአካልጉዳተኛ በመሆኑ እንደልብ መራመድ አይችልም። ልጁ ምክንያት የለሽ በሆነ ብስጭት ደጋግሞ ማልቀስ ከጀመረ ቆይቷል። ሲሳይ እሱን ጨምሮ የስድስት ዓመት ሴት ልጇን በኪራይ ቤት ይዛ ትኖራለች። የቀን ሠራተኛው ባለቤቷ የወር ገቢ በቂ የሚባል አይደለም።
ወይዘሮ ሲሳይ እንዲህ እንደአሁኑ በዓል በደረሰ ጊዜ ከጎረቤቶቿ ጋር የአቅሟን ተካፍላ ታሳልፋለች። ምንም እንኳን በዓሉን ሙሉ የሚያደርግ መሰናዶ ባይኖራትም ሳይከፋት ዕለቱን የማክበርን ልምድ ታውቅበታለች። ሲሳይ በዓሉ ፋሲካ እንደመሆኑ የተለየ ትኩረት እንደሚሰጠው ታውቃለች። እንደሌሎቹ ሁሉን ያሟላ ዝግጅት ማድረግ ብትፈልግም ግን ፈጽሞ አይቻላትም።
ቀደም ሲል አንዳንድ ድርጅቶች እንደ እሷ ላሉ እናቶች ለፋሲካ በአል የገንዘብ፣ የዘይትና የዱቄት ድጋፍ ያደርጉላቸው ነበር። ዘንድሮ ግን ከአንድ መቶ ብር የዘለለ ስጦታ ማግኘት አልቻሉም። ሲሳይ የዓመት በዓል ጓዳዋ ሙሉ እንዳልሆነ ታውቃለች። የፋሲካው ዶሮም በቤቷ እንደማይጮህ ይገባታል። የተሰጣትን አንድ መቶ ብር ግን ለቁምነገር አስባዋለች። ሽንኩርት ገዝታበትና ካላት አክላበት በግማሽ ኪሎ ስጋ ቤቷን ታውዳለችና።
ወይዘሮ አሰገደች እንድሪስ በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ ዘጠኝ ሴቶችና ሕፃናት ጽህፈት ቤት የሕፃናት ድጋፍና እንክብካቤ ባለሙያ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በወረዳው እንደ ወይዘሮ አዘነጋሽና ወይዘሮ ሲሳይን የመሰሉ በርካታ ድጋፍ የሚያሻቸው ሴቶች ይገኛሉ። እነዚህ እናቶች የኑሮ ጫና የከበዳቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከዕለት ፍጆታቸው የሚተርፍ የዓውደ ዓመት መወያ እንደማይኖራቸው ይታወቃል።
ወረዳው ቀደም ሲል ለተለያዩ ድርጅቶች በሚያቀርበው የ«እንረዳዳ» ጥያቄ ለዶሮ መግዣ የሚሆን ገንዘብን ጨምሮ የዱቄትና ዘይት ድጋፍ ያበረክትላቸው ነበር። ዘንድሮ ግን በሀገሪቱ ባጋጠመው የመፈናቀል ምክንያት ከድርጅቶቹ የተለመደውን ለማግኘት የሚቻል አልሆነም። ይሁን እንጂ ከጠቅላይ ቤተክህነት የተገኘውን ስጦታ ለአንድ መቶ አርባሁለት አቅመ ደካማ ሴቶች አንድ አንድ መቶ ብር ለመስጠት ተችሏል። ገንዘቡ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚበቃ ባይሆንም ለዕንቁላል እንኳን እንዲውል በማሰብ መሰጠቱን ወይዘሮ አሰገደች ይናገራሉ።
«የቅድሰተ ማርያም ሰፈር ለአረጋውያን» የተሰኘው የበጎ አድራጎት ማህበር አቅማቸው የደከመና እጅ ያጠራቸው ወገኖችን በመጎብኘት ይታወቃል። ማህበሩ በተለይ አውደዓመት በደረሰ ጊዜ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ወገኖች «እንኳን አደረሳችሁ» ለማለት ረፍዶበት አያውቅም።
የማህበሩ መስራችና ሥራአስኪያጅ አቶ ደምሴ ተሰጋ እንደሚሉት ዘንድሮም ለፋሲካ በዓል ይሆን ዘንድ ከበጎ ፈቃደኞች ያሰባሰበውን ገንዘብ ለአቅመ ደካማ ወገኖች አከፋፍሏል። ሁለት መቶ ሃምሳ ለሚሆኑ ሰዎች በተደረገው የአምስት መቶ ብር ድጋፍም ዳቦ ቆርሶ ቡና በማፍላት «የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ተላልፏል።
አቅመ ደካማ ወገኖችን መርዳት ዓላማ ያደረገው ይህ ማህበር በአገርውስጥና በውጭ አገራት ከሚገኙ በጎ ፈቃደኞች ገንዘብና ቁሳቁስ በማሰባሰብና የነፃ ህክምና በማፈላለግ መሥራት ከጀመረ ከሰባት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።
እንደ ቅድስተ ማርያም ለአረጋውያን ማህበር ሁሉ «የእንረዳዳ» የአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበርም የፋሲካን በዓል ከአቅመ ደካሞች ጋር ለማሳለፍ ተዘጋጅቷል። የማህበሩ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ሰናይት ድንቁ እንደሚሉት የድርጅቱ አንዱ ዓላማ በተመረጡ ሃይማኖታዊ በዓላት ቀን እጅ ያጠራቸው ወጎኖችን በማሰብ በጋራ ማክበር ነው። የዘንድሮውን ዕለተ ፋሲካን ለማክበርም በራስ ደስታ ሆስፒታል አካባቢ ለሚገኙ አንድ መቶ አቅመ ደካሞች የቅርጫ ስጋን የማከፋፈል ዕቅድ ተይዟል።
ይህ ልማድ ከሃያ ዓመታት በላይ የዘለቀና ሁሌም በታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓላት የሚከወን መሆኑን የሚገልጹት ወይዘሪት ሰናይት ለዓላማው መሳካት በጎ ፈቃደኛ ከሆኑ አባላትና ከተለያዩ ተቋማት ገቢ ማሰባሰብ መቻሉን ይገልጻሉ። ማህበሩ በዚህ ብቻ ሳይወሰን የዳግማይ ትንሳኤ በዓልን ከአረጋውያን ጋር በተለየ ውሎ የሚያሳልፍ ሲሆን በዕለቱም አንድ መቶ አምስት ዓመት ዕድሜ የሚሞላቸውን የወይዘሮ ሀዳስ አረጋዊ ልደትን በታላቅ ድምቀት ያከብራል።
«የስጦታ ጥቂት የለውም» እንዲሉ እያንዳንዱ ሰው የአቅሙን መወርወር ከቻለ ችግሮችን ለማቃለል መንገዱ አጭር ይሆናል። እነሆ! የፋሲካ በዓል ሊከበር የአንድ ቀን ለሊት ብቻ ቀርቶታል። በህዝበ ክርስቲያን ዘንድ ታላቅ ትኩረት የሚሰጠውን ዓውደ ዓመት በባዶ እጃቸው የሚቀበሉ ወገኖችን እያሰብን ጓዳቸውን ብንጎበኝ ደግሞ በዓሉ ይበልጥ ሙሉና በፍስሐ የተሞላ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም
መልካምስራ አፈወርቅ