በተለያዩ ከተሞች የሚስተዋለው የውጭ ሀገራት ገንዘብ ህገወጥ ምንዛሬ በትላልቅ አስመጪዎች እና በባንክ ማናጀሮች ዋነኛ ተዋናይነት የሚመራ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ገለጸ።
በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፋይናንስ ወንጀሎች ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ታደሰ አያሌው እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በህገወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ምንዛሬ ዋነኛ ተዋናዮች አስመጪዎች፣ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች በተለይም የባንክ ማናጀሮች ናቸው። በየአካባቢው የሚገኙት ዶላር መንዛሬዎች ግን ሶስተኛ ወይንም አራተኛ አካላት ናቸው።
እንደ ኮማንደር ታደሰ ገለጻ፣ በየአካባቢው የሚገኙት ዶላር መንዛሬዎች ዋነኛ የህገወጥ ተግባሩ ተዋናዮችን በውል የማያውቁ እና ለእነርሱ የሚሰሩ ናቸው። ህገወጥ ተግባሩ በተዋረድ (በኔትወርክ) የሚከናወን እና በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያላቸው አስመጪዎች የሚያንቀሳቅሱት ነው። በተጨማሪ የባንክ ማናጀሮች ዶላር ፈልጎ የመጣን ባለሀብት ቢሮክራሲ በማብዛት ዶላር እንደሌለ አስመስለው ያባርራሉ። በጎን ደግሞ ደላሎችን ልከው ወደ ህገወጥ መንገድ እንዲሄዱ በማመቻቸት ገንዘብ ተቀብለው ይሰጧቸዋል።
ኮማንደር ታደሰ እንደተናገሩት፤ በአንድ የአሜሪካን ዶላር ከ10 ብር እስከ አስራ አራት ብር ትርፍ በመውሰድም ከደላሎች እና በየደረጃው ካሉ ህገወጦች ጋር ይከፋፈላሉ። በተለይ በሶማሌ ክልል ቶጎ ውጫሌ የሚገሹ 16ቱም ባንኮች በህገወጥ የዶላር ምንዛሬ ውስጥ እንደሚሳተፉ መረጃ አለ። በሶማሌ ላንድ ጠረፍ ከተማዋ የሚገኙ እና በተለያዩ ከተሞች የሚሰሩ የባንክ ማናጀሮች በዚህ ህገወጥ ተግባር እንደሚሳተፉ የፌዴራል ፖሊስ መረጃው አለው። በሌላ በኩል በህገወጥ መንገድ ከአገር የዘረፉትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ለማንቀሳቀስ የሚፈልጉ ሰዎች ሀብታቸውን ወደ ዶላር መንዝረው ከአገር ለማስወጣት ይጠቀሙበታል።
በዚህ ዓመት በመርካቶ እንደተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ አሁንም በቀጣይ እንደሚደረግ የገለጹት ኮማንደር ታደሰ፤ ይሁንና ዋነኞቹ የምንዛሬው ተዋናዮችን ለመያዝ መረጃ ሳይሆን ማስረጃ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ለዚህ ደግሞ ህብረተሰቡ ተሳታፊ መሆን አለበት። ህብረተሰቡ ደግሞ መረጃ ቢያቀብልም መስካሪ ሆኖ የችግሩን አመንጪዎች ለመከላከል ፍላጎት አያሳይም። ፖሊስ ግን ገንዘብ የያዘን ሁሉ አስሮ መቅጣት ስለማይችል የህብረተሰቡ የማጋለጥ እና የመመስከር ልምድ መጠናከር አለበት። ፌዴራል ፖሊስም ማስረጃ ባጠናቀረ ወቅት ህገወጦችን ለመቅጣት የሚያስችል ስራ ማከናወኑ አይቀርም።
የኢኮኖሚ ምሁሩ ፕሮፌሰር ፍሰሀ ጽዮን መንግስቱ በበኩላቸው መንግስት ችግሩን ለመቀነስ በገቢ እና ወጪ ንግድ ላይ ያለውን ቁጥጥር ሊያጠናክር እንደሚገባ ገልጸዋል። አብዛኛው ነጋዴ ከዱባይ እና ከቻይና መኪናን ጨምሮ በርካታ ውድ ንብረቶችን ሲያስመጣ የውጭ ምንዛሬውን ከየት አግኝተህ አስገባከው? ተብሎ መጠየቅ እንዳለበት ጠቁመዋል። በተለይ ዋነኛ የሚባሉ አስመጪዎች እና ደላሎቻቸው ዶላሩን ከየት አግኝተው እቃውን ሊያስመጡ እንደቻሉ ጥናት ማድረግ እና ህጋዊነቱ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ካልተቻለ ችግሩን መቀነስ እንደማይቻል ተናግረዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ፍሰሀ ጽዮን ከሆነ፣ የውጭ አገራት ገንዘብ በህጋዊ መንገድ የሚዘረዝሩ ሰዎች ዞሮ ዞሮ የሚያስረክቡት ለትላልቆቹ አስመጪዎች ነው። በመሆኑም መንግስት ትኩረት ማድረግ ያለበት በአስመጪዎቹ ላይ ነው። አሁን ግን ቁጥጥሩ አነስተኛ እና ያልተቀናጀ በመሆኑ ማንም ከየት እንዳመጣው አይጠየቅም። ይህ አሰራር ደግሞ ህገወጦችን እንደፈለጉ የውጭ አገራት ገንዘብ ምንዛሬ ውስጥ እንዲሳተፉ እየገፋፋቸው ይገኛል።
ከብሔራዊ ባንክ እና ከባንኮች ማህበር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
እንደ ፌዴራል ፖሊስ መረጃ፤ በ2011 ዓመት በተካሄደው ድንገተኛ የፖሊስ ፍተሻ መርካቶ አካባቢ 83 ሰዎች በውጭ አገራት ገንዘብ ህገወጥ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውለዋል። በወቅቱም 17ሺ የአሜሪካን ዶላር ተይዟል። ይህ ቁጥር ግን ፖሊስ ሊይዝ ካሰበው ገንዘብ በእጅጉ ያነሰ ከመሆኑ ባሻገር ዋነኛ የገንዘብ ምንዛሬ ተዋናዮችን መያዝ ያስቻለ ፍተሻ አይደለም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም
ጌትነት ተስፋማርያም