ኢትዮጵያ እውቀታቸውንና ሃብታቸውን ሁሉ በመስጠት ብዙ ዋጋ የከፈሉላት ባለውለታ ልጆች አሏት። በተለይም በችግር ጊዜ ገሸሽ ሳይሉ ችግሯን ችግራቸው አድርገውና የመፍትሔ አካል ሆነው መድህን የሆኑዋት ምርጥ የአብራኳ ክፋዮች ቁጥር የሚናቅ አይደለም። ከእነዚህም የአገር ባለውለታዎች መካከል ብላቴን ጌታ ሎሬንዞ ታዕዛዝ አንዱ ናቸው። ብላቴን ጌታ ሎሬንዞ ትውልድም ሆነ እድገታቸው ቀድሞ የኢትዮጵያ አካል በነበረችው በአካለጉዛይ አውራጃ ዓዲ ቀይሕ ከተማ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአስመራና በከረን ከተሞች በሚገኙ የጣሊያን ትምህርት ቤቶች መከታተላቸውን የታሪክ ማህደራቸው ያመላክታል።
በኋላም በኢጣልያ አገዛዝ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ፤ እናም በአገር ተወላጆች ላይ ያደርግ የነበረውን ጭቆና በመቃወም በወቅቱ በአሥመራ የኢትዮጵያ ቆንሲል ከነበሩት ከደጃዝማች ነሲቡ ዛማኔል ጋር በመነጋገር በ 1912 ዓ.ም በኤደን በኩል ወደ አዲስ አበባ መጡ። በ1920 ዓ.ም ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን መጀመሪያ በኤርትራ የኢጣሊያ አስተዳደር የአስመራ ከተማ ገዢ ጽህፈት ቤት፣ በኋላም በአስተዳደሩ የሲቪልና የፖለቲካ ጉዳዮች ክፍል ተመድበው ሰርተዋል። በዘመኑ በፋሺስት ኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ትተዳደር በነበረው ኤርትራ የተንሰራፋው ግፍና መድልዖ በርካታ የኤርትራ ተወላጆችን ለስቃይ የዳረገ ነበር። በዚህ ምክንያት ከ100 ሺ በላይ የሚሆኑ ኤርትራውያን ፋሺስታዊውን ስርዓት ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
ብላታኔ ጌታ ሎሩንዞ በወቅቱ ኑሯቸው የተደላደለ ቢሆንም ፋሺስት በኤርትራውያን ወገኖቻቸው ላይ ያደርስ የነበረው ግፍና መከራ ግን ሁልጊዜም እረፍት የሚሰጣቸው አልነበረም፤ በስራቸውም ደስተኛ ሆነው አያውቁም። ስልጣናቸውን ለቀው በወገኖቻቸው ላይ ይደርስ የነበረውን መከራ አብሮ ለመካፈል ከጫፍ ደርሶ በነበረበት ወቅት ታዲያ የፋሺስት ስርዓትን ማገልገሉን ዕርም እንዲሉ ተገደዱ። በገዛ አገራቸው ከሰው በታች ሆኖ መታየቱ ሊሸከሙት የማይችሉት ነገር ሆነባቸው፤ ወትሮም የፋሺስትን ስርዓት ለመታገል የሚቆርጥበትን ቀን ሲጠብቅ ለነበረው ወጣት፤ ውሳኔውን ለነገ የሚተው አልነበረም፤ በዚህም የትውልድ አገራቸውን በመልቀቅ ወደ የመን ተሰደዱ።
እ.ኤ.አ በ1924 ዓ.ም በስደት የመን፣ ኤደን ከተማ ሳሉም የህይወታቸውን አቅጣጫ የለወጠ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት አልጋ ወራሽ የነበሩት ራስ ተፈሪ መኮንን፤ ለአንድ ተልዕኮ የመን አገር ኤደን ከተማ በሄዱበት አጋጣሚ ከሎሬንዞ ጋር ለመገናኘት ቻሉ፤ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ቢፈልጉ መንግስታቸው በደስታ እንደሚቀበላቸውም ቃል ገቡ። ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ገቡ፤ በችግር ጊዜ መሸሸጊያ እንደሆነቻቸው ሁሉ እርሳቸውም ለችግሯ ፈጥነው ደረሱላት። ሁኔታው ከዘመናዊ ትምህርት ጋር የተቆራኙና በአስተሳሰባቸው ተራማጅ የሆኑ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማገልገል ፈቃደኛ የነበሩ ግለሰቦችን ሲያፈላልጉ ለነበረው ለአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ጭምር መልካም አጋጣሚ ነበር። ኢትዮጵያ ከፋሺስት ኢጣሊያ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ትሆን ዘንድ በዲፕሎማሲው መስክ ታላቅ ተጋድሎ በማድረግ፣ ታሪክ በተለየ ሁኔታ ያስታውሳቸዋል።
ፋሺስት ኢትዮጵያን እስከወረረበት 1928 ዓ.ም ድረስም በፍትህ ሚኒስቴር በጸሃፊነት፣ በእንግሊዝ ሶማሊላንድና በኢትዮጵያ መካከል ድንበር ለማካለል በተሰየመው ኮሚቴ በአባልነት፣ በ1927 ዓ.ም በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የወልወል ግጭትን የሚያጣራው ቡድን አባል፣ የቀዳማዊ ሀይለሥላሴ የግል ጸሀፊ፣ እንዲሁም የዘውዳዊው መንግስት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። ብላቴን ጌታ ሎሬንዞ በፋሺስት ኢጣሊያ ዘመን የዘውዳዊው መንግስት የደህንነት መስሪያ ቤት፣ የሀረርጌ አካባቢ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ነበሩ። በማይጨው ጦርነት ወቅትም ስለ ጦርነቱ ሁኔታ የኢትዮጵያን መንግስት ቃል ለዓለም ማህበረሰብ የማቅረብ ኃላፊነት ነበራቸው።
በኢጣሊያና በኢትዮጵያ መካከል በተካሄደው የማይጨው ጦርነት፤ የፋሺስት ፍጹም የበላይነት የታየበት ነበርና በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ለማፈግፈግ ተገደደ። በዚህም በኮረም ላይ ኃይሉን አሰባስቦ፣ ዳግም ውጊያ ለመግጠም ንጉሰ ነገስቱ ሃሳብ አቅርበው ነበር። ይሁንና የቅርብ ባለሟሎቻቸውና ሹመኞቻቸው በነገሩ ላይ ከመከሩ በኋላ ዳግም ለውጊያ መነሳቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ የበለጠ እንደሆነ ለንጉሰ ነገስቱ ሃሳብ አቀረቡ። ይህን ተከትሎም የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በአብላጫ ድምጽ ንጉሰ ነገስቱ አገር ለቀው እንዲወጡ ወሰነ። የአዲስ አበባ መያዝ አይቀሬ ነበርና የንጉሰ ነገስቱ መቀመጫን መቀየር ያስፈልግ ነበር፤ እናም የት ይሁን? በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ቢመጡም የብላቴን ጌታ ሎሬንዞ ታዕዛዝን ያህል ግን ሚዛን የሚደፉ አልነበሩም። ሎሬንዞ ታዕዛዝ የመንግስቱ መቀመጫ እንዲሆን ብለው ያጭዋት ጎሬ ከተማ ነበረች። የሎሬንዞ ታዕዛዝ ተቀባይነት በማግኘቱ ቀዳማዊ አጼ ሀይለስላሴ የመንግስታቸውን መቀመጫ ወደ ጎሬ አንዲዞር፣ የዘውዳዊውን መንግስት እንዲጠብቁ ደግሞ ልዑል ራስ እምሩ ኃይለስላሴን ሰይመው አዲስ አበበን ለቀው በባቡር ወደ ጅቡቲ፣ ከዚያም በመርከብ ተሳፍረው ወደ አውሮፓ ተጓዙ። ንጉሰ ነገስቱን አጅበው ከሄዱት የዘመኑ ሹማምንት መካከል አንዱ ደግሞ ሎሬንዞ ታዕዛዝ አንዱ ነበሩ።
የፋሺስት ወረራ የብላቴን ጌታ ሎሬንዞን ህይወት በብዙ መልኩ የቀየረ ነበር። ከወረራው በፊት የመጀመሪያዋ ሴት ኢትዮጵያዊት የፓርላማ አባል፣ ገጣሚና ጸሀፌ ተውኔት ከሆኑት ከወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ጋር ጋብቻ መስርተው ይኖሩ ነበር። የፋሺስትን ወረራ ተከትሎ ግን ብላታ ሎሬንዞ ፋሺስትን በዲፕሎማሲው ግንባር ለመውጋት ወሰኑ፤ ባለቤታቸው ስንዱ ግን ፋሺስትን እዚሁ ኢትዮጵያ ሆነው መፋለምን ምርጫቸው በማድረጋቸው መለያየታቸው ግድ ነበር፤ በዚህ ሁኔታ የፋሺስት ወረራ ለትዳራቸው መፍረስ ምክንያት ሆነ።
ፋሺስት በሚያዚያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መናገሻ የነበረችውን አዲስ አበባ ከተማን በቁጥጥሩ ስር አደረገ። እንግዲህ የፋሺስትን ኃይል በጦር ማሸነፍ አልሆነምና ሌላ የትግል ስልት መዘየድ የግድ ሆነ፤ የነበረው ብቸኛ አማራጭ ደግሞ ፋሺስትን በዲፕሎማሲው ግንባር መግጠም ነበር። በኢኮኖሚና ወታደራዊ መስክ እጅጉን ኋላ ቀር የነበረችው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበረችውን ሃያሏን ኢጣሊያን በዲፕሎማሲው ግንባር ለመፋለም ስትነሳ ‘በየትኛው አቅሟ’ ብለው የተሳለቁ ጥቂት አልነበሩም። በእርግጥ በዲፕሎማሲው ግንባር ቢያንስ ተፎካካሪ ለመሆን ስለ ዓለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ወታደራዊ፣ የፍትህ ስርዓት በቂ ዕውቀት ያለው፣ በንግግሩ ሰዎችን በማሳመን ብቃት የተካነ፣ እንዲሁም በዓለማቀፍ መድረክ ዋነኛ የዲፕሎማሲ ቋንቋዎች የሆኑትን እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ አቀላጥፎ መናገር የሚችል ጠንካራ ዲፕሎማት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያም እንዲህ ያለውን ዲፕሎማት ማግኘት ፈተና ሆኖባት ስታማትር መፍትሄ የሆናት ብላቴን ጌታ ሎሬንዞ ታዕዛዝ ነበሩ።
ፋሺስትን በዲፕሎማሲው ግንባር ለመግጠም የተነሳውን የኢት ዮጵያን የዲፕሎማሲ ኃይል ከፊት ሆነውም በብስለት መርተዋል። ከፍ ያለ ትዕግስት፣ ጽናትና ቁርጠነኝነት የሚጠይቀውን ይህን አገራዊ አደራ በስኬት በመወጣታቸው ሎሬንዞ ታዕዛዝ ታላቅ የኢትዮጵያ ባለውለታ ናቸው። የእሳቸው የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ውጊያ ጅማሮውን ያደረገው ንጉሱ አውሮፓ እንደረገጡ ነበር። የኢትዮጵያን ነጻነት ለማስመለስ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ የትግል ስልት መከተል የሚል አቋም የነበራቸው ንጉሱ፣ ይህ አቋማቸው ከአንዳንድ ስመ-ጥር አርበኞችና ባለስልጣናቶቻቸው ተቃውሞ አስነስቶባቸው ነበር፤ በአገር ቤት ደግሞ አርበኞች በየጎራው ፋሺስትን ለመዋጋት በስፋት መንቀሳቀሳቸው አልቀረም። ንጉሱ የአርበኞች ትግል ዓላማቸውን ለማሳካት እንቅፋት እንደሚሆንባቸው ስጋት ገብቷቸው ነበርና የሰላም አማራጮችን አሟጦ መጠቀም እንደሚያሻ ከእርሳቸው በተቃራኒ የቆሙትን ማሳመን ነበረባቸው፤ ይህን ወሳኝ ተልዕኮ ያስፈጽሙላቸው ዘንድም ምርጫቸው የነበሩት ሎሬንዞ ናቸው። ብላቴን ጌታም አላሳፈሯቸውም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተልዕኳቸውን በስኬት አጠናቀዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ግንባር ያደረገችውን የመጀመሪያ ፍልሚያ በድል አጠናቃ ከውጭ ኃይሎች ጋር፣ በተለይም ከዋነኛዋ ጠላቷ ኢጣሊያ ጋር ለምታደርገው ፍልሚያ መዘጋጀት ጀመረች። በዚህ ሁሉ ታዲያ የፊት አውራሪነት ሚና የነበራቸው እኚህ ታላቅ የአገር ባለውለታ በዓለም መንግስታት ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው በሰሩባቸው ዓመታት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር ሲሉ በጽኑ ደክመዋል። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የዓለም መሪዎች በታደሙበት የጄኔቫው ስብሰባ ላይ ያሰሙትንና ብዙዎች ታሪካዊ ብለው የሚጠሩትን ንግግር አቀናብረው ያዘጋጁት ሎሬንዞ ነበሩ። በዚህም ፋሺስት በኢትዮጵያዊያን ላይ ያደርስ የነበረውን ግፍ ለመላው ዓለም በመግለጥ የዲፕሎማሲ ጫና ስር እንዲወድቅ ታላቅ ተጋድሎ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ተደጋጋሚ ጥረቶችን ብታደርግም የሚፈለገውን ውጤት ግን ማግኘት አልተቻለም ነበር። ንጉሱ ለነጻነት መረጋገጥ ሰላማዊ መፍትሄ ብለው የጀመሩት መንገድ አዋጭ እንዳልሆነና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍትህን ማግኘት እንደማይገኝ በተረዱበት ወቅት ስትራቴጂያቸውን በመቀየር የሽምቅ ውጊያ አማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነ ወሰኑ። ይሁንና በመላ ኢትዮጵያ የተፋፋመው የሽምቅ ውጊያ የተበታተነ፣ በተጨማሪም በተለያዩ የአርበኞች ስብስቦች መካከል አለመግባባት ስለነበር ፋሺስትን በሽምቅ ውጊያ ለማሸነፍ በጣም ከባድ ነበር፤ ንጉሰ ነገስቱም እነዚያን የተለያዩ ኃይሎች ማስተባበርና ማደራጀት ቀዳሚ አጀንዳ አደረጉ። ይህን እንዲያስፈጽሙ ደግሞ በስውር ወደ ኢትዮጵያ የተላኩት ብላታ ሎሬንዞ ታዕዛዝ ነበሩ።
ስለዚሁ ሁኔታ ክርስቶፈር ሳይክስ የተባለ እንግሊዛዊ ‹‹Orde Wingate፡ A Biography›› በተሰኘ መጽሀፉ እንዳተተው፤ ሎሬንዞ ታዕዛዝ ሮበርት ሞኔር በተባለ አንድ የፈረንሳይ የደህንነት መኮንን እገዛ አቅጣጫ ጠቃሚ መሳሪያ አጠቃቀም ስልጠና ወስደው ነበርና ወደተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደ ልባቸው ለመዘዋወር ችለዋል። በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ስማቸውን ቀይረው ወልደሚካኤል እና ቶምፕሰን በሚባሉ ስሞች ይጠሩ ነበር። መላ ኢትዮጵያን ሲያስሱም የፋሺስት ወጥመድ ውስጥ እንዳይገቡ ገጽታቸውን የሚለዋውጥ አለባበስ መከተል ነበረባቸው። በኢትዮጵያውያን አርበኞች ጠንካራ ይዞታዎች አካባቢ ሲዘዋወሩ የወታደራዊ ልብሶችን ይለብሱ ነበር፤ አንዳንዴም የአርሶአደር የአለባበስ ዘዬ ተከትለው፣ መነኩሴ መስለው ከጠላት ያመለጡባቸው አጋጣሚዎችም በርካታ ናቸው። ከሶስት ወራት በኋላም የተሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት ፈጽመው ወደ እንግሊዝ ተመልሰው ለንጉሰ ነገስቱ ሪፖርት አቀረቡ።
ሎሬንዞ ታዕዛዝ በዚህ ሪፖርታቸው ፋሺስት መላው ኢትዮጵያን ተቆጣጥሬአለሁ ቢልም እውነታው ግን እጅግ ብዙውን የኢትዮጵያ መሬት መቆጣጠር እንዳልቻለ፣ ፋሺስት እንደሚለው ሳይሆን ፈጽሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ተቀባይነት እንደሌለው፣ ይልቁንም ህዝቡ ለነጻነቱ ሲል የትኛውንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ወደኋላ እንደማይል የሚያረጋግጥ የአርበኞቹን መሪዎች ፊርማ ያረፈበት ሰነድ ጋር አያይዘው ለዓለም መንግስታት አቅርበዋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ዕውነት እንዲገነዘብና ፋሺስትን እንዲያወግዝም ጠይቀዋል። ይህን ተከትሎም በርካታ አገራት ቀድሞ የነበራቸውን አቋም ቀይረው በኢትየጵያ የፋሺስት አገዛዝን እውቅና ነፈጉ፤ ከነዚህ አገራት መካከል አሜሪካ፣ ሶቪየትህብረት፣ ስዊድን፣ ሜክሲኮ ይጠቀሳሉ።
የተለያዩ የአርበኞች ስብስቦች ትብብር መጀመራቸው እንዲሁም የዓለማቀፉ ማህበረሰብ የፋሺስትን ፕሮፓጋንዳ ችላ ማለት መጀመሩ ለኢትዮጵያ የነጻነት አንቅስቃሴ ተስፋን የፈነጠቀ ቢሆንም በ1932 ዓ.ም ገደማ ግን ይህን ተስፋ የሚያጨልምና ለፋሺስት ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያለው አንድ ሁነት ተከሰተ። ይህም የፋሺስት አገዛዝ ካበቃ በኋላ ስለሚመሰረተው መንግስት ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦች መንጸባረቅ መጀመሩ ነበር። ለንጉሱና ዘውዳቸው ታማኝነታቸውን ያሳዩ አርበኞች የመኖራቸውን ያህል 900 ገደማ የሚሆኑ የአርበኞች መሪዎች በጎንደር ተሰባስበው በሚመሰረተው መንግስት ንጉሰ ነገስቱ የመሪነት ሚና እንደማይኖራቸው፣ ከዚህ ይልቅ ህዝባዊ መንግስት እንዲቋቋም የሚል አቋም ያዙ። ይህ እንቅስቃሴ ንጉሱ የዓለም አገራትን በተለይም የታላቋ ብሪታንያን ድጋፍ እንዲያጡ የሚያደርግ፣ በዚህም እየተፋጠነ በነበረው የነጻነት እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ጋሬጣ የሆነ ነበርና እዚህን ሁለት ሃሳቦች አስታርቆ ወደ አንድ የማምጣቱ ስራ ፋታ የማይሰጥ ሆኖ ተገኘ። ንጉሱ ታዲያ ለዚህ ውስብስብ ጉዳይ መፍትሄ እንዲያፈላልጉ አደራ ያሉዋቸው ሎሬንዞን ነበር።
ሎሬንዞ ታዕዛዝም ውለው ሳያድሩ ነበር ይህን ግዳጅ ለመወጣት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ምስጢራዊ ጉዞ ያደረጉት። በኢትዮጵያ ባደረጉት አጭር ቆይታም የጸረ- ፋሺስት ንቅናቄው ዋነኛ መሪዎች የሆኑ 10 ሺ ገደማ የሚሆኑ ስመ-ጥር የጦር አበጋዞችንና አርበኞች ለንጉሰ ነገስቱ ያላቸውን ታማኝነት የሚያረጋግጥ ፊርማ በማሰባሰብ ወደ እንግሊዝ ተመለሱ። በዚህ መነሻነትም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስታቸው መልሶ እንዲቆም በማድረግ የላቀ ሚና የነበራትን ብሪታንያን ድጋፍ መልሰው ለማግኘት ቻሉ። የፋሺስቱ መሪ ቢኒቶ ሞሶሎኒ በእንግሊዝና ፈረንሳይ ላይ ጦርነት ማወጁን ተከትሎም ኢትዮጵያውያን አርበኞች በእንግሊዝ ወታደራዊ ድጋፍ እየታገዙ፣ በ1933 ዓ.ም ለአምስት ዓመታት ተነጥቆ የቆየውን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስመለሱ። ብላቴን ጌታ ሎሬንዞ ታዕዛዝም እንዲያ የደከሙለት የንጉሱ ዘውዳዊ ስርዓት እንደገና ቆመ።
ኢትዮጵያ ዳግም ነጻነቷን ብትቀዳጅም እንግሊዛውያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሙሉ ለሙሉ ከማክበር ይልቅ የሞግዚት አስተዳደር ለመመስረት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴም ብስለት በተመላበት መልኩ ይህን የብሪታንያን አጀንዳ ለማክሸፍ ባደረገት እንቅስቃሴ ሁሉ ከጎናቸው የነበሩት ሎሬንዞ ታዕዛዝ ነበሩ። ይህም ተሳክቶ እንግሊዞች ጓዛቸውን ጠቅልለው እንዲወጡ ተደረገ። ሎሬንዞ መልሶ በቆመው ዘውዳዊ መንግስት በቅድሚያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት (1933-1935)፣ ቀጥሎም የፖስታ፣ ቴሌፎን እና ቴሌግራም ሚኒስትር (1935-1936)፣ በሶቪየት ህብረት የአትዮጵያ ቆንስላ ሚኒስትር (1936-1938) በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በተጨማሪም ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለማቀፍ ስብሰባዎች ወክለው ተሳትፈዋል። ሎሬንዞ ታዕዛዝ እ.ኤ.አ በግንቦት ወር 1946 ዓ.ም በፓሪስ የሰላም ኮንፍራንስ ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው የልዑክ ቡድን አባል ነበሩ።
ከፓሪስ ኮንፍራንስ መልስ ብላቴን ጌታ ሎሬንዞ የጤና መታወክ ገጥሟቸው በተደጋጋሚ ሆስፒታሎችን መጎብኘት አበዙ፤ የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ ተብሎም ወደ ስዊድን አገር ተልከው በስቶክሆልም ከተማ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ እ.ኤ.አ በሰኔ 1946 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። እኛም በዛሬው ‹‹ባለውለታዎቻችን›› አምዳችን ባለዘርፈ ብዙ ዕውቀት ባለቤቱን፤ በሳል ለኢትዮጵያ ዋጋ የከፈሉትን ብላቴን ጌታ ሎሬንዞ ታዕዛዝን በእንዲህ መልኩ ልንዘክራቸው ወደድን። የሳምንት ሰው ይበለን!።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2015