የያዝነውን ሳምንት የምንቋጨው በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት በሚከበረው የትንሳዔ በዓል ነው። በሰሞነ በዓል ብዙዎች እንደ አየር ከሚተነፍሱት ፖለቲካ ዕረፍት ወስደው ትኩረታቸውን የገበያ ዋጋ ላይ ያደርጋሉ። ዶሮ ፣ በግ ፣ በሬ፣ ቂቤ ፣ ዕንቁላል፣ ሽንኩርትና ሌሎች ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ስንት ገባ ብሎ የማይጠይቅ የለም። ታዲያ በምርት እጥረትና በዋጋ ግሽበት አሊያም ነጋዴዎች በዓልን አስታከው በሚያደርጉት ጭማሪ ምክንያት የሚከሰት የዋጋ ንረት አዋራ ማስነሳቱ አይቀርም።
በበዓል ወቅት የሚደረግ የአምስት ሳንቲም ጭማሪ እንኳን “ጉድ” ያስብላልና። ዶሮ ይዞ የሚጓዝ፤ በግና ፍየል የሚጎትትና በሬ የሚነዳ ሰውን ያገኘው ሁሉ በየመንገዱ እያስቆመ ዶሮውን ቀበል አድርጎ በእጁ እየመዘነ፤ የበግና ፍየል መስባትን በእጁ እያረጋገጠ ሰንት ገዛኸው? ገበያው እንዴት ነው እያለ ይጠይቀዋል። ገዢውም ለጠየቀው ሁሉ ሳይታክት መልስ ይሰጣል። ሰፈርተኛ መንገድ ሲገናኝ ሰላምታ ከተለዋወጠ በኋላ እንደወትሮ መንገዱን አይቀጥልም የበዓል ሰሞን ገበያ አጀንዳ ይሆናል። በበዓል ሰሞን የጎረቤታሞች የቡና ርዕስ የገበያ ዋጋ ነው። ለበዓል ወቅት ገበያ ከፍ ያለ ትኩረት መስጠት በዘመነ ማህበራዊ ሚዲያ (ፌስቡክ) ቀጥሏል።
ለትንሳዔ በዓል የቀረበ የአንድ በሬ ዋጋ ደግሞ የገበያ ወሬ ማጣፈጫ ሆኗል። በሬው ለሽያጭ የቀረበው በሞረትና ጅሩ ወረዳ ገርባ ቀበሌ ሴፋጥራ ጎጥ በተባለ ቦታ ነው። አንድ ግለሰብ ያደለቡት ይህ በሬ ለሽያጭ የቀረበው በዘጠና ስምንት ሺህ ብር ነው። በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን እውቅና የተሰጠው የጅሩ ማኛ በሬ እየተባለ የተቆለጳጰሰው በሬው ወትሮም ቢሆን ትንሽ ለሚበቃው የበዓል ሰሞን የገበያ ዋጋ ወግ የመጠኑን ያህል ትልቅ ሲሳይ ሆኗል። በዋነኛው ማህበራዊ ድረ ገጽ (ፌስ ቡክ) ስለዚህ በሬ ብዙ ተብሏል። እስኪ ዘጠና ስምንት ሺ ብር ስላወጣው በሬ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ፈገግ ያደረጉኝን ላካፍላችሁ።
አንድ አስተያየት ሰጪ የበሬው ዋጋ 98 ሺ ብር መግባቱን ከማምን በሬ ወለደን ማመን ይቀላል ብሏል። ሌላኛው ደግሞ ማንችስተር ሲቲ አሊያም ሪያል ማድሪድ መሆን አለባቸው የገዙት ሲል ተሳልቋል። አንድ አስተያየት ሰጪ በበኩሉ “በቁጭት ምን አለ ሁለት ሺ ብር ጨምረው አንድ መቶ ሺህ ቢያደርጉት”ሲል አስተያየቱን አስፍሯል። በዜናው የምሩን የተቆጣ የሚመስል አስተያየት ሰጪ ደግሞ “ሁላችሁም ልታስቡበት ይገባል። ይሄ እንደ ቀልድ የሚታይ ነገር አይደለም።
ልታዝኑና ልትደነግጡ ይገባል። በሬ ሳር በልቶ ይሄን ያህል ሊያወጣ አይገባም። በአጠቃላይ የሰው ልጅ የሚመገባቸው ነገሮች መወደድ የለባቸውም”። የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። በበዓል ሰሞንም ከፖለቲካው ያልተፋታ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ “በሬ 98 ሺ ብር የገዛ ግለሰብ ያለበት አገር ውስጥ ነው ያለነው። «ለውጥማ አለ»። እደግመዋለሁ ዘጠና ስምንት ሺ ብር” ሲል የበሬውን ዋጋ ከለውጡ ጋር ለማያያዝ ሞክሯል።
ሁለት ግለሰቦች ደግሞ አስተያየታቸውን ለየት ባለ መልክ አቅርበዋል። የመጀመሪያው በሬው አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሟል እንዴ ሲል ጠይቋል። ሁለተኛው ጠያቂ ደግሞ “በሬው በበርገርና ፒዛ ሳያድግ አይቀርም” ሲል ጥርጣሬውን አጋርቷል። የበዓል ሰሞን ገበያ ትርምስ ይበዛዋል። በበዓል ሰሞን ጎዳናው ሁሉ መገበያያ ይሆናል። እግረኞች እግር መጣያ እስኪያጡ ድረስ መንገዱ በሸቀጦች ይሞላል። ዶሮ፣ ዕንቁላልና ሽንኩርት በመኪና ላይ ይቸበቸባሉ። ለበዓል አዲስ ልብስ የመልበስ፤ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን የመቀየርና ቤትን የማስዋብ ልማድ ስላለ የሸመታው አድማስ ይሰፋል። ትልልቅ የገበያ ማዕከላት (ሞሎች) በቀለማት አሸብርቀው ለሙዚቃ አስጨፋሪዎች በመቅጠር በየትላልቅ የድምፅ ማጉያዎች (ስፒከሮች) በሚለቋቸው ሙዚቃዎች የበዓሉን ድባብ ያደምቁታል።
አንዳንዶቹም በትላልቅ አሻንጉሊቶች ትርዒት ያቀርባሉ። ኤግዚቢሽንና ባዛሮች በየቦታው ተከፍተው ሸማቹ ይሰለፋል፤ የሙዚቃ ድግሶች (ኮንሰርት) ይጧጧፋል። በተለይ እንደ ትንሳኤ ባሉ በዓላት ተዘግተው የከረሙ ሥጋ ቤቶች እድሳት አደርገው ወደ ሥራ በመግባት የደንበኞቻቸውን አምሮት ይቆርጣሉ። ሙዚቀኞች በዓሉን አስታከው የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን (አልበሞቻቸውን) ለገበያ ያቀርባሉ።
ለዘንድሮ ትንሳኤ በዓል ሳሚ ዳን፣ ጃኪ ጎሲና አቤል ሙሉጌታ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን (አልበማቸውን) ለሽያጭ አቅርበዋል። የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ የሌባ ሲሳይ ሆኖ ኪሱን ታጥቦ በዓሉን ተኮራምቶ የሚያሳልፍ ምስኪንም አይጠፋም። ምን ይሄ ብቻ የገዙት ዶሮ፣ በግና በሬ አምልጧቸው በእግራቸው ሲኳትኑ የሚውሉም አሉ። እንዲህ ካለው ዱብዳስ ይሰውራችሁ! የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ ! መልካም በዓል ይሁንላችሁ!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18/2011
የትናየት ፈሩ