ሁለተኛውን ዓለም አቀፍ <<ቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም>> ለመሳተፍ ቻይና የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት የቻይናዋን ሀንዡ ከተማ መጎብኘታቸውን ኤፍ.ቢ.ሲ ዘግቧል፡፡ ብዙ የቴክኖሎጂ ተቋማትን በውስጧ በመያዝ በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከልነቷ የምትታወቀዋን የሀንዡን ከተማ ትናንት በጎበኙበት ወቅት፤ የአሊባባ ኩባንያ ዋና መስሪያ ቤትን ጨምሮ ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ጎብኝተዋል፡፡
አሊባባ ኩባንያ ሊቀመንበር ጃክ ማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የአሊባባ ኩባንያን ባስጎበኟቸው ወቅት ስለ ኩባንያው ማብራሪያ የሰጧቸው ሲሆን፣ ኩባንያው በዓለም ዙሪያ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለ40 ሚሊየን ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ አገራት በሩዋንዳ ብቻ ሥራውን እየከወነ የሚገኘው ኩባንያው ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገራትም ሥራውን ለማስፋፋት እቅድ እንዳለው አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጉብኝቱ ወቅት፣ አሊባባ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት እንዲያደረግ ግብዣ አቅርበዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሥራ ፈላጊ ወጣት መኖሩን ጠቁመው፤ አሊባባ ኩባንያ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ቢያደርግ ውጤታማ እንደሚሆን ተናግረዋል። አሊባባ ኩባንያ ሊቀመንበር ጃክ ማ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገራትም በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውሰው፤ በቀጣይ ዓመት ህዳር ወር ላይ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሀንዡ ከተማ ቆይታቸው ከዤጂያንግ ግዛት አመራሮች ጋርም በመወያየት፤ በግዛቷ ውስጥ የሚገኙ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታዎች ላይ መወያየታቸው ተዘግቧል። ሀንዡ በቻይናዋ ዤጂያንግ ግዛት ውስጥ የምትገኝ የፖለቲካ፣ የኦኮኖሚ እና የባህል ማዕከል የሆነች ከተማ ነች።
ከተማዋ ብዙ የቴክኖሎጂ ተቋማትን በውስጧ የያዘች በመሆኑ በአይ.ሲ.ቲ ከተማነቷም የምትታወቅ መሆኗም ተጠቁሟል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከጉባዔው በፊት ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዥንፒንግ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬኪያንግን ጨምሮ ከሌሎች የቻይና ኩባንያዎች አመራሮች ጋር የተለያዩ ውይይቶችን በማድረግ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል። ዶክተር አብይ ባካሄዱት የሁለትዮሽ ውይይት እ.አ.አ በ2018 ኢትዮጵያ ከቻይና ያለወለድ የተበደረችው ገንዘብ መሰረዙን አፍሪካ ኒውስ በድረገፁ ማስነበቡ ይታወሳል፡፡ አፍረካ ኒውስ እ.አ.አ ከ2000 ጀምሮ ኢትዮጵያ ከቻይና 12 ቢሊየን ዶላር ተበድራለች ተብሎ እንደሚገመት ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18/2011
ምህረት ሞገስ