የዚህ ሳምንት ‹‹ሳምንቱ በታሪክ›› በአንድ ቀን ሁለት ክስተቶች ላይ ያተኩራል፡፡ መጋቢት 24 ላይ፡፡ ክስተቶቹ የሰባት ዓመታት ልዩነት አላቸው፡፡
የመጀመሪያው ክስተት ኢትዮጵያውያን በአንድ ሳምባ የተነፈሱበት የዓባይ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት 12ኛ ዓመት ነው፡፡ ዕለቱ ቅዳሜ ነበር፤ እነሆ ዘንድሮ ደግሞ 12ኛ ዓመቱ መጋቢት 24 በዛሬዋ ቀን ዕለተ እሁድ ላይ ውሏል፡፡ ለመሆኑ ከዛሬ 12 ዓመታት በፊት የመሠረት ድንጋዩ ሲጣል ምን ተባለ የሚለውን ክስተት እንዲህ እናስታውሰው!
ዕለተ ቅዳሜ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ረፋድ፤ በያኔው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለመላው ኢትዮጵያውያን አንድ ታላቅ ብሥራት ተበሰረ። ሀገራዊ አቅምን የሚያሳይ፣ የተፈጥሮ ሀብት ፍትሐዊ ክፍፍልን የሚያስተምር፣ ሰላም እና መተባበርን የሚመሰክር፣ ሕዝባዊ ጥቅምን የማሳየት ዓላማ ያለው፣ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የጥረት አሻራ የሚታተምበት፣ አገር በአንድ ልብ የሚያስብበትና በአንድ ሳምባ የሚተነፍስበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሊገነባ የመሠረት ድንጋይ ተጣለ።
ይህ በኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የሆነ የህዳሴ ግድብ እንደሚገነባ ለኢትዮጵያውያን ተበሰረ። ይህን ለዘመናት የማይደፈር መስሎ የኖረ ዓባይ የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ደፈሩት። በትናንትናዋ ዕለት ቅዳሜ፣ በዛሬዋ ቀን 24፣ በዛሬዋ ወር መጋቢት ግን በያኔው ዓመተ ምሕረት 2003 ይህ ብሥራት ተነገረ።
የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመሠረት ድንጋዩን ሲያስቀምጡም እንዲህ አሉ። « … የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ ፊርማ ያረፈበት ግድብ በመሆኑ የህዳሴ ጉዟችን መሐንዲሶች እኛው፣ ግንበኞቹና ሠራተኞቹ እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮችና አስተባባሪዎች እኛው፣ በአጠቃላይ የህዳሴ ጉዟችን ባለቤቶች እኛው መሆናችንን የሚያሳይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታችን ነው።» ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኋላ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላቡን ፊርማ በማሳረፍ፣ መሐንዲስ፣ ግንበኛና ሠራተኛ፣ የፋይናንስ ባለቤት መሆኑን አረጋገጠ።
የመንግሥት ሠራተኛው ከደመወዙ፣ ነጋዴው ከወረቱ፣ ገበሬው ከምርቱ፣ ተማሪው ከደብተርና እስኪሪቢቶው ወጪውን በመቀነስ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የህዳሴው ግድብ ባለቤት መሆኑን አስመስከረ። በዓባይ ጉዳይ ላይ ለዘመናት ሲንከባለሉ የኖሩ ጥያቄዎች ምላሽ አገኙ። በቅኝ አገዛዝ ዘመን ዓባይ በኢፍትሐዊ ቦይ እንዲፈስ የተወሰነባቸው ውሳኔዎች በዚያች ዕለት በዚያች ቀን ዋጋ እንደሌላቸው ተረጋገጠ። ስሙ ብቻ የተረፋቸው የናይል ተፋሰስ አገሮች አንድም በኢኮኖሚ አቅም ማጣት አንድም በአውሮፓውያን ኢፍትሐዊ ውሳኔ ከደጃቸው ለሚፈሰው ዓባይ ለበርካታ ዘመናት የበይ ተመልካች ሆነው ኖረዋል። ዳሩ ግን የቅኝ አገዛዝ ዘመን አክትሞ፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ዘመናቸው አለፈና ዓባይ በፍትሐዊ ቦይ እንዲፈስ ተወሰነ።
ዓባይ በወኔ እና በቆራጥነት እንደሚገነባ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ በቆራጥ ወኔ ተናገሩ። ያኔ ባረጀ እና ባፈጀ አገዛዝ የነበረው አመለካከት ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ወኔያቸውን አሳዩ። እስኪ በፓርላማው ውስጥ ከተናገሩት ንግግር ደግሞ ይችን እንውሰድ።
«አንዱ የግብፅ ስትራቴጂ ያው ትልቅ ወታደር አስቀምጦ ማስፈራራት ነው፤ ይህን በተመለከተ ልንከተለው የሚገባ ፖሊሲ ቢኖር አለመፍራት ነው።» ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኢትዮጵያውያን እውን ሆነ። ግብፅ በየጊዜው የምታነሳው እንጉርጉሮ ግድቡን ለሰከንድም እንደማያስቆመው ዳግም ተረጋገጠ። ኢትዮጵያ ሰላማዊ ውይይትን ለዓለም አሳየችበት።
ከዚች ዕለት ጀምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የኔ እያለ የሚጠራው ሆነ። ዓባይ የጋራ መግባቢያ፣ የጋራ ማሰቢያ፣ የጋራ ሀብት ሆነ። ኢትዮጵያ በራሷ አቅም አትገነባውም የሚለው የውስጥ ለውስጥ ሹክሹክታ አንድምታ ሳያገኝ ቀረ። በዓባይ ጉዳይ የመጣ ነገር ሁሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ በመሆኑ በጋራ ማዳመጥ ሆነ።
የመገናኛ ብዙኃን ስለ ግድቡ የሚያወሩት ወሬ በሁሉም ሰው ልብ በአንዴ መድረስ ቻለ። ምክንያቱም ስለ ዓባይ ምን ተባለ የሚለው ነገር የሁሉም ሰው ጉጉት ስለሆነ። ይህ ኢትዮጵያንን በአንድ ቋንቋ ያነጋገረ ዓባይ በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ የደስታ ምንጭ በመሆን ኩራትን ፈጠረ። ለበርካታ ኢትዮጵያውያንም የሥራ ብቻ ሳይሆን የጥበብ ምንጭ ሆነ። ከተማሪ እስከ ተመራማሪ በዓባይ ላይ ቅኔ በመቀኘት መጠበብ ጀመሩ። ከትምህርት ቤት ሚኒሚዲያ እስከ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በዓባይ ላይ ምን እንጠበብ በሚል ውስጣቸውን ጠየቁ። በየመድረኮች ዓባይን የሚያመሰግኑ ስንኞች፣ ዓባይን የሚያስውቡ ዜማዎች ተፈጠሩ። ይህም ለበርካታ ወጣቶች እና ተማሪዎች የጥበብ የፈጠራ ምንጭ ሆነ።
ታላቁን የዓባይ ግድብ ከደለል ለመከላከል ሲባል ለበርካታ አርሶ አደሮች ሌላ አጋጣሚ ፈጠረ። ይህም አርሶ አደሮቹ የሚሰሩት እርከን ዓባይን ብቻ ሳይሆን የአርሶ አደሮችን የእርሻ ማሳም አፈሩን በማስቀረት በውሃ እንዳይሸረሸር እስከ ማድረግ ደረሰ።
የመገደቡ ብሥራት የተነገረው ዓባይ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ሌላ የይቻላል መንፈስን እና ወኔን ፈጠረ። እንዲያ በአስፈሪነቱ ይመለክበት የነበረው ዓባይ ለካ እንዲህ በሰው ልጅ ቁጥጥር ሥር መዋል ይችላል? የሚል የይቻላል በራስ መተማመንን ፈጠረ። በቃ! የሰው ልጅ የቱንም ነገር መሥራት ይችላል አሰኘ። ግድቡ ከተጀመረ በኋላ ዓባይ የመታየት እና የመጎብኘት ዕድሉ እየጨመረ፤ በስም ብቻ ያውቁት የነበሩ በርካታ ከተሜዎች ዓባይን በአካል ሄዶ የማየት ጉጉት አደረባቸው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የግድቡ ሥራ ከግማሽ በላይ ተከናውኖ ሲታይ እንኳን የግድቡ ባለቤት የሆነውን ኢትዮጵያዊ ይቅርና ይህን ከዓለማችን ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የተባለለትን ግድብ ማንም የማየት ጉጉት ያድርብዎታል።
ያኔ ሲጀመር 5250 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የታሰበው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አቅሙን አሳድጎ ከፍ አድርጓል። ይህ መላው ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ለመላው ዓለም ሰላም እና አንድነትን እየመሰከረ ያለ ታላቅ ግድብ ሲጠናቀቅ የዓለምን ቀልብ በመሳብ ኢትዮጵያ የዓለም የሰላም ተምሳሌት መሆኗን በተግባር ያረጋግጣል። እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን የሚለው መሪ ቃል ይፈፀምና ሌላ እንድንጀምር ማሳያ ይሆናል።
በቅርቡ ደግሞ ኃይል የመመንጨት ብሥራት ጀምሯል። በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደተነገረው፤ ይህ የኢትዮጵያውያን አሻራ የሆነው ግድብ የትውልድ ቅብብሎሽ ነው። ያሰቡትንም(ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ)፣ የጀመሩትንም(አቶ መለስ ዜናዊ)፣ እያስፈጸሙት ያሉትንም (ዶክተር ዐቢይ አሕመድ) እናመሰግናለን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2015