የመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት የመንገዶች የጥገናና ደኅንነቶች ወጪዎችን ለመሸፈን የሚያስችለውን ሥራ በትክክል ለማሳካት በጀቱን ከ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ሊያሳድግ መሆኑን አስታወቀ::
የኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ረሺድ መሀመድ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ እስከ 2010 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ የመንገድ ፈንድ ገቢ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፤ ይህንን በእጥፍ በመጨመር በአሁኑ ወቅት ወደ 2 ነጥብ5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል::ይህ በቂ ባለመሆኑም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አምስት ቢሊዮን ብር አቅም ለመፍጠር ታስቧል::ለዚህም ውይይቶች ተደርገው ውሣኔ እየተጠበቀ ሲሆን፤ በመንግሥት በኩል ተስፋ ሰጭ ግብረ መልስ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ዳይሬክተሩ፤ በአገሪቱ ባላፉት ሁለት አስርት ዓመታት በመንገድ ሴክተር ላይ በማንኛውም ጊዜ ተሠርቶ የማይታወቅ ለሌሎች አገሮችም አርአያ የሚሆን ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀው፤ ነገር ግን በጥገና ላይና በመንገድ ሀብት እንክብካቤ በኩል መሠራት የሚገባውን ያህል እንዳልተሠራ ጠቅሰዋል::የኢትዮጵያን የመንገድ ሀብት 200 ቢሊዮን ብር ግምት አለው የሚል ከተለያዩ ጥናቶች ማየት መቻሉን፤ በዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮ አንድ አገር በመንገድ ጥገናና በመንገድ ሀብት እንክብካቤ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ሊባል የሚችለው ቢያንስ የመንገድ ሀብቱን ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በየዓመቱ ለመንገድ ጥገና በጀት መመደብ ስትችል መሆኑን፤ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የመንገድ ፈንድ በአነስተኛው አምስት ቢሊዮን ብር ከፍ ሲል ደግሞ ሰባት ቢሊዮን ብር ማቅረብ እንዳለበት አስታውቀዋል::
‹‹አሁን ባለንበት ደረጃ ላይ እያቀረብን ያለነው 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ነው::ይህ ማለት የፍላጎቱን 50 በመቶ ብቻ የሸፈነ ነው::ይህ ደግሞ 50 በመቶ መሸፈን የሚገባቸውና መጠገን ሲገባቸው ሳይጠገኑ የሚቀሩ መንገዶች እንዲኖሩ ስለሚያደርግ ለባሰ ጉዳት የሚዳረጉበትና አገሪቷን ለሌላ ተጨማሪ ወጪ የሚያጋልጥ ይሆናል::ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ በተጨባጭ መረጃ ላይ በመመስረት የኢትዮጵያ መንገዶች በየዓመቱ ምን ያህል ወጪ ያስፈልጋቸዋል የሚለውን የሚያሳይ ጥናቶች ተጠንተው ለመንግሥት ቀርበዋል::በጎ የሆነ ምላሽም እያገኙ ነው›› ብለዋል ዳይሬክተሩ::
ገንዘቡ ቢገኝም ያለውን ገንዘብ ሥራ ላይ የሚያውሉና የተጠናከሩ የመንገድ ኤጀንሲዎች አለመኖራቸው ሌላው ፈተና መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል::የአሠራር፣ የአደረጃጀት፣ የመሣሪያ እጥረት፣ የሰው ኃይል ማነስ፣ በመንገድ ጥገና ላይ ያለው አመለካከት መዛነፍ፣ ከክብደት በላይ የሚጭኑ ተሸከርካሪዎች የሚፈጥሩት ችግር፣ የዲዛይንና ጊዜያቸውን የጨረሱ መንገዶችን ከመጠገንና ደረጃቸውን ከፍ በማድረግ በኩል ከፍተኛ የሆነ የአቅም ክፍተት መኖሩንም ጠቅሰዋል::ገንዘቡን መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ጎን ለጎን የአቅም ግንባታ ሥራዎችን የበለጠ እንዲጠናከሩ ካልተደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገሪቷ 200 ቢሊዮን ብር የሚሆን ሀብት ልታጣ እንደምትችል ጠቁመዋል::ይሁንና በትንሹ አምስት ቢሊዮን ብር እየተመደበ ከተሠራ፤ በ25 ቢሊዮን ብር ብቻ ሀብቱን መጠበቅ ይቻላል::ይህ ውሣኔ ካልተወሰነ ግን ከአምስት ዓመት በኋላ 200 ቢሊዮን ብር እንደገና ይታጣል::
ተቋሙ ከተቋቋመበት ከ1989ዓ.ም ጀምሮ በመንገድ ልማት ፕሮግራም ላይ ቢያንስ ከ15 በመቶ ያላነሰ አስተዋጽኦ በማድረግ ከፍተኛ በጀት አቅርቦ መንገዶች አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የበኩሉን ሚና ተወጥቷል::
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም
አዲሱ ገረመው