አዲስ አበባ:- በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተደረገ የሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር ድጋፍ እየተባዛ የሚገኝው አንዴ ተዘርቶ ለዓመታት ያለዘር ምርት የሚሰጥ የማሽላ ዘር በቅርቡ ለአርሶ አደሩ ሊሰራጭ መሆኑ ተገለፀ።
ተመራማሪው አቶ ታለጌታ ልዑል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ዘሩን የማባዛቱን ሥራ ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተደረገ የሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር ድጋፍ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በግማሽ ካሬ ሜትር ላይ እያከናወነ ይገኛል::በተያዘለት እቅድ መሰረትም በተያዘው ዓመት ዘሩን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ አስር ኩንታል የሚደርስ አራት አይነት የማሽላ ዝርያዎች ተዘጋጅቷል ብለዋል።
አቶ ታለጌታ አክለውም ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ውይይት በማድረግ ዘሩን ለአርሶ አደሩ በቅርቡ ለማሰራጨት እና የአሠራር ሂደቱን ለመወሰን ቀጠሮ መያዙን ገልፀዋል። ነገር ግን እነዚህ ዘሮች ገበሬው ዘንድ ለዓመታት አብረው የነበሩና ተፈጥሯዊ ባህሪያቸውን የያዙ በመሆናቸው በማንኛውም አካል በኩል ዘሮቹ ለአርሶ አደሩ ቢከፋፈል ምንም አይነት የጎንዮሽ ችግሮችን በአርሶአደሩ እና በማሳው ላይ እንደማያስከትሉ ተናግረዋ ‹‹አንዳንዶች ለረጅም ጊዜ ሌላ ዘር ሳይፈራረቅ አንድ አይነት ዘር ማሳው ላይ መቆየቱ የመሬቱን ለምነትና የሰብሉን ምርታማነት ይቀንሳል የሚል ሥጋት ያላቸው አሉ›› የሚሉት አቶ ታለጌታ፤ ዘሩ ከተዘራ በኋላ የመጀመሪያው ትውልድ ምርት ሰጥቶ ቀጣዩ ትውልድ በሚመጣበት ወቅት የመጀመሪያው ትውልድ ሥሩ በስብሶ ለመጭው ትውልድ ተጨማሪ ምግብና ማዳበሪያ ስለሚሆንለት ከመጀመሪያው ትውልድ ምርቱ በጥፍ እንዲጨምር እንደሚያደርግ ተናግረዋል::በመሆኑም ዘሩ የመሬትን ለምነት ጠብቆ በመያዝ ምርትና ምርታማነትን እንደሚጨምር አመልክተዋል።
‹‹እንዲሁም ማሽላው አፈሩ በውሃና በነፋስ እንዳይሸረሸር በማድረግ የመሬቱን ለምነት የሚጠብቅ ነው። የአካባቢውን አየር ንብረት የተስተካከለና የተዋበ ያደርገዋል።›› የሚሉት ተመራማው፤ በተጨማሪም ያለምንም ድካምና ወጪ በትንሽ ውሃ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን እንደሚጨምር አመልክተዋል::አገዳውና ተረፈ ምርቱ በድርቅ ወቅት ለእንስሳት መኖ የሚውል በመሆኑ፤ ዘሩ ለአርሶ አደሩ ስጦታ እንጂ ሥጋት እንደማይሆን በጥናታቸው እንዳረጋገጡ ተመራማሪው ገልፀዋል። የዝርያው የምርምር ውጤት በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የተመዘገበ መሆኑን ማወቅ ተችሏል::
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም
ሶሎሞን በየነ