አዲስ አበባ፡– አዲሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አዋጅ አገር በቀል ድርጅቶች ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ግፊት የማድረግ መብት እንዳላቸው በሕጉ ማካተቱን የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው የተሻሻለውን አዲስ አዋጅና ከአዋጁ ጋር ተያይዘው የመጡ ለውጦችን አስመልክቶ ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን መግላጫ በሰጠበት ወቅት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጅማ ደንበል እንደተናገሩት፤ አዲሱ የኤጀንሲው አዋጅ የተቋቋሙ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ግፊት የማድረግ መብት ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ሕጉ የአገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ ላይ ግፊት የማድረግ ወይም ምርጫን መታዘብና ለመራጮች ትምህርት መስጠት እንደሚችሉ መቀመጡ ከባለፈው የአዋጅ ሕግ እንደሚለይና፤ ዴሞክራሲን ለማስፈን ማሳያ መሆኑን ገልፀው ተፈፃሚነቱ የሚረጋገጠውም ድርጅቶቹ አስቀድሞ ይህንን ሥራ ለመሥራት በደንባቸው ውስጥ ማካተት አለባቸው::ይህም በዋነኝነት የሚገዛውም በምርጫው ሕግ ይሆናል::
የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ግፊት የማድረግ መብቱ ለውጭ ድርጅቶች እንዳልተሠጠ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በልዩ ሁኔታ ምናልባትም በምርጫ አዋጅ ወይም በምርጫ ሕግ ካልሆነ በቀር የውጭ ድርጅቶች ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ግፊት ማድረግ፣ የመራጮች ትምህርት መስጠትና ምርጫ መታዘብ ላይ እንዳይሳተፉ እንደሚከለክል ገልፀዋል::በልዩ ሁኔታ ከተፈቀደ ግን ሊሳተፉ እንደሚችሉና ይህም ተፈፃሚ የሚሆነው ከኤጀንሲው ሥልጣንና ተግባር ውጭ በሆነ መንገድ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም፤ ያለፈው ሕግ ከመብት አኳያ ገዳቢ የነበረ መሆኑን ጠቁመው በገቢና ድርጅቶች ሊሰማሩባቸው በሚችሏቸው የሥራ መስኮች ላይ ገደብ ያደረገ ነበር፤ ሕገ መንግሥታዊና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች የተረጋገጠውን የመደራጀት መብትና ሌሎች ተያያዥ መብቶችን በተገቢው ተግባራዊ ለማድረግ፣ ‹‹በዴሞክራታይዜሽን›› እና ልማት ላይ ድርጅቶች አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር፣ በነፃነት የተደራጀ የነቃ ማህበረሰብ በመፍጠር የመንግሥት አሠራር ግልፅና ተጠያቂነት ያለበት ለማድረግ፣ ድርጅቶች በተጠያቂነትና በግልፅነት ሥራዎችን በመሥራት በሥራው የህዝብን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ቁጥጥር ለማድረግ፣ የበጎ አድራጊነትና የበጎ ፈቃደኝነት ባህል ለማጎልበት ሕጉ እንዲቀየር ምክንያት መሆናቸውን አስታውቀዋል::
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም
አዲሱ ገረመው