የአዲስ አበባ ስታዲየም የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ በድጋሚ ማስተካከያ እንዲደረግበት ግብረመልስ ተሰጠ። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ባለሙያ በእድሳት ላይ የሚገኘውን የአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲሁም የአቃቂ ስታዲየሞችን ጎብኝተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ ሜዳ እንዲሁም አስፈላጊውን መስፈርት የሚያሟሉ ስታዲየሞች አለመኖራቸውን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያከናውኑ ከታገዱ ስቴድየሞች አንዱ አንጋፋው የአዲስ አበባ ስቴድየም መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ከምትገነባቸው ስቴድየሞች ባለፈ የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ተደርጎለት ወደ ውድድር እንዲመለስ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ እድሳቱ በተለያዩ ምክንያቶች በተያዘለት ጊዜ ባይጠናቀቅም የመጫወቻ ሜዳው ግን በአዲስ መልክ የሳር ተከላና እድሳት እንደተደረገለት ባለቤት የሆነው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ከወራት በፊት አስታውቆ ነበር፡፡ ይሁንና ከሰሞኑ በካፍ ባለሙያዎች በተካሄደው ጉብኝት ሜዳው በድጋሚ ማስተካከያ እንዲደረግለት መጠየቁ ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ ማዘጋጀት የሚችል ድርጅት ባለመኖሩ ባለሙያዎችን ከውጭ በመጋበዝ እንዲሠራ ከዚህ ቀደም የተጠቆመ ቢሆንም፤ የሜዳው ሥራም ሆነ የሳር ተከላው የተከናወነው እጅግ ኋላቀር በሆነ መንገድ በመሆኑ የተለያዩ ትችቶች ሲሰነዘሩ እንደነበር ይታወሳል። ሰሞኑን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋባዥነት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የካፍ ክለብ ላይሰንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ መሀመድ ሲዳት በእድሳት ላይ የሚገኘውን የአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲሁም የአቃቂ ስታዲየሞችን በጎበኙበት ወቅት፣ በቅድሚያ የተመለከቱት የአዲስ አበባ ስታዲየምን ሲሆን፤ እድሳቱ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን መግለጻቸውን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡ እድሳቱ በተለያዩ ምክንያቶች በተቆራረጠ ሁኔታ ሲካሄድ ቢቆይም የሁለተኛው ምዕራፍ ሥራ ከሞናኮ ትሬዲንግ ኮንተራክተር ጋር የኮንትራት ውል በመፈጸም ካለፉት ሁለት ወራት አንስቶ በከፍተኛ ርብርብ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር እና የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎችም በተለያዩ ጊዜያት በአካል በመገኘት ክትትል ሲያደርጉበት ቆይተዋል፡፡
በውሰት ሜዳዎች ላይ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለመፈጸም የተገደደውን ብሔራዊ ቡድን ወደ አገሩ ለመመለስም ቀድሞ በተሰጠው አስተያየት መሠረት ከሜዳው ውጪ ያለው እድሳት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ አሁን ባለበት ደረጃም መሻሻል ይገባቸዋል በሚል የተጫዋቾች መግቢያ፣ የመልበሻ ክፍል ወለሎች፣ የሚዲያ ትሪቡን፣ የቪአይፒ እና ቪቪአይፒ ትሪቡኖች፣ የመኪና ማቆሚያ እንዲሁም የቦታ ሽግሽግ ሊደረግባቸው ይገባል በሚሏቸው ክፍሎች ላይ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ባለሙያው በአጠቃላይ በእድሳቱ የታዘቧቸው ጉዳዮች ላይም ግብረመልስ በማዘጋጀት በቀጣይ እንደሚልኩ አሳውቀዋል፡፡ በተለይ በፍጻሜ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራና የተሰጡ የማስተካከያ ሀሳቦች ከተተገበሩ መስፈርቱን ማሟላት እንደሚቻልም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ሌላኛው ጉብኝት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተገነባ ባለው አቃቂ ስታዲየም ነው የተደረገው፡፡ አስቀድሞ የዞናል ስታዲየም ደረጃን እንዲያሟላ በማድረግ የተጀመረው የዚህ ስታዲየም ግንባታ፤ በድጋሚ የዲዛይን ማሻሻያ በማድረግ የካፍ መስፈርትን የሚያሟላ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎም ባለሙያው ያለበትን ሁኔታ ከተመለከቱ በኋላ፤ የመልበሻና የሚዲያ ክፍሎች፣ የቪአይፒ እና ቪቪአይፒ ትሪቡኖች እና ሌሎች አስፈላጊ ክፍሎች ሊቀመጡባቸው የሚገባቸውን ስፍራ ከማቀያየር ውጪ በጥሩ ሁኔታ መገንባታቸውን ተናግረዋል።
ግንባታው ከ70 በመቶ በላይ የደረሰው የአቃቂ ስታዲየም በግንባታ ላይ ከመሆኑ አንጻር ለማስተካከያ ሥራ ምቹ ነው። በመጫወቻ ሜዳው ግንባታ ላይ ግን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የዘርፉ ፍቃድ ባላቸው ኩባንያዎች እንዲገነባ ባለሙያው መክረዋል። በአጠቃላይ የተሠሩት መሠረታዊ ሥራዎች በቂ ጊዜ እና ትኩረት በመስጠት እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ ጥሬ ዕቃ በመጠቀም የማጠቃለያ ሥራዎች ማከናወን ከተቻለ የካፍን መመዘኛዎች በቀላሉ ማሟላት እንደሚችልም ባለሙያው መጠቆመቸውንም በመረጃው ተመላክቷል። ከዚህን ስታዲየም ቀጣይ የሥራ ሂደት በሚመለከትም ባለሙያው በየ3 ወሩ በተንቀሳቃሽ ምስል በታገዘ ቴክኖሎጂ ውይይት በማድረግ ክትትላቸውን እንደሚቀጥሉም አሳውቀዋል።
በጉብኝት መርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ፣ በፌዴሬሽኑ የክለብ ላይሰንሲንግ መምሪያ ኃላፊ አቶ አምሀ ተስፋዬ፣ የግንባታ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2015