አዲስ አበባ፡– የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የትንሣኤ በዓል ከፀጥታ ችግርና ከአደጋ ነፃ ሆኖ በሠላም እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታወቁ::
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የኢንዶክትሬሽንና የህዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረው የትንሣኤ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን ገልፀዋል::
በገበያ ቦታዎች፣ በእምነት ተቋማት፣ በታክሲ መጫኛና ማውረጃ አካባቢዎችና በመዝናኛ ቦታዎች ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ እንዲኖር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የገለፁት ኮማንደሩ በተጠቀሱት ቦታዎች በጋራና በተናጠል ወንጀልንና የፀጥታ ችግርን ለመከላከል ግንዛቤ መፍጠሪያ ቅስቀሳ መካሄዱንና ከዛሬ ጀምሮ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የፖሊስ ኃይል በስፋት እንደሚሰማራ አመልክተዋል፡፡
ከተደረገው ቅድመ ዝግጅት አኳያ ችግር ይገጥማል ብለው እንደማያስቡ የጠቆሙት ኮማንደር ፋሲካ ህብረተሰቡ ያለሥጋት በዓሉን እንዲያከብርና አካባቢውንም በንቃት በመጠበቅ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል::
በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ በበኩላቸው፣ ባለሥልጣኑ ሁልጊዜም 24 ሰዓት በተጠንቀቅ ላይ ቢሆንም የትንሣኤ በዓልን ታሳቢ ያደረገ በቂ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል::ከበዓል ጋር በተያያዘ ለሚነሱ አደጋዎች ምላሾችን ለመስጠት በስምንት የባለሥልጣኑ ቅርጫፎችና በማዕከል ደረጃ 44 የአደጋ መቆጣጠሪያ ማሽኖችና ልዩ ተሸከርካሪዎች እንዲሁም በየቅርንጫፉም በአማካይ 2 አምቡላንሶች በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውንና 1ሺ350 ሠራተኞች መመደባቸውን ገልፀዋል፡፡
ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የመኖሪያ አካባቢዎች ለሚገኙባቸው አራዳ፣ አዲስ ከተማና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ያስታወቁት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው ህብረተሰቡ፣ የእምነት ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል::ባለሥልጣኑ እሳትና ድንገተኛ አደጋን ቀድሞ የመከላከል ሥራን ከ 11 ባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም
ሙሐመድ ሁሴን