ኢህአዲግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በወሰደው እርምጃ ቀደም ሲል የነበረውን ሳንሱር የሚባለውን በሕግ እንዲነሳ ማድረግ ነው። ሳንሱሩ ከተነሳ በኋላ በሽግግሩ ወቅት ቻርተር የሚባለው ሲወጣ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ጋዜጦች መውጣት ጀምረው ነበር እንዲሁም በ1983 ዓም የፕሬስ ነፃነት የሚባል አዋጅ ወጥቶ አንፃራዊ በሆነ መልኩ በኢትዮጰያ የተሻለ ነፃነት እንዲመጣም አስችሏል። ከዛም በኋላ በ1987 ዓም የወጣው ዋናው ሕገ መንግሥት እንደዚሁ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነትን ባካተተ መልኩ መውጣቱ ለፕሬሱ ጥሩ መሰረት ነበር። በእነዚህ ህጎች መሰረት የተለያዩ በርካታ ጋዜጦች በኢትዮጵያ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ መታተም ችለውም ነበር።
ትንሽ ችግር ያጋጠመው ነገር ቢኖር መንግሥትና ፕሬሱ በተለይ በግሉ ዘርፍ የጥላትነት መንፈስ በሚመስል መልኩ ግንኙነታቸው ሻክሮ መቆየቱ ነው፤ በዚህም ተቀራርቦ በመካከላቸው ያለውን ችግር በውይይት ከመፍታት ይልቅ መንግሥትም እንደጥላት ማየት ፕሬሱም መንግሥትን በያዘው መሣሪያ የማጥቃት ሁኔታ ተፈጥሮ
አስቸጋሪ መካረር ውስጥ ተገባ፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ ባለፉት ዓመታት ብዙ ጋዜጠኞች ለእስር ተዳረጉ ተሰደዱ ፤ ፕሬሱም በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታና ስነምህዳር ውስጥ ገባ።
የጥላትነቱ ስሜት ከምን የመነጨ ነው
ይህ የጥላትነት ስሜት ለመፈጠሩ ዋናው ምክንያት ደግሞ መንግሥት በጎ በጎው ብቻ እንዲንፀባረቅለት መፈለጉና ጉዳዮን ለማስፈፀም ኃይል መጠቀሙ ለየፕሬስ እድገቱን አስቸጋሪ ሆኗል። በግሉ ፕሬስ በኩል ደግሞ ከአመሰራረቱ ጀምሮ ሚዲያውን እንደ ትግል መሳሪያ አድርጎ የማየት ሁኔታ ስለነበረ እሱም እራሱ ከፍተኛ
አስተዋጽኦ አድርጓል። በዚህ ምክንያት ደግሞ አክቲቪዚም የሚባለውና ጋዜጠኝነት ተደባልቆ በጓዙ በራሱ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። በመካከል የተሻሻሉ ነገሮች ቢኖሩም በመካከል ወደኋላ የሄደበት ሁኔታ ታይቷል።
በሌላ በኩልም በተለይ በእኔ እይታ ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የግል መገናኛ ብዙኃን እንዲሳተፉ መደረጉ ባለፉት ዓመታት የታየ አንፀባራቂ ውጤት ነው። ሆኖም አስፈፃሚ አካሉ ወይም ካቢኔው የታገዘ አልነበረም ስላልነበር የፕሬስ ነፃነት አዋጁም በዛው ልክ ተፈፃሚ መሆን አልቻለም።
አሁን ላይ የታየው አንድ ለውጥ በቀጥታ ሰዶ ከማሳደድ ወደ ራስ አቅርቦ የታሠሩ ጋዜጠኞች ተፈተው በብዛት ተዘግተው የነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ተከፍተውና ጋዜጦች ቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁ ፍቃድ እያገኙ መሥራት በመቻላቸው ለውጡን አመለካች ነው።
ባለፈው አንድ ዓመት ብዙ ጋዜጠኞች እንዳዲስ መፈጠር ችለዋል ይሄ ትልቅ እርምጃ ነው እኔ በግሌ በጣም ጥሩነው ነገር ግን ያልተፈታው ችግር የመረጃ አሰጣጥ ሥርዓት ላይ ያሉ ችግሮች ናቸው። ሌላው በተለይ በህትመት ሚዲያው አካባቢ የማተሚያ ቤት ችግር፣ የህትመት ዋጋ ንረት በአስቸጋሪ ሁኔታ ቀጥሏል። ስለዚህ ጋዜጦች መውጣት ባለባቸው ጊዜ መውጣት የማይችሉበት ሁኔታ በተደጋጋሚ እያየን ነው።
በተጨማሪ ብዙ ማስታወቂያዎችን የሚያሰራው መንግሥት ቢሆንም በፍትሃዊ መንገድ ሁሉም ሚዲያ እንዲያገኘው በተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበ ቢሆንም መንግሥት ሁኔታውን እያየ ዝም ከማለትና መመሪያና ሕግ እያዘጋጀሁ ነው ከማለት ውጭ ወደ ተግባር አለመሄዱ እንቅፋት ነው።
መገናኛ ቡዙኃን እንደማንኛውም ኢንቨስትመንት ለማንኛውም ባለሀብት የማበረታቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁልጊዜም የሚያቀርቡት ጥያቄ ቢሆንም አንድ የአበባ እርሻ የሚጠቀመውን ያክል ሚዲያውም የሚጠቀምበት አግባብ የለም ፤ መንግሥት ይህንንም ሰምቶ ተግባራዊ ቢድረግና መልስ ቢሰጥበት ምናልባት ከአሁን በኋላ በተሻለ ቁመና መሄድ የሚቻልበት አጋጣሚ ይፈጠራል።
ዩኔስኮ የዘንድሮውን የዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር መወሰኑ ፋይዳው ብዙ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ችግር ባይቀረፍ ኖሮ ይህ ዕድል አይገኝም ነበር። ከባለፈው አንድ ዓመት በፊት ዓለም የሚያውቀን በፕሬስ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግር ስንፈጥር ነው። ስለዚህ አሁን በተገኝው አዎንታዊ ለውጥ እውቅና የሚሰጥ ነው ። ሁኔታው ጥሩ አጋጣሚ ነው ስለሆነ ይህን ተጠቅመን መንግሥት ያልመለሳቸውን ጥያቄዎች እንዲመልሱ በሙያ ውስጥ ያለን ሰዎችና የሚመለከታቸው አካላት ግፊት ሊያደርጉ ይገባል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም