ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በሌሎች የክልል ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች የወጣት ማዕከላት ተገንብተው ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለወጣቱ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ወጣቶች አልባሌ ስፍራ ከመዋል በእነዚህ ማዕከላት ውስጥ በመገኘት እንደየዝንባሌያቸው በተለያዩ የኪነጥበብ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ስፖርትና በሌሎችም መስኮች ሲሳተፉ ቆተዋል፡፡ በዚህም ማዕከላቱ በመልካም ስነ ምግባር የታነፁና አካባቢያቸውን ብሎም ከተማቸውን ሊጠቅሙ የሚችሉ ወጣቶችን በማፍራት ባለውለታ ሆነዋል፡፡
በአንድ ወቅት እነዚህ ወጣት ማዕከላት ለወጣቱ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ተጠቃሽ ቢሆኑም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ተቀዛቅዘው ቆይተዋል። የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ሲሰጡም አይታዩም፡፡ ወጣቶችም ወደነዚህ ማዕከላት መጥተው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቀስቃሽ በማጣታቸው ተነሳሽነታቸው ወርዷል፡፡ በተለይ ደግሞ በስብዕና ግንባታ ረገድ ማዕከላቱ የሚጠበቅባቸውን ያህል እየሠሩ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡
አብዛኞቹም ማዕከላት ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ የተለያዩ ስብሰባዎች የሚካሄድባቸውና ልዩልዩ መንግሥታዊ ክንዋኔዎች የሚፈጸምባቸው ከመሆናቸውም ባሻገር አሁን አሁን ቪዲዮ ማሳያዎች፤ የጆተኒና ከረንቡላ ማጫዎቻዎች እንዲሁም አለፍ ሲልም ጫት መቃሚያና የቁማር ውርርድ የሚካሄድባቸው ቦታዎች እስከመሆን ደርሰዋል፡፡
በዚህም ምክንያት የወጣቱን ስብዕና ይገነባሉ ተብለው የታሰቡት እነዚሁ ማዕከላት በተቃራኒው የወጣቱ ስብዕና የሚበላሽባቸው እየሆኑ ብዙ ወላጆችን ምሬት ውስጥ ከተዋል፤ በርካታ ወጣቶችም ወደ እነዚህ ማዕከላት ከመሄድ ለመቆጠብ ተገደዋል፡፡
ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የወጣቶች ስብዕና ልማት ዘላቂነትን ለማረጋገጥ የወጣቶች ማዕከላት ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በመረዳትና ማዕከላቱ ለዚሁ የስብዕና ልማት ግንባታ እንዲውሉ ለማስቻል በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ የወጣት ስብዕና ግንባታ ማዕከላትም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን አቅጣጫ በመከተል በተዋረድ በስብዕና ግንባታ ዙሪያ ለመሥራት እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡
ወጣት ሰለሞን አባተ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ እርሱ እንደሚለው በማዕከሉ የሚኒ ሚዲያ፣ በኤች አይቪ ኤድስ ዙሪያ የምርመራ፣ ምክርና ግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ የቅድመ ወሊድ መከላከያ፣ የጂምናዚየም፣ የክብደት ማንሳት አገልግሎት፣ ከረምቡላና ፑል የመሰሉ የቤት ውስጥ ጨዋታ፣ የዲ ኤስ ቲቪ፣ ቴይኳንዶ፣ የካፍቴሪያ፣ የቤተ- መጽሐፍት፣የአይ ሲቲ እንዲሁም የጤና ነክ ስልጠና አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡፡ እነዚህም አገልግሎቶች ወጣቱ በጤና፣ በአካል ብቃት፣በአዕምሮ እንዲበለፅግ ያስችሉታል፡፡ ፑልና ከረምቡላ የመሳሰሉ ጨዋታዎችንና የካፍቴሪያ አገልግሎትን ወጣቶቹ በቋሚነት የሚጠቀሙ ሲሆን ከትምህርት ሰዓት ውጪ ተማሪዎች የቤተ- መጽሐፍት አገልግሎት እስከ ምሽት አራት ሰዓት ድረስ ያገኛሉ፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ ወጣቶቹ በኪነ ጥበብ ዘርፍ በዘመናዊና ባሕላዊ ውዝዋዜ፣ በዳንስ፣ በቲያትር ከትምህርት ሰዓታቸው ውጪ ወደ ማዕከሉ በመምጣት ሥልጠና ይከታተላሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በየአስራ አምስት ቀኑ የሥነ-ጽሑፍ ምሽት ያዘጋጃሉ፡፡ በክረምት ወቅት ደግሞ የቪዲዮ ኤዲቲንግ፣ ፊልምና ቲያትር ሥራ ሥልጠናዎችን ይወስዳሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎች መሰል አገልግሎቶችን በማዕከሉ ያገኛሉ፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ አንዳንድ ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ሳቢ አለመሆን፣ በቁሳቁስና በሰው ኃይል አለመጠናከር፣ የሚሰጧቸው አገልግሎቶች በቂ አለመሆን፣ ለሌላ ተግባርና ዓላማ እየዋሉ መሆን ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አለመቻል ችግሮች ይታዩባቸዋል፡፡ ይሁንና እንደ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከል እነዚህ ችግሮች አይታዩም፡፡ ለሠራተኞች ደሞዝ ክፍያ ከመንግሥት ከሚወስደው በጀት ውጪ በውስጥ ገቢ ራሱን በራሱ ያስተዳድራል፡፡ የጣልቃ ገብነትና ሌሎች መሰል ችግሮችም የሉም፡፡ ማዕከሉ ለታለመለት ዓላማ ብቻም ነው እየዋለ ያለው፡፡
ይህ ሲባል ግን ማዕከሉ ምንም አይነት ክፍተት የለበትም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የሰው ኃይል እጥረት አለበት፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን አንዳንድ ማዕከላት የተገነቡበት ቦታ ወጣቱን የማይስቡ ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ እዛው በወረዳ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ይገነቡና ወረዳዎች እነዚህን የወጣት ስብዕና ግንባታ ማዕከላት ለተለያዩ ጉዳዮች የመጠቀም ዝንባሌዎች ይታያሉ፡፡ ነገር ግን የእኛ ወጣት ስብዕና ግንባታ ማእከል ከዛ ወጣ ያለና ማኅበረሰቡ በሚኖርበት አካባቢ ላይ የተገነባ በመሆኑ ያን ያህል የጎላ ችግር አይታይበትም፡፡ እንደውም ማዕከሉ ሌላ አካባቢ ከሚገኙ ማዕከላት የተሻለ ነው፡፡
ከዚህ ውጪ ግን ማዕከሉ በአዲስ አበባ መሳለሚያ እህል በረንዳ አካባቢ የሚገኝ እንደመሆኑ ከጫት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ወጣቶች ግቢው ውስጥ መጠቀም አለብን፣ ኳስ እያየን እንቅማለን ከማለትና የማዕከሉን ንብረት ከመስረቅና መስበር በስተቀር ከራሱ ከማዕከሉ የመነጨ ችግር የለም፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በማዕከሉ አስቀድሞ በወጣቶች የተያዙ ፕሮግራሞች እያሉ ለፓርቲ ስብሰባ ቅድሚያ የሚሰጠበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም ወጣቶችን ከማዕከሉ ጋር የሚያቃቅር ችግር ነው፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ እንደሚለው ወጣቱ በሁለንተናዊ መልኩ ስብዕናው እንዲገነባና በወጣቱ ላይ የተለየ ሥራ ለመሥራት ማዕከሉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልገዋል። በማዕከሉ ባለው ነገር ግን አንድም በአካል ሁለትም በአዕምሮ የስብዕና ግንባታ ይደረጋል፡፡ ለአብነትም በማዕከሉ ባለው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ መጽሐፎችን ወጣቶች አንብበው በሥነጽሑፍ፣ በቲያትርና በተለያዩ ክበባት ተሳትፈው ራሳቸውን አልባሌ ቦታ ከመዋል ይታደጋሉ፡፡
ለአብነትም ከዚሁ ከማዕከሉ የወጡ ወጣቶች በባላገሩ አይዶል ተሳትፈው ተወዳዳሪ የሆኑ ወጣቶች ተፈጥረዋል፡፡ በብሔራዊ ትያትር ጨረታ አሸንፈው በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ የውዝዋዜ ትርኢት በማሳየት ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰቦቻው ገቢ እያስገኙ ያሉም ወጣቶች አሉ፡፡ ወጣቶቹ እንዲህ አይነቱ እድል ባይመቻችላቸው ምንአልባትም አላስፈላጊ ነገሮች ውስጥ የሚገቡበት እድል ሰፊ ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ወጣቶቹን ስብዕና ለመገንባት ከክፍለ ከተማው ጋር በመነጋገር በማይንድሴት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎች እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ስብዕና ግንባታን ማዕከል አድርገው ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ወጣቶች ጥቂት ናቸው። በዚሁ የስብዕና ግንባታ ዙሪያ ሥልጠናዎች ሲዘጋጁም ፍላጎቱ ኖሯቸው ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ወጣቶች የሉም። አብዛኛዎቹ ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ወጣቶች አገልግሎት ፈላጊዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ካፍቴሪያ ውጪ ካለው ገበያ በጣም ቅናሽ በመሆኑ አብዛኛዎቹ ወጣቶች በማዕከሉ ባለው ካፍቴሪያ መገልገል ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡ እግር ኳስ በዲ ኤስ ቲቪ ለማየት፣ ፑልና ከረምቡላ ለመጫወት ወደ ማዕከሉ ይመጣሉ፡፡
ነገር ግን ደግሞ የወጣት ስብዕና ግንባታ ማእከሉ በተለይ በራሱ የፌስ ቡክ ገፅ፣ቲክቶክ አካውንትና በሚኒሚዲያ አማካኝነት ትምህርት አዘል መልክቶችንና በማእከሉ ያሉ አገልግሎቶችን ለወጣቶቹ በማስተዋወቅ የስብዕና ግንባታ ስራ ይሰራል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ታዲያ ማዕከሉ የሰለጠነ የሰው ሃይል በተለይ ደግሞ በስብዕና ግንባታ ዙሪያ እውቀቱ ያለውና ሥልጠና የሚሰጥ ባለሙያ የለውም፡፡ በዚህ ዙሪያ ማዕከሉ እየሠራ ያለውም ከተለያዩ አካላት ጋር በስልክም በአካልም አነጋግሮ በመጥራትና ሥልጠና እንዲሰጡ በመጋበዝ ነው፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የወጣቶች ዘርፍ አማካሪ ወይዘሮ የሺወርቅ አያኖ እንደሚሉት የወጣቶችን ስብዕና ለመገንባት የወጣቶች ማዕከላት ያላቸው ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡ ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአስር ዓመት የልማት እቅድን መሠረት በማድረግ የዘርፉን እቅድ አዘጋጅቶ ከወትሮ በተለየ መልኩ አጋርነትን በማጠናከር በተሰጡት ተግባራትና ኃላፊነቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ወደ ተግባር ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ በበጀት ዓመቱም ከተያዙት እቅዶች አንዱ የወጣቶች ስብዕና ልማት ማዕከላትን አስመልክቶ ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ማካሄድ ነው። ንቅናቄውን ማካሄድ ያስፈልገበት ምክንያትም የስብዕና ልማት ማዕከላት ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉና ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ ነው፡፡
ማዕከላቱ ለወጣቶች የእውቀት፣ የክህሎት፣ የስራ ፈጠራና የመገናኛ አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም በተለይ ማዕከላቱን ወደ ማኅበራዊ ኢንተርፕራይዝ ከማሳደግና የስብዕና ልማት ግንባታውን በዘላቂነት ከማረጋገጥ አንፃር ሥራዎች በትኩረት ሊሠሩ ይገባል፡፡ ማዕከላቱን ለወጣቶች ስብዕና ግንባታ ለማዋልና ወደ ማኅበራዊ ኢንተርፕራይዝ ለማሳደግ በክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የመስክ ምልከታና የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል፡፡
በዚህም ማዕከላቱ ከተደራሽነት አኳያ የተሻለ ቢሆኑም ከግንባታ ዲዛይን፣ ከይዞታ ማረጋገጫ፣ ከባለቤትነት፣ አገልግሎት ጥራት፣ ከበጀትና አስተዳደር አንፃር ሰፊ ክፍተት አለባቸው፡፡ ወጣቶች በአካልና በአዕምሮ እንዲዳብሩ ብሎም የተሟላ ስብዕና እንዲኖራቸው ከማድረግ አኳያም የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል አናሳ ነው፡፡
አማካሪዋ እንደሚሉት እነዚህ ችግሮች ለመፍታትና የወጣቶች ማዕከላት የተሻለ የስብዕና ግንባታ ልማት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እንዲሁም በቂ ገቢ ማመንጨት እንዲችሉና ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ብሎም የይዞታ ማረጋገጫ ባለቤትነት እንዲኖራቸው መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በቅርቡ ተካሂዷል፡፡ ንቅናቄው ውጤታማ እንዲሆንም የዘርፉ አካላት የድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡
የወጣቶች ስብዕና ልማት ግንባታቸውን በማሻሻል፤ ሳቢ በማድረግ፣ በቁሳቁስና በሰው ኃይል በማጠናከር እንዲሁም በሚሰጧቸው አገልግሎቶች በቂ ገቢ በማመንጨት የበጀት አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ዘላቂነት ያለውና ለወጣቶች ስብዕና ልማት ግንባታ አስተዋፅዖ እንዲበረክቱ የማኅበራዊ ኢንተርፕራይዞች እሳቤን ማስረፅና በዚህ መርሕ እንዲመሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ስብዕና ግንባታ ዴስክ ኃላፊ አቶ አብዱለጢፍ መሐመድ በበኩላቸው እንደሚናገሩት ንቅናቄው ማዕከላቱ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲያገኙ፣ የተሟላ የስብዕና ግንባታ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻልና ለሌላ አገልግሎት የዋሉ የወጣቶች ማዕከላት ወደ ወጣቶች እጅ ተመልሱ ለተገነቡበት ዓላማ እንዲውሉ ለማድረግ ያስችላል፡፡
የወጣቶች ስብዕና ልማት ማዕከላት ግንባታቸውን በማሻሻል ሳቢ እንዲሆኑ አለመደረጉ፣ በቁሳቁስና በሰው ኃይል በማጠናከርና በሚሰጡ አገልግሎቶች በቂ አለመሆን፣ አንዳንድ ማዕከላት ለሌላ ተግባርና ዓላማ እየዋሉ መሆናቸውንና የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው መሆኑ፣ በራሳቸው ከመንግሥት የሚደረጉ ድጋፎች እንደተጠበቀ ሆኖ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩና በዘላቂነት በሶሻል ኢንተርፕራይዝ እሳቤ እንዲንቀሳቀሱ አለመደረጉና ገቢያቸውን ለማሻሻል የተደረገው ጥረት በቂ አለመሆኑ ከችግሮቻቸው ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ በሆነ መልኩአለመገንባታቸውናአገልግሎት አለመስጠታቸውም እንደ አንድ ችግር ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ አንፃር እነዚህን ችግሮቻውን ለመፍታት ንቅናቄው ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ለዚህም የባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ ነው፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 ቀን 2015 ኣ.ም