አዲስ አበባ፡- ሥልጣኑ፣ ቢሮክራሲው፣ መከላከያው፣ ደህንነቱ፣ ሀብቱ በተወሰኑ ቡድኖችና ግለሰቦች በሞኖፖል ተይዞ በነበረበት ሁኔታ ለውጡ ካለምንም እንቅፋት ይጓዛል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ቢሆንም፤ የተከሰቱት ችግሮች ያጋጥማሉ ተብለው ከተገመቱት በታች እንደሆኑ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ገለፁ ::
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የጂኦፖሊቲክሰና ሶሻል ጂኦግራፊ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ማህበራዊ እሴቷ ጠንካራ የሆነባት አገር በመሆኗ ህዝቡ ፈጣሪውን ስለሚፈራ እንጂ ሌላ አገር ቢሆን፤ ከዚህም በላይ ችግር ያጋጥም እንደነበር ተናግረዋል::
ፕሮፌሰሩ የኋላውን በመተው ይቅርታ በመጠያየቅ እና በመቻቻል ምሁራን እና ጋዜጠኞች በጋራ ለውጡን በመደገፍ የነፃ ሂሳዊ ድጋፍ (critical support) ቢሰጡ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል::
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለፃ በታሪክ እንደሚታወቀው በዓለም ላይ የተለያዩ ነገሥታትና መሪዎች አገር ለማስፋፋት፣ ቅኝ ገዥ ለመሆን ሲመኙና ኃያልነታቸውን ለማሳየት ሲፈልጉ በሰው ልጆች ላይ የተለያዩ በደሎችን ፈፅመዋል:: ደቡብ አፍሪካ ከጫንቃዋ ላይ የጣለችው የአፓርታይድ አገዛዝ፤ በጥቁሮች ላይ ይህ ነው የማይባል ግፍና በደል ለብዙ ዘመናት የተካሄደበት ነበር:: ያንን ያየ ከአፓርታይድ ፍፃሜ በኋላ ጥቁሮች ከነጮች ጋር በሠላም ይኖራሉ ብሎ ለማሰብ አዳጋች ነበር:: ነገር ግን የኋላውን ትተው ይቅርታ በመጠያየቅና በመቻቻል አበረው እየኖሩ ናቸው::
<< በኢትዮጵያም ወደ ኋላ እያዩ ወደ ፊት ለመሄድ የሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች መኖር የለባቸውም:: >> የሚሉት ፕሮፌሰር ተስፋዬ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አነሰም በዛ በታሪክ ላይ ችግሮች እንደነበሩ መካድ አይቻልም:: ትልቁ ነገር ከኋላው ታሪክ በመማር፣ ስህተቶች እንዳይደገሙ መተማመን ላይ መድረስ ይሻላል ብለዋል::
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም