አውድ ዓመት ሲመጣ የገበያ ግርግር የበዓሉ አንዱ ለየት ያለ ገጽታ ነው። የአውዳመት ገበያ በእርግጥ የተለየ ከመሆኑም በላይ በግና ዶሮው እንዲሁም በሬው፤ እነዚህን ለማጣፈጥ የሚያስፈልጉ እንደ ቅቤና ሌሎች ቅመማ ቅመሞች ብቻ ሁሉም በዓልን የማድመቅ ገበያውንም ሞቅ የማድረግ ኃይል አላቸው።
ሁሉም ሰው እንደ አቅምና ቤቱ ምንም ሳይጎልበት አስፈላጊውን ሁሉ አድርጎ በዓሉን ለማሳለፍም ወደ ገበያ የሚወጣው ከቀናት ቀደም ብሎ ነው። በዚህ ምክንያት ደግሞ የሚገርም ግርግር በገበያዎች ላይ ይታያል:: በብዙ ሰዎች ተጎብኝተው የማያውቁ የገበያ ቦታዎች ጎብኚዎቻቸው ይበዛሉ::
በተለይም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የትንሣኤ (ፋሲካ) በዓል ከረጅም የፆም ወራት በኋላ የሚመጣ እንደመሆኑ ለምግብ ልዩ ትኩረት የሚሰጥበትና በግ፣ ዶሮ፣ ቅርጫ ሥጋ የሚባልበትም ነው።
እኛም ወደ አንዳንድ የገበያ ስፍራዎች በመዘዋወር የ 2011 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ገበያ ምን ይመስላል ስንል ጠይቀናል። አያት አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወዳለው በግ ተራ ጎራ ብለንም የበግ ዋጋ እንዴት ነው? ስንል ጠይቀናል፤ ከአርሲ፣ ከደብረ ብርሃን እንዲሁም ከወላይታ ሶዶ የመጡ በጎች ገዥዎቻቸውን ይጠባበቃሉ።
በግ ስንት ነው ? ስንል ወጣቱ የበግ ነጋዴ ጎሽም አዲሱን ጠየቅነው «የበግ ዋጋ ትንሽ ወደድ ያለ ይመስላል» ይላል። በጣም ትልቅ የሚለው በግ እስከ 6 ሺ 5መቶ ብር ፍየልም እስከ 5 ሺ ብር ድረስ ዋጋ እንደተቆረጠለትም በመናገር።
ወጣቱ እንዳለው የበግ ዋጋው መነሻው 6 ሺ ብር ይሁን እንጂ እስከ 2 ሺ ብር ዋጋ የወጣላቸው በጎች ፍየሎችም መኖራቸውንና ምናልባትም በዓሉ ቀረብ ሲል ከየአቅጣጫው ነጋዴው ስለሚያመጣ ዋጋው ሊወርድ እንደሚችል ይገልፃል።
የበግ ዋጋ በቅርብ ከነበረበት የገበያ ዋጋ አሁን ላይ መጠነኛ ጭማሪ እንዳሳየና፤ ይህም የሆነው ከምንጩ ዋጋ በመናሩ መሆኑን አብራርቷል።
በተመሳሳይ ሰሚት አደባባይ በግ ተራ ላይ በጎችን ከደብረ ብርሃን፣ ከቦረና ከመንዝ ብቻ ከየአቅጣጫው ይዘው ከቆሙት ነጋዴዎች መካከል ወጣት ጣሰው አለሙ አንዱ ነው። እርሱ እንደሚለው ዘንድሮ የበግም ሆነ የፍየል ዋጋ ጭማሪ ያሳየው ከምንጩ በመወደዱ መሆኑንና ከ 4ሺ 2 መቶ ብር ጀምሮም ቆንጆ በግ እንደሚገኝ በተመሳሳይ ፍየልም ሙክት ያልሆነ እስከ 5 ሺ ብር መኖሩን ይናገራል።
ወጣት ጣሰው ገበያው ትንሽ ወደድ ያለ ከመምሰሉም በላይ ከየክልሉ የሚገቡ በግና ፍየሎች መንገድ ላይ በመሆናቸው ገበያው ቀዝቀዝ ማለቱንና እነሱ ሲመጡ የዋጋው ሁኔታ ወደላይና ወደታች ሊል እንደሚችልም ግምቱን ያስቀምጣል። የዘንድሮው የበዓል ገበያ ካለፈው ገና በዓል ጋር እንኳን ቢነፃፀር የ8 መቶ ብር የዋጋ ልዩነት እንዳለው ነው የተናገረው።
በአያት አደባበይ በግ በመግዛት ላይ ያገኘናቸው አቶ ግርማ መላኩ እንዳሉት «በግ ለመግዛት ሳስብ ዋጋው በጣም ከፍ ይላል ብዬ ሰግቼ ነበር፤ አሁንም ግን ዋጋው ደህና ቢመስልም ብዛት ያላቸው በጎች ባለመግባታቸው መምረጥ ማስቸገሩንና በዓሉ ቀረብ ሲል አማራጮችን አስፍቶ መግዛት አዋጭ መሆኑን ተረድቻለሁ»። ሆኖም ባሉት በጎችና በገበያው ልክ ግን ዋጋው ያን ያህል አስደንጋጭ አለመሆኑን ነው ያብራሩት።
በሌላ በኩል ዶሮ፣ ቅቤና እንቁላል በብዛት የሚገኙበት የገበያ ማዕከል ነው የካ ሾላ ገበያ፤ በዛም ተገኝተን ለመታዘብ እንደቻልነው በዓል አክባሪው ህብረተሰብ ለመገበያየት ከወዲያ ወዲህ ይላል በቅቤ ተራ ያገኘኋቸው ወይዘሮ አሰለፈች በላይ የዘንድሮ የትንሣኤ በዓል በተለይም ቅቤና ዶሮ እጅግ ይወደዳሉ በሚል ፍርሃት ውስጥ ሲጠበቅ መቆየቱን ገልፀው አሁን ላይ ያለው ነገር ግን መጠነኛ ጭማሪ በአንዳንድ ዕቃዎች ላይ ቢኖርም እንደተፈራው አለመሆኑን ይናገራሉ።
እርሳቸው አንድ ኪሎ መካከለኛ ቅቤን በ 2መቶ 80 ብር ገዝተዋል፤ ቀጥለውም የዶሮ ገበያውን ለማየት ይሄዳሉ፤ በዓሉ የእምነቱ ተከታዮች ሁሉ በደስታ በመተሳሰብ ያለው ለሌለው በማካፈል መከበር እንዳለበት በተለይም ነጋዴው ምንም ምክንያታዊ ባልሆነ ሁኔታ ገበያን የማናር ሥራቸውን ማቆም እንዳለበት ተናግረዋል።
በሾላ ገበያ የቅቤ ነጋዴዋ ሴና ሙሉ እንድምትለው የዘንድሮው የትንሣኤ በዓል በቅቤ ዋጋ ላይ መጠነኛ ጭማሪን አሳይቷል ፤ ለጋ 3 መቶ 50፣ በሳል ደግሞ 2 መቶ 60፣ መካከለኛው 2 መቶ 80 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝና በተለይም መካከለኛ ተብሎ የሚሸጠው ቅቤ የ20 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ትናገራለች።
በተመሳሳይ በዚሁ ገበያ ሦሰት ዶሮዎችን በአንድ ላይ አስራ ስትጓዝ ያገኘኋት ወይዘሮ ቤተልሄም አበራ በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ሆና ወደ ዶሮ ገበያው እንደገባች ገልፃ ሆኖም ከዚህ በፊት ከገዛችበት በተሻለ ዋጋ አንድ ዶሮ በ 2 መቶ 70 ብር ገዝታ መሄድ መቻሏን ትናገራለች።
በገበያው ዶሮን እየጠየቁ ሲዘዋሩ ያገኘኋቸው እናት ወይዘሮ ፋንታዬ አበራም የዘንድሮው የትንሣኤ በዓል የዶሮ ገበያ ተመስገን የሚያስብል ነው፤ የዛኑ ያህል የሽንኩርት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መናሩ አንዱን በአንዱ እንድናካክስ እያደረገን ነው። ነጋዴው ገበያተኛው ተሳስቦ በተመጣጣኝ ዋጋ እየተገበያየ በዓሉን በደስታ ማሳለፍ ይገባል ይላሉ።
በሾላ ገበያ ትልቅ የሚባለው ዶሮ ከ 3 መቶ 70 እስከ 4 መቶ ብር የሚጠራበት ሲሆን ከዛ በታች ያሉት ደግሞ ከ 2 መቶ 70 ብር ጀምሮ እየተሸጡ ተመልክተናል። እንቁላል የአበሻ 5 ብር የፈረንጁ ደግሞ 4 ብር፣ ሽንኩርት 20 እስከ 22ብር በኪሎ ፣ ነጭ ሽንኩርት ከ 80 እስከ መቶ ብር በኪሎ እየተሸጡም ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም
እፀገነት አክሊሉ