አዲስ አበባ፡– የኦሮሚያና የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በመጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ 528 ሺ761 ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው መመለሳቸው አስታወቁ::
ከምዕራብ ጉጂ ተፈናቅለው በጌዲኦ ዞን ከተጠለሉ ተፈናቃዮች ውስጥ 15ሺህ የሚሆኑት በትናንትናው ዕለት ወደ ቀዬያቸው መመለሳቸውን የደቡብ ክልል ፕሬስ ሴክሬተሪያት አስታወቀ:: የኦሮሚያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ በክልል ከሚገኙ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ተፈናቃዮች ውስጥ 513 ሺህ 761 ወደ ቀዬያቸው መመለሳቸውን ገልጿል::
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ አማን እንደገለፁት፤ ከትናንት በስቲያ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኤሊያስ ሽኩርና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አህመድ ቱሳ ከጌዲኦ የተፈናቀሉ ጉጂዎችን ወደ ጌዲኦ፤ ከምዕራብ ጉጂ የተፈናቀሉ ጌዲኦዎችን እንዲሁ ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከተፈናቃዮች ጋር ውይይት አድርገዋል::
ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙና ለመፈናቀል ምክንያት የሆኑ የፖለቲካ ነጋዴዎች ለሕግ ለማቅረብ የሁለቱ ክልል መንግሥታት በትኩረት ለመሥራት መስማማታቸውን የገለፁት አቶ ፍቅሬ፣ እስከ ሚያዝያ 30 ድረስ ከምዕራብ ጉጂና ከጌዲኦ ዞኖች የተፈናቀሉትን ወደ ነበሩበት ለመመለስና ለማቋቋም ከስምምነት መድረሳቸውን አብራርተዋል:: ሁለቱ አመራሮች ያካሄዱትን ውይይት ተከትሎ በትናንትናው ዕለት ከምዕራብ ጉጂ ተፈናቅለው በጌዲኦ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ 15ሺህ ወደ ምዕራብ ጉጂ እንዲመለሱ መደረጉን አብራርተዋል።
እንደ አቶ ፍቅሬ ማብራሪያ፤ በክልሉ ውስጥ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የተፈናቀሉትም ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ሥራ እየተሠራ ነው::ከከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ተፈናቅለው በከምባታ ዞን ከተጠለሉት 25 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ውስጥ ሦስት ሺህ የሚሆኑት ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል::ከመሎ ተፈናቅለው በባስኬቶ የተጠለሉትንም ወደ መሎ እንዲመለሱ ተደርጎ የማቋቋም ሥራ እየተሠራ ነው::
በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞኖች ተፈናቃዮቹን ለመቀበልና መልሶ ለማቋቋም ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ፍቅሬ፤ አሁን ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስና መልሶ የማቋቋም ሥራ በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደረጃ ተፈናቃዮቹ ወዳሉበት ቦታ ወርደው ሥራውን እንዲመሩ እየተደረገ ነው ብለዋል::
አቶ ፍቅሬ እንዳብራሩት ቤት ለወደመባቸው በቀዬያቸው ጊዜያዊ መጠለያዎችን ለመሥራት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ርብርብ በማድረግ ላይ ናቸው::አምርተው ራሳቸውን መቀለብ እስኪችሉ ድረስም ድጋፍ እየተዘጋጀ ነው::በቀጣይ ክረምት ወራት በአፋጣኝ የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲያመርቱ ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራም እየተሠራ ነው::የፀጥታ ጉዳይም የመከላከያ ሠራዊትና የፀጥታ አካላት እንዲሁ ህዝቡ ተባብሮ በመሥራት ቀድሞ የነበረው ችግር እንዳይከሰት በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
የኦሮሚያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ገረመው ኦሊቃ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ዝናብ መጣል በመጀመሩ ተፈናቃዮቹ በአስቸኳይ ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው::እስካሁንም በክልል ከሚገኙ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ተፈናቃዮች ውስጥ 513 ሺህ 761 ወደ ቀዬያቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል::የተመላሾቹ ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ ወደ ቀዬያቸው ከተመለሱ በኋላ በምግብ፣ በመጠጥ ውሃና በፀጥታ ችግር ምክንያት ዳግም እንዳይፈናቀሉ መንግሥትና ህዝብ ድጋፍ እያደረገ ነው ያሉት አቶ ገረመው፤ በዘላቂነት ተመላሾቹ እንዲቋቋሙ በቀጣይ ክረምት ወራት የግብርና ሥራቸውን በማከናወን ራሳቸውን እንዲችሉ የሚመለከታቸው አካላት ግብዓት የማቅረብ ሥራ እየሠሩም መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ገረመው ማብራሪያ፤ ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው የፀጥታ ችግር ዳግም እንዳይከሰት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው::የሀገር መከላከያ፤ የየአካባቢዎቹ የፀጥታ አካላት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም ለማስፈን እየሠሩ ናቸው::ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ በተለይም በክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው::
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም
መላኩ ኤሮሴ