የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በመጪው እሁድ የሚከበረውን የትንሳሰኤ በአል ምክንያት በማድረግ ለሜቄዶንያ የበአል ስጦታ አበረከተ።
የኮርፖሬሽኑ የበላይ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ዛሬ (ሚያዚያ 17) በሜቄዶንያ አረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በመገኘት የ100 ኩንታል ስንዴ ስጦታ አበርክተዋል።
የማዕከሉ ተወካይ አቶ ማሞ ታደሰ የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች በዓሉን በማስመልከት እንኳን አደረሳች ለማለት በመምጣታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
“መጪው የትንሳኤ በዓል እንደመሆኑ በዛሬው ዕለትም ቃል በገቡት መሰረት 100 ኩንታል ስንዴ አምጥተዋል፣ አረጋዊያንንም ጎብኝተዋል። ይህም ተግባራቸው በሌሎች ዘንድ ሊለመድና ሊመሰገኑ ይገባል። የተደረገልን ድጋፍም ትልቅ ስጦታ ነው” ሲሉም አቶ ማሞ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ከፍያለው ብርሀኑ እንኳን ለትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት፤ “ኮርፖሬሽኑ ይህን ስጦታ ያበረከተው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻርም ብቻ ሳይሆን እናንተን ለመርዳት፣ ለመጠየቅ፣ ኢትየጵያ አሁን ካለችበት ለማድረስ ትልቅ አስተዋጾ ያደረጋችሁ ባለውለታዎቻችን ለመደገፍም ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ በተያዘው አመትም ከ2000 በላይ አረጋዊያንን ምሳ ያበላ ሲሆን ፤ በዛሬው ዕለትም 100 ኩንታል ስንዴ በስጦታ ማበርከቱን ነው አቶ ከፍያለው ያስታወቁት።
ኮርፖሬሽኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አቅም በፈቀደ መጠን እንደሚቀጥልና በዚህ ብቻ እንደማይወስንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ቀደም ሲልም ለሜቄዶንያ ህነጻ ማሰሪያ አንድ ሚሊዬን ብር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።
በወንድምአገኝ አሸብር