የደርግ አብዮት በፈነዳበት ዘመን በ1966 ዓ.ም በተለይም እየተጋመሰ በሚገኘው መጋቢት ወር ላይ የወጡ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘገባዎች የዛሬው ዓምዳችን መዳረሻ አድርገናቸዋል፡፡ ለትውስታ ከመራረጥናቸው ዘገባዎች መካከል ዓሣ ማስገር ላይ የነበሩ ተማሪዎች ባሕር ገብተው ሞቱ፤ ከተመን በላይ ዋጋ ያስከፈሉ ነጋዴዎች ተቀጡ፣ ‹‹ሌባን ሌባ ቢሰርቀው ምን ይደንቀው›› እንዲሉ አበው ሌባዪቱን ሌባ ሰረቃት የሚል ዘገባም ይገኙበታል፡፡ የዘገባዎቹ ዝርዝር የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ዓሣ በማስገር ላይ የነበሩ ተማሪዎች ባሕር ገብተው ሞቱ
ጎባ ፤(ኢ.ዜ.አ.) ዓሣ በማስገር ላይ የነበሩ ፫ ተማሪዎች ከሚያጠምዱበት ፫ ሜትር ጥልቀት ካለው ባሕር ገብተው መሞታቸው ተገለጠ፡፡
ዕድሜያቸው ከ፲፬ እስከ ፲፱ ዓመት የሆናቸው ክብረት አበበ ፤ አድማሱ ላቀውና ጥበቡ ታደሰ ይባሉ የነበሩት እነዚህ ተማሪዎች የሞት አደጋ የደረሰባቸው ባለፈው ቅዳሜ በባሌ ጠቅላይ ግዛት በፋሲል አውራጃ ጎባ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኘው ሻያ ወንዝ አፋፍ ላይ ሆነው ዓሣ በማጥመድ ላይ እንደነበሩ ነው፡፡
በዚህም ዕለት ፫ቱ ተማሪዎች ከቤት ወጥተው ሳይመለሱ በመቅረታቸው ለ፫ ቀናት በተደረገው ፍለጋ አስከሬናቸው ፫ ሜትር ጥልቀት ካለው ሻያ ወንዝ ውስጥ ሊገኝ መቻሉን ታውቋል፡፡
ከዚያም አስከሬናቸው ጎባ ከተማ ወደ ሚገኘው ሆስፒታል ተወስዶ አስፈላጊው ምርመራ ከተደረገለት በኋላ እንዲቀበር ለየዘመዶቻቸው ተሰጥቷል፡፡
እንዲሁም አቶ ኃይሌ ደጨሞ ይባሉ የነበሩ የድንሾ ከተማ ነዋሪ ከአዲሱ ከተማ ወደ አሮጌው ከተማ ወደ ሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሲሔዱ ከመኖሪያ ቤታቸው ለመድረስ በግምት ፬፻፶ ሜትር ያህል ሲቀራቸው ድልቃ በተባለው ወንዝ ውስጥ ገብተው ሞተዋል፡፡
በግምት የ፷፭ ዓመት ዕድሜ የነበራቸው አቶ ኃሌ ደጨሞ አስከሬናቸው አንድ ሜትር ጥልቀት ካለው ውሃ ውስጥ በሕዝብና በፖሊሶች ዕርዳታ ወጥቶ በክፍሉ ሐኪም በተደረገለት ምርመራ በሟቹ አስከሬን ላይ ምንም የአደጋ ምልክት ባለመታየቱ ምናልባት ለውሃ ዋና ገብተው ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ማሳደሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
( መጋቢት 11 ቀን 1966 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ከተወሰነ ዋጋ በላይ ያስከፈሉ ነጋዴዎች ቅጣት ተፈረደባቸው
አዲስ አበባ ፤ (ኢ.ዜ.አ.) አቶ ተካ አስፋው የልዕልት የሻሽ ወርቅ ይልማ ቡና ቤት ባለ ንብረት ፤ አቶ ደበበ ዓለማየሁ በአገር ግዛት ሚኒስቴር ግቢ ባላቸው ቡና ቤት ውስጥ አንዱን ጠርሙስ የሾላ ወተት ፳፭ ሳቲም መሸጥ ሲገባቸው በ፶ ሳንቲም ለሕዝብ ሲሸጡ በመገኘታው አንደኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ተከሰው ቀርበው ተከሳሾቹ ጥፋታቸውን ስላመኑ እያንዳንዳቸው በ፷ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው፡፡
እንዲሁም አቶ ፀጋዬ ሙሉነህ በመሥፍነ ሐረር መንገድ ‹‹ንጋት›› እየተባለ የሚጠራው የልብስ ንፅህና መስጫ ባለንብረት ቀድሞ ለ ፩ ሙሉ ልብስ ፫ ብር ከ ፶ ያስከፍሉ የነበረውን ዋጋ በመጨመር ፬ ብር ሲያስከፍሉ በመገኘታቸው በዐቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦባቸው ተከሳሹ ጥፋታቸውን ስላመኑ ፻ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የተፈረደባቸው መሆኑን የአንደኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ግርማ ማን አግደው አስታውቀዋል፡፡
ይህ ቅጣት በተከሳሾቹ ላይ የተወሰነው የካቲት ፴ ቀን በዐቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦባቸው በ፴፩ ኛው ዓመት ነጋሪት ጋዜጣ ዓዋጅ ቁጥር ፲፮ ፫፻፩ /፷፬ በአንቀጽ ፲፱ መሠረት ነው፡፡
ይህን የመሰለው ጥፋት በመሠረቱ ፲ ሺህ ብር ወይም በሁለት ዓመት እስራት ፤ በገንዘብ መቀጫ እና በእስራትም ከፍተኛ ቅጣት የሚያስቀጣቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱ ግን የተከሳሾችን የኑሮ የገቢ መጠን ፤ በዚህ ወንጀል አፈጻጸም ምክንያት ያገኙትን ጥቅም በመገመት መቅጫውን አቃሎ ከላይ የተጠቀሰውን ቅጣት የወሰነባቸው መሆኑን የአንደኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ በተጨማሪ አረጋግጠዋል፡፡
( መጋቢት 3 ቀን 1966 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ሌባዪቱን ሌባ ሰረቃት
አሰላ ፤(ኢ.ዜ.አ.) በግርድና ተቀጥራ ከምትሠራበት ቤት ፪ ሺህ ብር ሰርቃ ስትኮበልል፤ የሰረቀችውን ገንዘብ በሌላ ሌባ የተሰረቀችው ዘውዲቱ ሞላ ፤ በ፮ ወር እስራት እንድትቀጣ አሰላ ከተማ ያስቻለው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ችሎት ፈረደ፡፡
ተከሳሽ ለእስራት ያበቃት ይህንኑ ገንዘብ የተሰረቀችው በአሰላ ከተማ በግርድና ተቀጥራ ትሠራበት ከነበረው አቶ ግርማ ድፋባቸው ቤት ፤ ባለፈው መጋቢት ፩ ቀን ፷፮ ዓ/ም / ሲሆን ፤እሷ ገንዘቡን ይዛ ወደ ተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ግዛት ከኮበለለች በኋላ ፤ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ ስትዘዋወር በጋሻው አጥላው በተባለው ልማደኛ ሌባ መሰረቋ ታውቋል፡፡
ከዚያም ዘውዲቱ ሞላ ሀብቷ በልማደኛ ሌባ መሰረቁን ለክፍሉ ፖሊስ አመልክታ ፤ በተደረገው መከታተል በጋሻው አጥላው ተይዞ ምርመራው ከተጣራ በኋላ ፤ ደብረ ብርሃን አስቻለው የከፍተኛው ፍርድ ቤት በመቅረብ ጥፋቱ በማስረጃና በሕግ ምስክሮች በመረጋገጡ ፤ አንድ ዓመት እስራ እንዲቀጣ ሲፈረድበት፤ የተሰረቀውም ገንዘብ ለባለቤቷ እንዲመለስ ታዘዘ። በዚህም መሠረት ዘውዲቱ ሞላ በፍርዱ መሠረት ገንዘቡን ለመረከብ ስትሰናዳ ዋናው ባለ ገንዘብ አቶ ግርማ ድፋባቸው በክትትል ደርሰውባት ኖሮ ፤ አስቀድሞ ገንዘብ ከሳቸው የተሰረቀ መሆኑን ማስረጃ አቅርበው ዘውዲቱ ከነገንዘቡ እጅ ከፍንጅ ተያዘች፡፡
ከዚያም ተከሳሿ ወደ አሰላ ከተማ ተልካ ወንጀሉን በፈጸመችበት ክፍል ክስ እንዲቀርብባት ተደርጎ ፤ አድራጎቷ በማስረጃና በሕግ ምስክሮች በመረጋገጡ በ፮ ወር እስራት እንድትቀጣ የተፈረደባት መሆኑን አንድ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ አስታውቋል፡፡ በሁለቱ ሌቦች መቀባበል ከተሰረቀው ከዚሁም ፪ ሺህ ብር ውስጥ ፮፻፳፭ ብር ከ፳፭ ሳንቲም ሲባክን በመጨረሻ የተገኘው ተራፊ ገንዘብ ፩ ሺህ ፫፻፵፰ ብር ከ፸፭ ሳንቲምና በተሰረቀው ገንዘብ ተገዝተው በኤግዚቢትነት የቀረቡት ልብሶችና ዕቃዎች ለባለገንዘቡ ለአቶ ግርማ ድፋባቸው እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ በዚሁ ጊዜ አብሮ ማዘዙን ቃል አቀባዩ ጨምሮ ገልጧል፡፡
( መጋቢት 27 ቀን 1966 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2015