ፋሽን እንደግል ምርጫ እንደመሆኑ ውበትና አንድናቆትም እንደየሰው እይታ ነው። በመሆኑም ፋሽን ወጥ የሆነና ይሄ ነው የሚባል ስምምነትም ሆነ ቅርጽ የለውም የሚለው ሃሳብ ብዙዎችን ያስማማል። አንድ ነገር ግን ሁሉንም ሊያስማማ ይችላል። ማንም ሰው ቢሆን የትኛውንም ፋሽን ሲከተል ዋነኛ አላማው በሰዎች ዘንድ ቆንጆ ሆኖ መታየት ነው። ታዲያ እዚህ ጋር አንድ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ሁሉም ፋሽኖች በእያንዳንዱ ሰው ዘንድ እኩል ውበትን ማላበስ ይችላሉ? ብዙዎችን የሚያስማማው መልስ አይሰጡም ይሆናል።
ምክንያቱ ደግሞ የምንከተለው እያንዳንዱ የፋሽን አይነት ውብ ሆኖ አምሮብሃል፣ አምሮብሻል የሚያስብለው የፋሽኑ የጥራት ደረጃ፣ የወጣበት የገንዘብ መጠን ወይንም ሌላ አይደለም። ጉዳዩ የተፈጥሮና የስነ-ውበት ነው። ፋሽን የግዴታ የሚያስብል ህግ ባይኖረውም የስነ-ውበት ህግ አለው። አብዛኛውን ጊዜ በፋሽንና ሞዴሊንግ ውድድሮች ላይ እነዚህ ህጎች እንደ መስፈርት ይታያሉ። እነዚህን ህጎች የተሻለ በጠበቅን ቁጥር የተሻለ ቆንጆ ሆነን እንታያለን። በፋሽናዊ እይታ ውስጥ የሚያምር ፊት ስላለን ብቻ ቆንጆ አያስብለንም። የማያምር ፊት ስላለንም አስቀያሚ አይደለንም። ሁሉም ነገሮች የሚወሰኑት ያለንን ነገር በምንጠቀምበት መንገድ ነው።
ተፈጥሮ የሰጠችንን ጥሩም ይሁን መጥፎ የውበት ገጽታ በሚመጥን የፋሽን አይነት ጠብቆ ማቆየትም ሆነ ማከም እንችላለን። የስነ-ውበት ህጎቹ ባለን የሰውነት ቅርጽ፣ ቁመት፣ የቆዳ ቀለም፣ አቋም እንዲሁም ባለን የሰውነት ክብደት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እነዚህ ነጥቦች በእያንዳንዱ የፋሽን ስርዓት ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው። አንዳንድ ጊዜ ወደ ቡቲኮች ጎራ ብለን የሚያምር ልብስ ገዝተን እንመጣና ስንለብሰው ግን በእኛ ላይ የማያምር አይነት ሆኖ ልናገኘው እንችላለን። አንዳንዴ ደግሞ እኛ አስጠልቶን የጣልነውን ለሌላ ሰው ሰጥተነው አሊያም ድንገት ካስቀመጥንበት አንስቶ ለብሶት ስናየው እስከዛሬ ያልታየን የልብሱ ውበት ይገለጥልና አዲስ ይሆንብናል።
ስለዚህ በአንዱ እያማረ በሌላው ደግሞ ውበቱ የሚደበቅበት ምክንያት የህጎቹ የስነ-ውበት ሚስጥር ነው። ታዲያ እነዚህን ህጎች በመከተል የእኔን የውበት ቁልፍ እንዴት ነው ላገኘው የምችለው አሊያም የማውቀው ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። ነገር ግን ምላሹ ቀመር አሊያም ስሌት አይደለም። ይህን ለማግኘት ስለ ተፈጥሯዊ የቀለማት ውህደት በጥቂቱም ቢሆን ማወቅን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል በእነዚህ ህጎች ውስጥ የቀለማት ህግጋቶች ይገኙበታል። ቀይ ሰው ከወገብ በላይ ቀይ ቀለም ያላቸውን አልባሳት ባይለብስ ይመከራል። የፊቱና የልብሱ ቀለም በሚመሳሰልበት ወቅት የሰውየው መልክ ይደበቃል አሊያም የልብሱ ውበት ይደበዝዛል።
ይሄ ደግሞ ለእይታ የማይማርክ ገጽታን ያጎናጽፋል። እግረ ቀጭን የሆኑ ሰዎች ከቁምጣና በጣም ጠባብ ከሆኑ አልባሳት ይልቅ ሰፋ ያሉ ሱሪዎችን ቢያዘወትሩ የተሻለ የውበት ገጽታ ይኖራቸዋል። ሌላው ደግሞ ሱሪ፣ ጫማ፣ ሸሚዝ፣ ኮት ወዘተ..የምንጠቀምበት መንገድ በራሳቸው እይታዊ ውበትን መፍጠር ይችላሉ። ምን አይነት ሱሪ ከምን አይነት ጫማ ጋር ብንለብሰው የተሻለ ውበት ይኖረዋል…ለመረጥነው ሱሪ አሊያም ሹራብ ከቀለማትም ሆነ ከሌሎች ነገሮች አንጻር የተሻለና አብሮ ሊሄድ የሚችል ነገር መምረጥ ከቻልን አለባበሳችንም ጥሩና ያማረ መሆን ይችላል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት በአንድ ላይ መሰባጠራቸውና ከላይ እስከታች የተሰባጠሩበት መንገድ ለእይታ የተለየ ውበትን ይፈጥራሉ። ነገር ግን ቀለማቱ ለየብቻ ቢሆኑ አሊያም ቅደም ተከተላቸው በእንዲህ አይነት መልኩ ባይሆን ኖሮ ያንን ውበት ላናየው እንችላለን።
የምንከተላቸው ፋሽኖች ስኬታማና ሁሌም ተመራጭ ለመሆን ምንጊዜም የራሳችንን ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል። ስታይሎቻችን የተፈጥሮ ውበታችንን አጉልተው የማውጣትም ሆነ የመደበቅም ኃይል አላቸው። አንዲት ጸጉሯ ከፊት ገባ ያለ ቆንጆ ሴት፣ ጸጉሯን ሹርባ ብትሰራው የውበት ገጽታዋን ሊያበላሽና ቁንጅናዋን ሊሰውረው ይችላል። ነገር ግን ከዚህ ይልቅ የጸጉሯ ስታይል ፓንክ ቢሆን የተሻለ ይሆናል። ጸጉሯን ወደፊት በመድፋት ገባ ያለውን ክፍል የሚሸፍንላትን ስታይል በመጠቀም ክፍተቱን ልትሞላው ትችላለች። አብዛኛውን ጊዜ ወንዶች ጸጉራቸው መመለጥ ሲጀምር ኮፊያ ያዘወትራሉ። ራሰ በራነት በተፈጥሮ የሚፈጠር ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ይህ ተፈጥሮ ለአንዳንዶቹ ውበትና የሚያምር ገጽታን አላብሷቸው እንመለከታለን።
እዚህ ጋር ከላይ ያነሳነውን የሰውነት ቅርጽ የምትለዋን የስነ-ውበት ህግ እናነሳታለን። መመለጥ የሚያምርባቸውና የማያምርባቸው እነማን ናቸው ካላችሁ፤ ምላሹ የሚገኘው ሰዎቹ ባላቸው የራስ ቅልና የፊት ቅርጽ የሚወሰን ይሆናል። ሁልጊዜ ባይሆንም፣ አብዛኛውን ጊዜ ትልቅ የራስ ቅል ያላቸው ሰዎች እምብዛም ጸጉር ላያምርባቸው ይችላል። በሴቶቹ ዘንድም ከጸጉር ይልቅ የጸጉር ቁርጥ የሚያምርባቸው እንዳሉ አስተውለን ሊሆን ይችላል። በዚያው ልክ ደግሞ ጸጉራቸውን ከመቆረጥ ይልቅ ሲያሳድጉ፣ ሹሩባና የመሳሰሉትን የጸጉር አሰራሮች ሲከተሉ የሚያምርባቸውም እንዲሁ ሞልተዋል። እነዚህ ምሳሌዎች ተፈጥሮ ምን አይነት የፋሽን ሳይንስን መከተል አለብን የሚለውን ሀሳብ ያጠናክራሉ። ስለዚህ በፋሽኖቻችን ውስጥ ውበትን ለመፍጠር በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሁልጊዜም ተፈጥሯችንን ያማከሉ መሆን አለባቸው።
ፋሽን ጥበባዊ ሳይንስ እንደመሆኑ የፋሽን ተከታዮች ስንሆን ደግሞ አስቀድመን ሳይንሱን ልናውቅ ይገባል። በሳይንሱ ውስጥ ያሉት እነዚህ ህጎችም ከሰው ሰው እንደሁኔታው የሚለያዩ ናቸው። እነዚህን ነገሮች ለማወቅ ማስተዋልን እንጂ ብዙ ማሰብም ሆነ መጨነቅና መጠበብ የሚጠይቁ አይደሉም። ምናልባትም አብዛኛዎቹ የምናውቃቸው ነገር ግን የማናስተውላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ሁሉም ሰው ቆንጆና ውብ ሆኖ መታየት ይችላል። ሁሉም ሰው ደግሞ የራሱ የሆኑ የውበት ምንጭና ሊከተላቸው የሚገባው የራሱ የሆኑ ስርዓቶች አሉት። ትልቁ ነገር ካለን ነገር በመነሳት ለእኛ የሚመጥነውን መፈለግ ነው።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም