ወላጆችን ወላጅ የሚያስብላቸው በመውለዳቸው ብቻ አይደለም። መውለድ አንዱ ጉዳይ ቢሆንም ወላጅ ለልጁ ሊያደርግ የሚገባውን አድርጎ ማሳደግ ደግሞ ግዴታ ጭምር ነው። ይህን የማያደርግ ወላጅ ግን እስከነተረቱ “የከብት እዳሪም …. ይወልዳል ” ይባላል። ይሄ የሚባለው ወላጅ ወላጅ የሚሆነው ስለወለደ ብቻ ሳይሆን የወላጅነቱን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ሳይችል ሲቀር፣ ልጆቹን ለቁም ነገር ሳያበቃ ሲቀር፣ ሲያስርብ ሲያስጠማ፣… ነው። ለልጅ የሚያስፈልገውን ካላደረገ “ወላጅ” የሚለው በጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። ወላጅ ወላጅ የሚሆነ ታዲያ ያፈሯቸውን ልጆች በወላጅ የኃላፊነት ስሜት፣ በስነምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ ሲችል ነው። ለልጅ የሚያስፈልገውን በአቅሙ አሟልቶ ሲያሳድግ ነው። ልጅን በፍቅር ማሳደግ ሲቻል ነው። አባትን አባት የሚያደርገው ለሚወስደው ማንኛውም እርምጃ ኃላፊነትን የሚወስድ ሲሆን ነው። ለእናትም በተመሳሳይ።
አባትን አባት የሚያደርገው ራስ ወዳድ አለመሆኑ ነው። አባትነት መስጠት ማካፈል ነው። ለመስጠትና ለማካፈል አባት የፍቅር ሰው መሆን አለበት። ልጆቹን በትህትና ማገልገሉ ነው። አባትነት ዝም ብሎ የተሰጠ ስያሜም ተግባርም ሳይሆን የወላጅነት እድል ነው። አባት ልጆቹን በማገልገል መምራት ይገባዋል። ልጆቹን በትጋትና በታማኝነት መምራት አለበት። መንከባከብ፣ ማብላት ማጠጣት፣ ማልበስ ማስተማር ሁሉ የአባት ተግባር ወይም የውዴታ ግዳታም ነው። ልጅን በስነምግባር ማሳደግ፣ ለራሱም ለሀገርም ለወላጅም ልጅ እንዲሆን አድርጎ በእውቀት፣ በስነምግባር መቅረጽም ይጠበቅበታል። በድህነት ውስጥ ያለ ሰው ቢሆን እንኳን ለልጁ ፍቅር ሰጥቶ ከድህነት ለመውጣት የሚችልበትን መንገድ ማሳየት ይኖርበታል። በአንዳንድ አጋጣሚ የሚታየው ግን ልጅን ወላጅ መጠቀሚያ ሲያደርገው ነው። መለመኛ፣ በልጅ ጉልበት መነገድ ( ገንዘብ ማግኛ) ሲደረግ ነው። ይሄ እንደ ሰው አስተሳሰብም ሆነ በህግ የሚያስጠይቅ ነው።
አባትነት የ24 ሰዓት የ7 ቀን ኃላፊነት ነው። አባትነት መናገር ማስተማር ብቻ ሳይሆን መኖርን ይጠይቃል። አባት እንዲያውቁትና እንዲከተሉት ለልጆቹ ጊዜን መስጠት ይገባዋል። ልጆች ከንግግር በላይ ኑሮን ይኮርጃሉ። በአስተሳሰብ በአነጋገርና በድርጊት ለልጆች መልካም ምሳሌ መሆን ነው። አባትን አባት የሚያደርገው በትጋት ማሳደጉ ነው። እንዲሁም ማሳደግ ማስተማሩ፤ ማብላት ማጠጣቱ ብቻ ሳይሆን ጥፋቶችንም በሆደ ሰፊነት ማየትና ማረም መቻሉ ነው። ይቅርታና ምህረት ማድረጉ ነው። ሌላም ሌላም ማለት ይቻላል።
አባት ልጆቹን ለክፋት አሳልፎ የማይሰጥ፤ በተግዳሮት ለመከላከል ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ሊሆን ይገባዋል። ችግር ወደ ልጆች ላይ ከሚመጣ አባት ራሱ ዋጥ የሚያደርገውና ቤተሰቡን የሚጠብቅ መሆንም አለበት። የነገሮችን አካሄድ በትጋት የሚከታተል አደጋን ከሩቅ የሚያይ ትጉህ ጠባቂ፣ ዋስ ጠበቃ ሊሆን ይገባዋል። ከጥቂቶች በስተቀርም አባት ያልነውን ሆኖ ነው የምናየው። አንዳንድ ጊዜ ግን እጅግ የማይጠበቅ አስደንጋጭና አስገራሚ ዜናዎችን እንሰማለን። አባት ልጁን ደፈረ አባት ልጁን ገደለ … የሚሉ።
ሰሞኑን ከወደ ምዕራብ ጎንደር ዞን ፍትህ መምሪያ ያገኘነው መረጃ ግን አባት ይህን ያደርጋል እንድንል አስገድዶናል። ከምዕራብ ጎንደር ዞን ፍትህ መምሪያ ያገኘነው መረጃ እንደሚገልጸው፤ አባት ልጁን ምግብ ሳትሰሪ ጠበቅሽኝ ብሎ ደብድቦ መግደሉን ነው። ነገሩ እንዲህ ነው…..
አባት…..ወይስ?
አባት አቶ አለፈ አዲሱ ገብሬ ይባላል። ከሰው ጋር ነገር አለሙ የማይገጥምለት ከዚህም ከዛም መናጨት የሚወድ አይነት ሰው ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ ነጭናጫ ስለነበር “ አይፀዳሽ…..” በሚል ቅፅል ስም ነበር የሚጠራው። ምንም ነገር አስደስቶት አያውቅም። ከማንም ጋር መግባባት ስራ የሚሆንበት የአንድም ሰው ሀሳብ ከእሱ ሀሳብ ጋር የማይጣጣም ባህሪ ያለው ሰው ነበር። ለአቅመ አዳም እንደደረሰ እንደምንም ቤተሰቦቹ ሰው ፈለገው ሽማግሌ ልከው ቢድሩትም ትዳሩ በጭቅጭቅና በንትርክ የተሞላ ነበር።
አንዳንዴ እራሱም በማያውቀው ምክንያት ሚስቱ ላይ ሲጮህ ይገርመው ነበር። ለመግባባት የሚያደርጋቸው ሙከራዎች በሙሉ ይበልጥ የሚያጣሉት፤ የሚናገረው ነገር በሙሉ ለአድማጩ ጆሮ የማይመች፤ የትዳር አጋሩም “ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል እድሜ ልኩን ያለቅሳል” ነገር ሆኖ በመቻልና ባለመቻል መካከል ተውተርትራለች። በትዳር ሂደት ውስጥ መውለድ መክበድ የተለመደ ነውና አተካራው የማያጣው ቤት በሴት ልጅ ተባረከ። ልጅት የተወለደች ሰሞን ቤቱ ውስጥ የተፈጠረው ንትርክ እንደመቀዛቀዝ ብሎም ነበር። “ወዳጅ ዘመዱም ልጅ ሲወልደ ልብ ገዛ….” በማለት ደስታውን ገለፀ።
ያዳቆነው ሴይጣን ሳያቀስስ አይተውም እንዲሉ ከአምስት አመታት በኋላ ክፉ አመሉ አገረሸበት። ዳግም ንዝንዝና ጭቅጭቅ ተጀመረ። ከጭቅጭቁም ዘሎ ዱላ ተከተለ። ያኔ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የወሰነችው ሚስት የአምስት አመት ልጇንና ባሏን አስተኝታ በጠፍ ጨረቃ ቤቱን ጥላ ዳግም ላትመለስ ተሰደደች።
ያኔ ነው እንግዲህ አባትና ልጅ በግላጭ የተዋወቁት። አቶ አለፈ አመሉ ስለከፋ ወዳጅ ዘመድ አይቀርበውም ነበር። የአምስት አመት ህፃን ሴት ልጁና እሱ ብቻቸውን መቅረታቸውን ተከትሎ ልጁን የሚበላ ለማቅመስ ከማጀት መግባት ግድ ሆኖበታል።
ግብርና ሲሄድ እንደ ወትሮው ምሳ አስሮ ለሚጠጣው ጉሽ ጠላን ሰንቆ የሚሄድለት ይቅርና አስከተሏት ግብርና ለሚሄደውን ህፃን ልጁን ኩርማን የሚመግብለት አጣ። ከልጅነት እስከ እውቀት እንኳን ማጀት ገብቶ ሊያበሰል የቀረበለትንም አቃቂር ሲያወጣ ነው የኖረው። እንደምንም እየታገለ ያለፋቸው አመታት ከባድ ፈተና ሆነበት አሳለፈ። በሕይወት ትግል ውስጥ አመት አመትን እየጨመረ ልጅቷም ከፍ ከፍ እያለች ሄደች።
ልጅት እንደጠነከረች የእማወራነትን ቦታ ተክታ ታገለገል ጀመር። በተቻላት አቅም ምግብ ሰርታ ለአባቷ ማቅመስ ጀመረች። ከአባቷ እየተደበቀችም ሄዳ የምትጠይቃቸው ዘመዶቿ የሚቆጣጥሩላትን ይዛ እየመጣች በወግ እህል መመገብ ጀመሩ። ማደግ አይቀርምና ልጅት እያደገች ስትሄድ ጉርምስና መጣ። ካልታዘዝኩኝ አልሰራም አይነት ነገርም ታሳይ ጀመረ። ከአባቷ ጋር የምታሳልፈው ሕይወት ምንም ደስታን የማይሰጥ እየሆነባት ከሱ የምትገላገልበትን ቀን መናፈቅ ጀመረች።
ያልታሰበው የአባትና ልጅ ፀብ
የአባት የከረመ አመል የልጅ የጉርምስና ባህሪ አንድ ላይ ተደማምሮ አባትና ልጅ ምንም መግባባት አቅቷቸዋል። ልጅ አልታዘዝም ባይነት አመል አምጥታለች። አባትም እንዴት ብትደፍረኝ ነው በሚል ነጋ ጠባ ይነታረካሉ። በዚህ መካከል አንድ ቀን ፀባቸው ከረረ። አባት እርሻ ውሎ ሲመጣ ልጅቷ ከጓደኞቿ ጋር ፀጉራቸውን ሲሰራሩ ውለው ገና ቤት መድረሷ ነበር።
አባት በተቆጣ ድምፅ “ራቴን ወዲህ በይ” አላት።
ልጅም “ መች ሰርቼ..” አለች ፍርሃትና ደፍረት በተቀላቀሉበት ድምፅ።
አባት “ ለምነ ነው ያልሰራሽ ?” አላት ቁጣውን መቆጣጠር አቀቶት።
ልጅ “ መች አዘዝከኝና…” አለችው።
ያን ጊዜ ነው እንግዲህ ቁጣው ከቁጥጥር ውጭ የሆነበት አባት ለምን እራቴን /ምግብ አልሰራሽም በማለት ልጁን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ደብድቦ ዛሬ ለፀፀት የዳረገውን ጉዳት ያደረሰባት።
የመጨረሻዋ ቀን
አቶ አለፈ አዲሱ ገብሬ የተባለ ተከሳሸ ነዋሪነቱ ቋራ ወረዳ ወርቂና ቀበሌ ሲሆን ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 3:00 አካባቢ ቋራ ወረዳ ወርቂና ቀበሌ ወንበልጌ ተብሎ ከሚጠራው ልዩ ቦታ ከመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ከ15 ዓመት ልጁ ጋር ከባድ ፀብ ውስጥ ይገባሉ። ከልጅቱ ጋር አንድ አንድ እየተባለ የተካረረው ፀብ ባልታሰበ ሁኔታ ወደ ኃይል ጥቃት ይቀየራል።
አባትየው አንድያ ሴት ልጁን “ሳልጠይቅሸ ለምን እራቴን አዘጋጅተሽ አልጠበቅሽኝም?” በሚል ምክንያት እጇን እና እግሯን በሰንሰለት በማሰር በዱላ እና በሲባጎ በተደጋጋሚ ይደበደባታል። ድብደባውን መቋቋም ያቃታት ወጣትም ሕይወቷ ባልታሰበ ሁኔታ አባቷ እጅ ላይ ጠፋ።
የልጅቷን የድረሱልኝ ድምፅ ከርቀት የሰሙ ጎረቤቶችም ሰውየው አመለኛ ስለሆነ ሊገላግሉ ለመግባት ባይደፍሩም በአካባቢው ያገኙትን የፀጥታ ኃይል ጠርተው ቤቱን ያስከፍታሉ። ሰዓቱ ምሽት ቦታው ገጠራማ ስፍራ በመሆኑ ልጅት ጉዳት ሳይደርስባት መድረስ ሳይችሉ ይቀራሉ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ የማህበረሰቡን ጥቆማ ተከትሎ ሲደርስ አባት ልጁን የገደላት መሆኑን ይመለከታል። ገዳይን በቁጥጥር ስር አውሎ በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማረጋገጥ የቋራ ወረዳ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ምርመራ አጣርቶ ለምዕራብ ጎንደር ዞን ዐቃቤ ህግ መምሪያ መዝገቡን ልኳል።
የዞን ዐቃቤ ህግም የምርመራ መዝገቡ እንደደረሰው መዝገቡን በመመርመር ተከሳሹ የገዛ ልጁን ለምን ምግብ አላዘጋጀሽም በሚል ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ደብድቦ የገደላት በመሆኑ የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 539 (1- ሀ) በመጥቀስ በከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ክሰ መስርቶ ተከራክሯል።
ተከሳሹም ወንጀሉን አልፈፀምኩም በማለት ክዶ የተከራከረ ቢሆንም ዐቃቤ ህግ ምስክሮችን አስቀርቦ ያሰማ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ህግ እንደክሱ አመሰራረት ያስረዳ በመሆኑ ተከሳሹ የዐቃቤ ህግን ክስ እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።
ውሳኔ
ተከሳሹም የመከላከያ ምስክር የለኝም በማለቱ የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠ ሲሆን የዐቃቤ ህግንና የተከሳሹን የቅጣት አስተያየት ካዳመጠ በኋላ ዛሬ በቀን 12/07/2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹንና መሰል የወንጀል ድርጊት የሚፈፅሙ ግለሰቦችን ያርማል፣ ያስተምራል ያለውን የ18 ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣት ወስኗል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2015