ሰላም በእምነት ጥላ ስር ላሉ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ተስማምቶ ለመኖር ጭምር ወሳኝ ነው። በቀላል ነገር ሁሉ የሚከፋን፣ በጥቂት ሆድ የሚብሰን ከሆነ ሰላማችን ይደፈርሳል። ወጥተን መግባት፣ ተኝተን መነሣት አንችልም። በአሁኑ ጊዜ ስለ ሰላም ከመናገር ባለፈ ሰላም እንዲመጣ ቁርጥ ውሳኔ መወሰንና ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። የሚሰማው ጦርነት፣ ግጭት፣ መለያየት ነው። እነዚህ ሰላም ካላመጡ ብዙ ወጪ የማይጠይቀውን ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ይቅርታን መያዝ ግድ ነው።
ስጋት፣ ፍራቻ፣ መጠራጠር የሌለበት ይልቁንም ተስፋ፣ ፍቅር፣ እምነት፣ የሚገኝበት ሕይወት የሀገርን ሰላም ጠብቆ ለዜጎች ወጥቶ መግባት ዋስትና ይሰጣል። ሰላማውያን እንኳን ከሰው ከአራዊት ጋርም ለመኖር ችለዋል። የእምነት ሰዎች ለአምላካቸው ያላቸውን ፍቅር ለመግለጥ ለእነሱ የሚገባውን ሳይቀር አሳልፈው የሚሰጡ፣ ለእኔ ይቅርብኝ ለአንተ ይሁን የሚሉ ናቸው።
ዛሬ ከስግብግብነት ርቀን ያለንን እየሰጠን ሃይማኖታችንን በምግባር እንድንገልጥ ይጠበ ቃል። ከምግባር ዕሴቶች አንዱ ደግሞ ሰላም ነው። ሰላም የሚመሠረተውም በሆደ ሰፊነት፣ በአርቆ አሳቢነት፣ ስምን ተክሎ ለማለፍና ለትውልድ የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ከመፈለግ ነው። ዓለምን የለወጡ፣ ለጨለማው ዓለም ብርሃን የሆኑ ሰላማውያን ሰዎች ናቸው።
እንዲህ ዓይነት ሰዎች ተከብረው የሚኖሩ፣ ታሪክ በመልካም ሲያነሣቸው የሚኖሩ መሆናቸውን መረዳት ይገባል። ቤተ እምነቶች ስለ ሰላም የሚሰብኩት ከሰላም ትርፍ እንጂ ኪሳራ፣ ጥቅም እንጂ ጉዳት ስለሌለው ነው። እኛስ በዓልን ስናከብር ለሰላም ምን ያህል ዋጋ ሰጥተን ይሀን? በበዓል ዋዜማ ያሰባሰብነውን አስተያየት እነሆ…
ተወልዳ ባደገችበት አማራ ክልል ጎጃም ቡሬ አካባቢ የፋሲካ በዓል አከባበር ለየት ያለ ነው የምትለን ወጣት ትርንጎ ፀጋ ናት። ክብረበዓሉን ለየት ከሚያደርጉት ከአይረሴ ሁነቶች አንዱ የበዓሉ አጀማመር ሲሆን በአካባቢው የፋሲካ በዓል የሚጀመረው በቤተሰቡ በእድሜ ትልቅ በሆነው ቤት ነው ስትል ሀሳቧን አካፍላናለች። የፋሲካ በዓል በዚህ መልክ ቢጀመርም የመተሳሰብ፣ የመከባበርና የፍቅር መገለጫዎቹ ግን በርካታ እንደሆኑም ጠቁማለች።
በዓሉ በእድሜ ትልቅ በሆነው ቤት የመከበሩ ተምሳሌት አክብሮት እንደሆነ የምትናገረው ትርንጎ ሁሉም እንደ እድሜ ቅደም ተከተል
ለበዓሉ ምግብና መጠጡን ያዘጋጃል። በዝግጅቱ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ጎረቤትም ይታደማል። እንዲህ መተሳሰብና አብሮ መብላት ያለበትን በዓል ከቤተሰቦቿ ጋር ለማክበር ዛሬ ከአዲስ አበባ ተነስታ መድረሻዋን ጎጃም ቡሬ መሆኑን ገልፃልኛለች።
በመዲናዋ አዲስ አበባ ውስጥ በትምህርት ላይ የምትገኘው ወጣቷ እንዲህ የምትናፍቀውን በዓል ለመታደም ሰላም ትልቅ ዋጋ እንዳለው ትገልጻለች። ትርንጎ ቡና፣ ስኳር እና ሌሎች በገጠር አካባቢ በቀላሉ የማይገኙ ቁሳቁሶችን ይዛ አገሯ ለመግባት ገበያዋን አስቀድማ መሸመቷን አመልክታናለች።
አፋቸውን የፈቱበት የትግርኛ ቋንቋ ሀሳባቸውን በአማርኛ ለመግለጽ እያስቸገራቸውም ቢሆን የበዓሉን ስሜት ያካፈሉን አቶ ሀብታም ገብርአብ ቀበና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግለሰብ ቤት ተከራይተው ከሁለት ልጆቻቸው ጋር እንደሚኖሩ አጫውተውናል። ከሦስት ወር በፊት ከአስመራ ኢትዮጵያ የመጡት አቶ ሀብታም አሁን ወደ ስዊድን ሀገር ለመሄድ የሚያስፈልጋቸውን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ በኪራይ እየኖሩ መሆኑን አስታውቀዋል። ላለፉት 20 ዓመታት ኤርትራና ኢትዮጵያ በሰላም እጦት መለያየታቸው በሕዝቦች መካከል የተፈጠረውን ቀውስ በመጥፎ መልኩ ያስታውሱታል።
ዛሬ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ሰላም ወርዶ አሁን ያሉበትን ሁኔታ ማየታቸውን እጃቸውን ወደ ሰማይ በማንሳት አምላካቸውን አመስግነው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም እድሜና ጤና ተመኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ሰላም እንዲወርድ
የአንበሳውን ድርሻ ባይወጡ ኖሮ አሁን ያገኙትን ዕድል እንደማያገኙ አልደበቁም። አቶ ሀብታም የፋሲካን በዓል ለማክበር በአቅማቸው የተዘጋጁት እንግድነት ሳይሰማቸው ኢትዮጵያ ውስጥ መቆየት መቻላቸው ሰላም ምን ያህል ትልቅ ዋጋ እንዳለው ማሳያ በማድረግ ነው።
ወጣት ወርቁ ተቻለ በአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ‹‹ሰላም ለማምጣትም ሰላም ለማደፍረስም እኛው ነን መንስኤዎቹ። ሰላም ወዳድ የሆነው ሕዝብ ከተባበረ ሰላም አደፍራሾችን ከውስጣችን ማውጣት አያቅተንም። ትልቁ ነገር ለሰላም መተባበር ነው የሚያስፈልገው›› በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
ወጣት ወርቁ እንዳለው፣ ሕዝቡ በአካባቢው ችግር የሚፈጥሩትን በመለየት ለሕግ አሳልፈው እንዲሰጡ ከፖሊስ ኃይሎች ጋር በቅርበት ለመስራት የተጠናከረ ሥራ ተጀምሯል። በተለይ ወጣቱ በሰላም ላይ የጎላ በመሆኑ ዋና ተሳታፊ ሊሆን ይገባል ሲል መክሯል። ሰላም ለበዓሉ ብቻ ሳይሆን ለእየዕለት ተዕለት ኑሮ መረጋገጥ መቻል አለበት ሲል ሀሳቡን ሰንዝሯል።
ነጠላቸውን አጣፍተው ያገኘናቸው ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ በዓሉን በአቅማቸው ለመዋል ዝግጅት ማድረጋቸውን ነግረውኛል።በዓል አብሮነትን የሚያሳይ እንደሆነም አስታውሰው በበዓል ጊዜ ኅብረተሰቡ አብሮ ማሳለፉ የበዛ ቢሆንም በአዘቦቱም ቀን አንዱ ጎረቤት ለሌላው ሌላ ቤተሰብ የሚያስብለት መሆኑን አስታውሰዋል። በዚህ የጸሎት ወቅት ስለሀገራቸው እና ስለሕዝባቸው ሰላም መጸለያቸውን እና የዘወትር ጸሎታቸውም እንደሆነ ወይዘሮ አበራሽ ተናግረዋል።
የትንሳዔ በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከሚያከብሯቸው ሃይማኖታዊ በዓላት ትልቅ ስፍራ የሚሰጡት እንደሆነ የእምነቱ ተከታዮችና የእምነቱ አባቶች ይናገራሉ። የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ በዓሉ ትልቅ የደስታ እና የይቅርታ እንደሆነ ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንዳሉት የእምነቱ ተከታዮች ከእምነቱ ተከታይ ውጪ ከሆኑት ጋርም ደስታቸውን በመካፈል በዓሉን ያከብራሉ። ይህ የደስታ ቀን ከጥላቻና ከምቀኝነት በራቀ መንፈስ የሚከበር ሲሆን ከበዓሉ በፊት ያልታረቁ ሰዎች ካሉ ታርቀው ይቅር በመባባል ትንሳኤውን ያከብራሉ ብለዋል። ኅብረተሰቡ ሀገር የሚገነባው ከግለሰብ ጀምሮ መሆኑን ተገንዝቦ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ የሚያዘውን መፈጸም እንዳለበት መክረዋል። በተለይም ምዕመናን ለጾም ለጸሎት እንደሚተጉት ሁሉ ለሰላሙም እንዲተጉ ጠይቀዋል።
በዓልና ሰላም የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ገጽታ እንደሆኑ የሚገልጹት መጋቢ ዘሪሁን በዓል በራሱ ሰላም እንደሚፈልግና ሙሉዕ የሚሆነውም ሰላም ሲኖር እንደሆነ ያስረዳሉ። በዓልን በደመቀ ዝግጅት ለማክበር የተለያዩ ጥረቶች እንደሚደረገው ሁሉ ለሰላም ተመሳሳይ ጥረት በማድረግ የላቀ ዋጋ በመስጠት ተገቢውን ሥራ መስራት ይገባል ይላሉ።
«ኢትዮጵያ የእምነት ሀገር ናት» የሚለውንም በተግበር ለማሳየት በሰላም ላይ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል። ባለፈው እሁድ በሲሪላንካ በቤተእምነት ውስጥ ሆነው የትንሳኤ በዓልን ሲያከብሩ በአጥፍቶ ጠፊዎች የደረሰው አደጋ የበዓል ድባቡን ያበላሸ እና አሳዛኝ እንደነበር ልብ ሊባል ይገባል ሲሉ መክረዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2011
በ ለምለም መንግሥቱ