ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ግን የፕሬስ ነጻነትን የሚገፉ አሰራሮች ተከስተው የፕሬስ ነጻነት ብቻ ሳይሆን ፕሬሱ እራሱ አለምም የለምም በሚባል ደረጃ ላይ ሆኖ ቆይቷል። የፕሬስ ነጻነት ህግም ከወረቀት በዘለለ በተግባር ሳይተገበር ቀርቷል።
እናም የፕሬስ ነጻነት በሀገራችን መጥፎ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር ማለት ይቻላል። በተለይም በመንግስት በኩል ያሉ ችግሮችን የሚያነሱ ሚዲያዎች በከፍተኛ ጫና ስር ሆነው ነበር ስራቸውን የሚሰሩት።
አንዳንዶቹ እንደውም ሥራቸውን እስከማቆም ደርሰዋል፤ የታሰሩና የተሰደዱ የተለያዩ እንግልቶች የደረሰባቸው የሙያው ባለቤቶችም ነበሩ። ዌብሳይቶችና ማህበራዊ ሚዲያዎችም መዘጋት ጀመሩ።
በዚህም ምክንያት ተፈጥረው የነበሩት ሚዲያዎች ቁጥራቸው ተመናምኖ ወደ መጥፋቱ ደርሰዋል። በተለይ የህዝብን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስተያየት እንዲሁም ያልተሰሙ ድምፆችን ለማሰማት የሚሞክሩ ሚዲያዎች የመንግስት ጠላት ተደርገው ይፈረጁ ነበር።
ሌላው ትልቁ ጉዳይ መረጃ የማግኘት ነጻነት ያለመከበሩ ነው። ለምሳሌ የብሮድካስት ባለስልጣን ባወጣው ደንብ አንድ የሚዲያ ተቋም መረጃ ፍለጋ ወደ አንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ሲሄድ በምን ያህል ቀነ ገደብ ማግኘት እንደሚገባው አስቀምጧል።
የተቀመጠው የጊዜ ገደብ አሰልቺ መሆኑ ሳያንስ በደንቡ መሰረት እንኳን መረጃውን ለማግኘት የሚቻል አይደለም። ስለዚህ መረጃ የማግኘት ነጻነት በሚል በአዋጅ ቁጥር 590/2000 የተደነገገው ህግ ተፈጻሚ ካልሆኑት ህጎች አንዱ ነው። እናም ሚዲያዎች በአፈና ውስጥ ነበሩ ማለት ይቻላል።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መረጃን ለይቶ የመስጠት ሁኔታም ይስተዋል ነበር። በይበልጥ ለመንግስት ቅርበት ያላቸው ሚዲያዎች መረጃን የማግኘት ዕድል ነበራቸው። ከመንግስት ሚዲያዎች ውጭም የሚመረጡ ሚዲያዎች ነበሩ።
እነዚህ የሚመረጡ ሚዲያዎች ደግሞ ታማኝና የመንግስት ቀኝ እጅ የተባሉ ናቸው። እንደሚዲያ ግን ሁሉም የሚያገለግሉት ህዝብንና ሀገርን እስከሆነ ድረስ እንዲህ አይነት ልዩነት መፍጠሩ ተገቢ አልነበረም። ስለዚህ መንግስት የሚዲያ ነጻነት ህጉን ለይስሙላ አስቀመጠው እንጂ አልተገበረውም ።
አሁን ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በሚዲያው ዘርፍ ትልቅ መሻሻል ታይቷል። በአሸባሪነት የተፈረጁ የተለያዩ ሚዲያዎችና የሚዲያ ስራ አስፈጻሚዎች ነጻ መውጣት ችለዋል። ወደ ሁለት መቶ የሚደርሱ ተዘግተው የነበሩ ዌብ ሳይቶች ተከፍተዋል። ብዙ ጋዜጠኞች ከእስር ተፈተዋል። ከስደትም ተመልሰዋል። አሁን ሚዲያዎች በነጻነት ሲሰሩ እያየን ነው።
እንግዲህ የሚዲያ ነጻነት ማለት የራስን ነጻነት ብቻ መጠበቅ አይደለም። ኃላፊነትን መሸከምን ይጠይቃል፣ በተጠያቂነት መስራትን ይመለከታል፣ ህግን አክብሮ መስራትን ይጠይቃል። በተለይ አሁን አሁን ሚዲያዎች የተሰጣቸውን ነጻነት በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም ጥፋቶችን ሲያጠፉ እናያለን። ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፣ ሰውን ስሜታዊ የሚያደርጉና ለጥፋት የሚያነሳሱ መልዕክቶች ሲተላለፉ እናያለን። ስለዚህ ሚዲያዎች የተሰጣቸውን ነጻነት በትክክለኛ መንገድ መተርጎም ይጠበቅባቸዋል።
መንግስትም ለሚዲያው ልጓም ሊያበጅለት ይገባል። ሚዲያዎች ነጻነት አላቸው በሚል ዝም ተብለው ሊለቀቁ አይገባም። ገደብ ሊኖራቸው ይገባል። አላማችን ይችን ሀገር ወደ ከፍታ ማሸጋገር እስከሆነ ድረስ መረን የወጡና በሀገር እና በህዝብ ላይ አደጋ የሚፈጥሩ ሚዲያዎችን መንግስት ሀይ ማለት ይኖርበታል።
መንግስትም በራሱ በኩል የሚጠበቅበትን መረጃ ለሚዲያዎች መስጠት ይኖርበታል። የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለባለሙያዎች በመስጠት የአቅም ውስንነቶችን በማገዝ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የሚዲያ ነጻነት ህግን አክብሮ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ አለበት።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2011