‹‹በገና›› የአማርኛ ቃል ነው። በግዕዝ አጠራሩ ደግሞ ‹‹አንዚራ›› የሚል ስያሜ ተችሮታል። የቤተክርስቲያን ሊቃውንት እንደሚሉት ‹‹በገና›› ማለት ‹‹በገነ›› ከሚለው ግስ የተወረሰ ቃል ነው። በሌላ መልኩ ‹‹ወግሥ ወ መዝገበ ቃላት ሐዲስ ›› በሚለው የአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ላይ ‹‹በገና›› ቃሉን በማጥበቅና በማላላት ሊሰጥ የሚችለው ትርጓሜ እንዲህ ተቀምጧል።
‹‹በገና›› በዕብራይስጥኛ ‹‹ናጌን›› በመባል ይጠራል። የዚህ ቃል ትርጓሜም ነዘረ፣ መታ፣ ደረደረ፣ እንደማለት ነው። በሌላ መልኩ ይኸው ቃል ጠብቆ ሲነበብ ነደደ፣ ተቆጣ የሚል ፍቺን ይይዛል። በአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ መጽሐፍ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው በገና በቁሙ ሲመነዘር መዝሙር እንደማለት ይሆናል።
በአባ ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር ትግርኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ ደግሞ በገናን በጥሬው እንደነበረ ሆኖ ‹‹በገና›› ተብሎ ተተርጉሟል። የከሳቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ የሰፈረው እውነታም የበገናን ትርጓሜ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል።
‹‹በገና በአሥር አውታር ጅማት በገናን ሰራ፣ ቃኘ፣ ደረደረ፣ ድምጽን እያጣራ፣ እያጣቀሰ፣ እየነዘረ፣ በገናን በገነ ማለት ነው። ‹‹በገነኛ ›› ማለት ደግሞ በገናውን የሚመታ፣ ዕውቀቱ ያለው፣ ደርዳሪውን ሰው ያመለክታል። በሌላ መልኩ በገነ ማለት አደረቀ፣ አቃጠለ፣ አነደደ የሚል ሀሳብን ይይዛል።
የዚህ ቃል ትርጓሜም ከበገና አካላዊ አሰራር ጋር የሚቀናጅ ነው። በገና ደረቅ በሆኑ ግብአቶች እንጨትና ቆዳ እንዲሁም በደረቅ ጅማት ይሰራልና……
ዕውቁ የበገና ደርዳሪ ዓለሙ አጋ እንደሚሉት ደግሞ ‹‹በገና›› የሚለው ቃል ‹‹ገና›› ከተሰኘው የእየሱስ ክርስቶስ ልደት ጋር የሚዛመድ ነው። ይህም ከመወለዱ ጋር ተያይዞ በዕለቱ ምስጋና የተደረደረበት መሳሪያ መሆኑን ያስታውሳል። የበገና ሌላው ፍቺ ‹‹ደረደረ›› እንደ ማለት ነው። በቃሉ ውስጥም ድርደራን፣ ምስጋናን ዝማሬን ይዋህዳል።
ብዙዎች በጥንት ጊዜ በገና ለነገስታት ፍላጎት ብቻ ይውል እንደነበር ያስባሉ። ይሁን እንጂ በገና ከፈጣሪ ለሰው ልጆች የተሰጠና ቅዱስ የሆነ የማመስገኛ ጥበብ መሆኑን በርካታ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ።
በገና በተወጠሩ ክሮች የሚሰራ የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያ ነው። ቁመቱ የረዘመ፣ ገበታው የሰፋ ቁመናም አለው። የላይኛው የአናቱ ክፍል ‹‹ቀንበር›› ወይም ‹‹ጋድም›› ይባላል። በዚህ ክፍል ላይ ያማሩ ጌጦችና መቃኛው ይቀመጣሉ። በቀኝና ግራ ምሰሶዎቹ የተወጠሩት ክሮች ከድምጽ ሳጥኑ /ገበቴው/ ጋር የተዛመዱ ናቸው።
በገና አስር የክር አውታሮችን የያዘ ነው። ብርኩማ፣ እንዚራ፣ መወጠሪያና መምቻ/ ድህንጻ / የተባሉት ክፍሎች በገናን ሙሉ ለማድረግ የሚያግዙ አካል ናቸው።
በገና የሚደረደረው በቤተክርስቲያን እንደመሆኑ የአፈጣጠሩ ይዘት በመንፈሳዊነት ምሳሌ ይመነዘራል። የሐይማኖት ሊቃውንት እንደሚሉት ከላይ ያለው ቀንበር /ጋድም/ እግዚአብሔር የበላይ መሆኑን አመላካች ነው። በቀንበሮቹ ላይ አጊጠው የተቀመጡት መስቀሎችም እግዚአብሔር በመስቀል ተሰቅሎ ፍቅሩን ስለመግለጹ ጠቋሚ ናቸው።
በስተቀኝ በኩል ያለው ምሰሶ እግዚአብሔርን የመውደድን ማሳያና የብሉይ ኪዳን ተምሳሌት ነው። በግራ በኩል ያለው ምሰሶም ሰውን የመውደድና የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ተደርጎ ይወሰዳል። ዝቅ ብሎ ያለው የገበቴው አካልም ቅድስት ድንግል ማርያምን ይወክላል።
አውታሩ ሲመታ ድምጹ የሚወጣው ከገበቴው ክፍል ነው። ይህም ወልድ እየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ቅድስት ማርያም የመወለዱን እውነታ ይጠቁማል። ይህ ገበቴ በሁሉም አቅጣጫ አንዳች ቀዳዳ የሌለው ፍጹም ድፍን መሆኑ ይታያል። ይህም የማርያምን የድንግልና ምስጥር ይጠቁማል።
ብርኩማው የሲና ተራራን አመላካች ምሳሌ ነው። ሙሴ በዚህ ተራራ አስርቱን ትዕዛዛት ከአምላኩ መቀበሉን ልብ ይላል። እግዚአብሔርና የሰው ልጅም ልክ እንደመቃኘው በአምላኩ መንፈስ ሲቃኝ ጣዕም ያለው ሕይወት ይኖረዋል በሚል እሳቤ የበገናውን ጥዑም ዜማ ያስታውሳል።
በበገናው የታችኛው ክፍል የሚገኘው መወጠሪያም የሰው ልጅንና የምድርን ገጽታ የሚወክል ምሳሌን ይዟል። የሰው ልጅ የሁሉም ፍጥረታት የበላይ የሆነውን እግዚአብሔርን ሊያከብር የሚችለው በአስርቱ ትዕዛዛት በመመራት ነው። ይህም ከበገናው አናት ጀምሮ በታሰሩት አስር አውታሮች ተምሳሌትነቱ ተጠቅሷል።
በገና የጸሎትና የምስጋና ዜማ መሳሪያ ነው። መሳሪያውን ተቀምጦም ሆኖ ቆሞ መደርደር ይቻላል። እንደ ቅዱስ መጽሐፍ እውነታ በገናን ለመጀመሪያ ጊዜ የደረደሩት የላሜህ ልጅ የዩባል /ኢዮቤል/ ልጆች ነበሩ። አይነስውሩ አያታቸው ላሜህ በበረሀ ይጓዝ በነበረ ጊዜ አባቱ ቃኤል ከእሱ ተለይቶ በዱር በጫካው ይንቀዠቀዥ ነበር።
ላሜህ በመንገዱ ቅጠሎች የተንኮሻኮሹ፣ ቢመስለው አውሬ እንደመጣባቸው መስሎ ተሰማው። ወዲያው ስጋቱን መንገድ ይመራው ለነበረ ሰው ተናገረ። በዚህ ብቻ ዝም አላለም። ድንጋይ እንዲያቀብለው ጠየቀው።
የዓይኑ መሪ ወዲያው የጠየቀውን ድንጋይ ፈጥኖ ከእጁ አኖረለት። ላሜህ አልዘገየም። ድምጽ ወደሰማበት አቅጣጫ ድንጋዩን አርቆ ወረወረው። የተወረወረው ድንጋይ የአባቱን የቃየንን ግንባር መታና ገደለው። አባትም በልጁ ላሜህ እጅ ለሞት በቃ።
ላሜህ በአባቱ ላይ የሆነውን ሁሉ ባወቀ ጊዜ በመሪር ሀዘን ተደፍቶ አለቀሰ። አስቀድሞ አቤል በቀናተኛው ወንድሙ ቃየል ተገድሏል። የሚያውቁ ልጆቹም የቀደመውን ታሪክ አስታውሰው በእጅጉ አዘኑ። በቤተሰቡ ዘንድ የመረረው ለቅሶም ከደረቀ እንጨት በገና አሰርቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀዘን ዜማ አስቆዘማቸው። የሀዘን ዜማው በበገና ድርደራ የታጀበ ነበር።
በኢትዮጵያ የበገናን አጀማመር በተመለከተ ትክክለኛው መረጃ አልተቀመጠም። ይሁንና የጅማሬው ምንጭ ከንጉስ ሰለሞንና ከኢትዮጵያዊቷ ንግስት ማክዳ /ዕሌኒ/ ልጅ ከቀዳማዊ ምኒልክ ታሪክ ጋር እንደየሚያያዝ ይገመታል። ቀዳማዊ ምኒልክ በአገረ አስራኤል ቆይቶ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰ ጊዜ የበገና መሳሪያ አብሮት እንደገባ ይታመናልና።
ኢትዮጵያዊው ካህን ማህሌተ- ቅዱስ ያሬድ በአምስቱ ጽዋዕተ ዜማዎቹ ተለይቶ ይታወቃል። ድጓ፣ ጾመድጓ ፣ ዝማሬ፣ መዋዕሰት፣ ምዕራፍ እመመለሰ በተባሉት ዜማዎቹ በዓለም የዜማ ታሪክ ቀዳሚውን ድርሻ እንዲይዝም ሆኗል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም፣ በህገ ልቦናና በህገ ኦሪት እግዚአብሔር ሲመሰገንበት የኖረውን የዜማ ዕቃዎችና ከቅዱስ ያሬድና ሌሎች ሊቃውንት ከአዲስ ኪዳን ጀምሮ የተላለፈውን የዜማ ሀብት በክብር ይዛ አቆይታለች። በብሉይ ኪዳን የዜማ መገልገያ ከነበሩት መሳሪያዎች መካከል አንዱ በገና እንደነበርም አበው ሊቃውንት ያስረዳሉ።
በገና እንደሌሎች የዜማ መሳሪያዎች ጊዜና ቦታ ተወስኖለት በአግባቡ የተጠበቀ አልነበረምና በአንድ ወቅት ‹‹በመሞት›› ላይ ያለ የሚል ስያሜ ተችሮት ነበር። ይሁን እንጂ በሀገራችን ብቻ የሚገኝ የዓለማችን ቅርስ ለመሆን ችሏል።
የበገና ጥንታዊ ዳራ ሲመረመር ታሪኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ሲጠቀስ መቆየቱን ማረጋገጥ ይቻላል። በገና ለፈውስ፣ ለድህነት፣ ለማህበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎቶች ሲውል ቆይቷል። ይህ የዜማ መሳሪያ ከሰው ልጆች ጋር ረጅም ዓመታትን የዘለቀ ሲሆን ሰዎች ደስታና ሀዘናቸውን የሚገልጹበት ዘመን ተሻጋሪ መሳሪያ ነው።
በዘመነ ኦሪት በገና ከእንቢልታ ተቀናጅቶ የቃል ኪዳኑን ታቦት ያጅብ ነበር። እስራኤላውያንም ጠላቶቻቸውን ድል በነሱ ጊዜ ለምስጋናና ውዳሴ ተጠቅመውበታል። ሐይማኖታዊ አስተምህሮቱ እንደሚጠቁመው በገና ፈጣሪን የማመስገኛ የዜማ መሳሪያ ነው።
በገና የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ከአቢዳር ቤት በሚመጣበት ጊዜ፣ በዳዊት ከተማ ገብቶ በድንኳን በኖረበት ወቅት፣ ንጉስ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሰርቶ ባጠናቀቀበት ዘመንና እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ድል በነሱ ጊዜ ሁሉ በአገልግሎት ላይ የነበረ የዜማ መሳሪያ ነው። ልበ -አምላክ ዳዊት በእግዚአብሔር ከተሰጠው ሰባት አይነት ሀብቶች መካከልም አንዱ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሷል።
በሀገራችንም ከጥንት ጀምሮ በቤተመንግስት አካባቢ ንጉሳውያንና መኳንንቱ፣ በቤተክህነት ዘንድም ካህናትና ቀሳውስት ለመንፈሳዊ አገልግሎት ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ብዙዎች እንደሚሉት የበገና ዜማ የሚደርሰው ለጆሮ ብቻ አይደለም። ድምጹ ውስጥን የማረስረስ፣ መንፈስን የመመሰጥ ታላቅ ኃይል አለው።
‹‹አንገረ ፈላስፋ› የተባለው መጽሐፍ ስለበገና ዜማ ኃያልነት እንዲህ ሲል አስፍሯል። ‹‹በገና በተደረደረ ጊዜ አራቱ ባህርያተ ሥጋ ለሶስቱ ባህርያተ ነፍስ ይገዛሉ›› ሊቃውንት እንደሚሉትም ክፉ ድርጊቶች ሁሉ በሰው ልጆች ስጋዊ አካል ላይ የሰለጠኑ ናቸው። ከልብ ዘልቆ የሚገባው የበገና ዜማ ግን የስጋ ፈተናዎችን የማረጋጋት ኃይል አለው።
ንጉስ ሳኦል መንፈሱ በታወከ ጊዜ ቅዱስ ዳዊት በገናውን እየደረደረ በንጉሱ ውስጠት ያደረውን ክፉ መንፈስ እንዳወጣለት ይታወቃል።
ስለበገና ምንነት ቅርበቱ ያላቸው ሰዎች እንደሚሉት ደግሞ በገና ሲደረደር መንፈስ ይማረካል፣ ክፉ ስሜት ይሰደዳል፤ ተቅበዝባዥ ኃይል ይሰክናል። ይህ እውነታም የበገና ባህሪያት ዋና መገለጫ ሆኖ አሁን ድረስ በመልካም ተጽእኖው እንዲዘልቅ አስችሎታል።
መምህር ሲሳይ ደምሴ ገብረጻዲቅ የሲሳይ በገናና የዜማ መሳሪያዎች ተቋም ስራ አስኪያጅ ናቸው። በአንድ ወቅት ለአንድ ሬዲዮ ጣቢያ በሰጡት አስተያየት ስለበገና ኃያልነት እንዲህ ብለዋል። ‹‹ ሀብተ በገና እንጨት ጠርቦ፣ ቁርበት ገልቦ፣ ጅማት ወጥሮ መደርደር ሲሆን ሀብተ ፈውስ ደግሞ በገናውን እየደረደሩ ድውይን መፈውስ ነው ››
ንጉስ ዳዊት ከብላቴናነቱ ጀምሮ በአምላኩ የተወደደና የተመረጠ ነበር። ዳዊት በገናን መልካም አድርጎ የመደርደሩ እውነትም በሰው ዘንድ ጭምር እንዲወደድ አድርጎታል። ንጉስ ሳኦልን ክፉ መንፈስ ባስጨነቀው ጊዜ የሳኦል ባሪያዎች በገናን በመደርደር ከክፉ መንፈስ መላቀቅ እንደሚቻል ያምኑ ነበር። ይህን ሀቅም ለንጉሱ በማሳመን በበገና እንዲፈወስና ውስጠቱ በበጎ እንዲማረክ ይመክሩት ነበር።
በገና ከአምስት ሺህ ስምንት መቶ ዓመት ዕድሜ በላይ እንዳስቆጠረ ይነገርለታል። በነዚህ ዘመናት ሁሉ ያገለግል የነበረው ፈጣሪን ለማመስገኛነት ብቻ ነው። በቤተክህነትና ስልጣን ባላቸው የቤተመንግስት ሰዎች እጅ ተከብሮ የመቀመጡ ሚስጥርም አብሮት የቆየው ክብርና ታላቅነት ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የጎንደሯን እቴጌ ምንትዋብን ጨምሮ አጼ ቴዎድሮስና አጼ ዮሀንስ አጼ ምኒልክና ፣ እቴጌ ጣይቱ ፣ እንዲሁም የአጼ ኃይለስላሴ አባት የነበሩት ራስ መኮንን የታወቁ በገና ደርዳሪዎች እንደነበሩ ይነገራል። በተለይ አጼ ቴዎድሮስ የዓለም ከንቱነት ሲሰማቸው፣ እቴጌ ተዋበችን ሲያስታውሱና በሀዘን ሲቆዝሙ ማረፊያቸው በገና እንደነበር ይነገርላቸዋል።
የበገና ግጥሞች የተለዩ ናቸው። በሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎች የተለመዱ አይነት ዜማ የላቸውም። ስንኞቹ ታስበውባቸው የሚጻፉና አእምሮ ላይ የተለየ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ናቸው። በገና በሚደረደር ጊዜ ‹‹ውስጠት ይቀየራል፣ መንፈስ ይረጋጋል፤ ለጸሎት ያበረታል›› የሚሉ ብዙ ናቸው።
በገና በአብዛኛው ጾምና የንስሀ ጸሎት በሚያዝበት ጊዜ የሚደረደር ኃያል መሳሪያ ነው። ታቦታትን ለማጀብም ጭምር ያገለግላል። በተለይ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ታላቁ ዓቢይ ጾም /ሁዳዴ/ ገብቶ ፋሲካ እስኪሆን ድረስ የበገና ድርደራዎች ጎልተው ይሰማሉ።
ብዙዎች እንደሚስማሙበት የበገና ድምጸት በተለየ ስሜት ውስጠትን ይቀይራል። መንፈስን ያድሳል። በርካቶች ለጾምና ጸሎት የሚጠቀሙበት፣ ከፈጣሪያቸው በተለየ የሚገናኙበት ኃያል የዜማ መሳሪያ ነው።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2015