አዲስ አበባ፡- የሱዳን ፖለቲከኞች የሀገራቸውን ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል።
በካይሮ ከትናንት በስቲያ በተካሄደ የአፍሪካ ህብረት የምክክር ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሱዳን የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት በሀገሪቱ የተፈጠረውን ወቅታዊ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ለዚህም ሁሉም የሀገሪቱ የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት በሰከነ መንገድ መወያየትና ልዩነታቸውን በመነጋገር መፍታት የሚገባቸው መሆኑን አሳስበዋል።
“ሱዳናውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በጥበብ እንደሚያልፉትና የአገራቸውን ሉዓላዊነትና ፖለቲካዊ ነጻነት እንደሚ ያስጠብቁ ኢትዮጵያ ሙሉ ዕምነት አላት” ያሉት
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት ከሚለው መርሆ ሳትወጣ ሀገሪቱ ያጋጠማትን ችግር ለመፍታት የምትችለውን ሁሉ ድጋፍ እንደምታደርግና በማንኛውም ጊዜ ከሱዳን ህዝብ ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
የሱዳንን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት የአፍሪካ ህብረት እያደረገ ያለውን ጥረት ኢትዮጵያ በበጎ ዓይን የምትመለከተውና የምትደግፈው መሆኗንም ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀ መንበርና የህብረቱ ሙሉ አባል እንደመሆኗ መጠን በሱዳን የተፈጠረው ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ እንዲያገኝና የሀገሪቱ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርብና በትብብር ለመስራት ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ ናት” ብለዋል።
በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር የግብጹ ፕሬዚዳንት አብድልፋታ አልሲሲ ጠሪነት በካይሮ የተካሄደው የአፍሪካ ህብረት አስቸኳይ ጉባኤ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህመትን ጨምሮ የኢትዮጵያ፣ የጅቡቲ፣ የኬንያ፣ የሶማሊያ፣ የሩዋንዳና የደቡብ አፍሪካ መሪዎች ታድመውበታል።
በዚህም ህብረቱ ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ በአሁኑ ሰዓት አገሪቱን እየመራት ያለው የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት በሦስት ወራት ውስጥ ስልጣኑን ለሲቪላዊ መንግስት እንዲያስረክብ ውሳኔ አስተላልፏል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2011
በ ይበል ካሳ