አዲስ አበባ፡- የ54 ዓመት ጎልማሳው አቶ ግርማ ጎዳና የሰባት ዓመት ልጅ እያሉ ከአባታቸው ጋር ወደ ምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ እንደሄዱና እዚያው አድገው አግብተው 12 ልጆችን አፍርተው ለወግ ማዕረግ ማብቃታቸውን ይናገራሉ።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 2 ቀን 2010 ዓ.ም በአካባቢው በተቀሰቀሰው ግጭት ወንድማቸው እንደተገደለባቸው የሚናገሩት አቶ ግርማ ‹‹ከወንድማቸው ሞት በኋላ ጨርቄን ማቄን ሳልል ወደ ጌዲኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ ለመሸሽ ተገድጃለሁ›› ይላሉ።
ለሃይማኖታዊና ለባህላዊ በዓላት ልዩ ቦታ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ግርማ በዓላትን ደማቅ በሆነ ሁኔታ የማክበር ልምድ እንደነበራቸው ይናገራሉ። በተለይም ፋሲካ በተለየ ሁኔታ ከሚያከብሩት በዓላት አንዱ መሆኑን ያስታውሳሉ።
ከጎረቤት ጋር ቅርጫ በመግባት፣ ዶሮ በማረድና ሌሎች የበዓል ግብዓቶችን በማሟላት በደማቅ ሁኔታ ያከብራሉ። በበዓላት ከሚበላውና ከሚጠ ጣው ባሻገር የተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ የቤተሰብ አባላት ጋር የሚገናኙበት፤ ከጎረቤት ጋር ያለው መቀራረብ የሚጠብቅበት ነው፤ ከአባትና እናት ምርቃት የሚቀበሉበት፤ በቤተክርስቲያን በመሄድ ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት እንደነበር ይናገራሉ።
እንደ አቶ ግርማ ማብራረሪያ አምና ከቀዬያቸው ከተፈናቀሉ ወዲህ ግን በዓላት የሚደሰቱበት ሳይሆን በድሮ ትዝታ ብቻ የሚቆዝሙበት ሆኗል። ልጆቻቸው ተበታትነዋል። እጅግ ይወዷቸው የነበሩ ጎረቤቶች ግማሾቹ ወደ ጉጂ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ግማሾቹ ደግሞ ጌዲኦ ዞን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ ተጠልለዋል።
ቤተሰብ የ2011 ዓ.ም ገና ሰሞን በሁለቱ ህዝቦች መካከል ዕርቅ ከወረደ በኋላ ገናን በቤታቸው ለማሳላፍ ወደ ቀርጫ ሄደዋል። ‹‹ይሁን እንጂ በታጠቀው ሃይልና በተደራጁ ወጣቶች ማስፈራሪያ ዳግም ወደ ይርጋጨፌ ለመመለስ ተገደናል›› ይላሉ።
በዘመድ ቤት ውስጥ ከልጆቻቸው ጋር ወራትን ካሳለፉ በኋላ ከዘመድ ቤት በመውጣት ከሌሎች ተፈናቃዮች ጋር በይርጋጨፌ ስታዲየም ውስጥ መኖር ከጀመሩ ወራት እንደተቆጠሩ የሚናገሩት አቶ ግርማ ለአሁኑ ፋሲካ ምንም ያዘጋጁት ነገር እንደሌለ ይናገራሉ። ‹‹ከፈጣሪ ውጪ ምንም ተስፋ የለንም›› የሚሉት አቶ ግርማ ‹‹ፈጣሪ ተዓምር እንዲሰራ እየለመንን ነው›› ብለዋል።
‹‹በአካባቢው ከባድ ዝናብ እየዘነበ ነው። የተጠለልንበት ስታዲየም በአሁኑ ወቅት ጎርፍና ጭቃ በመሆኑ በዓሉን በጎርፍና በጭቃ ውስጥ ሆነን በከባድ ሁኔታ ውስጥ እየኖርን ነው›› ያሉት አቶ ግርማ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከዚህ በፊት ያደርጉ የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ወደ ቀዬያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻችም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፈጣሪውን እንዲለምን ጠይቀዋል። መንግስት ደግሞ የህግ የበላይነት በማስከበር ወደ ነበሩበት ሁኔታ የሚመለሱበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።
የዞኑ ህዝብና መንግስት በበኩሉ ተፈናቃዮቹ ፋሲካን ተደስተው እንዲያሳልፉ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። የጌዲኦ ተፈናቃዮች የሎጂስቲክስ አቅርቦት ፍላጎት ልየታና ሀብት አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰላማዊት አየለ እንደተናገረችው መላው ኢትዮጵያውያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በጌዲኦ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ አድርጓል፤ አሁንም ድጋፉ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የፋሲካ በዓልን በተመለከተ ባለሀብቶችና ወጣቶች ተባብረው ለበዓል የሚሆን ግብዓት የማሰባሰብ ስራ እየሰሩ ነው። የዞኑ ወጣቶች አደረጃጀቶችንና ታዋቂ ግለሰቦች፣ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በማስተባበር ለበዓል የሚሆኑ ግብዓቶችን በማሰባሰብ የበዓል ዕለት ተፈናቃዮቹ ባሉባቸው ካምፖች አካባቢ በዓሉን በጋራ ለማክበር ጥረት ላይ ናቸው።
መላው የአካባቢው ነዋሪዎች ለድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እየሰጠ ነው ያለችው ሰላማዊት በተለይም አንዳንድ ባለሀብቶች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ገልፃለች። እስከ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ በማድረግ ተፈናቃዮቹ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ መኖራቸውን አብራርታለች።
የጌዲኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተካልኝ ታደሰ እንዳብራሩት የዞኑ ህዝብ የተለያዩ ድጋፎችን ከማድረግ አልፎ በቤቱ በማስጠለል ጭምር የሚጠበቅበትን ሲወጣ ቆይቷል። አሁንም ከመንግስት ጋር በመሆን ድጋፉን አጠናክሮ ቀጥሏል። ተፈናቃዮቹ የፋሲካ በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ የዞኑ ህዝብ ዝግጅት እያደረገ ነው።
ከመንግስት የሚቀርበው እርዳታ በተለያዩ የቢሮክራሲ ችግሮችና በተፈናቃዮች ቁጥር መብዛት ምክንያት በጊዜ መቅረብ ባለመቻሉ የዞኑ መንግስት ሰሞኑን 1ሺህ 200 ኩንታል እህል እንዲቀርብ ተደርጓል ያሉት አቶ ተካልኝ፤ ይህም ተፈናቃዮቹ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ለበዓሉ ወጣቶች ያሰባሰቡት ድጋፍ መጠን ከታወቀ በኋላ በወጣቶች የተሰባሰበው ግብዓት ለተፈናቃዮች የማይበቃ ከሆነ የዞኑ መንግስት በጀት መድቦ ግብዓት ለማሟላት ዝግጅት ላይ መሆኑንም አብራርተዋል።
በዕለቱ በገደብ አካባቢ ባሉ ዋና ዋና ካምፖች የመንግስት አካላት፣ ወጣቶች፣ ሌሎች ፈቃደኛ የሆኑ የማህበረሰብ አካላት በተገኙበት በጋራ ይከበራል ብለዋል። የዞኑ ህዝብና መንግስት ለበዓሉ ድጋፍ በማድረግ በዓሉን ከተፈናቃዮች ጋር ለማሳለፍ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ለማሳየት ከትናንት ጀምሮ በርካቶች ተፈናቃዮች ወዳሉበት አካባቢ በመሄድ እየጎበኙ ነው።
የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፕሬዝዳንት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ዛሬ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ እንዳብራራው ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተፈናቅለው በጌዲኦ ዞን በተለያየዩ መጠለያዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ ነበሩበት አካባቢ ለመመለስ የኦሮሚያና የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች ከተፈናቃዮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቋል።
የሁለቱ ክልሎች ምክትል ፕሬዝዳንቶች ተፈናቃዮቹን ወደ ቀዬያቸው መልሶ ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስቷል። አፈናቃዮችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመራሮቹ አብራርተዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮችም በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ጥረት እየተደረገ ነው። የኦሮሚያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገረመው ኦሊቃ እንደተናገሩት ክልሉ በርካታ ተፈናቃዮችን አቅፎ ከያዙ ክልሎች አንዱ ነው። ለተፈናቃዮቹ መንግስት እርዳታ ሲያቀርብ ቆይቷል። በክልሉ ከሚገኙት ተፈናቃዮች ውስጥ በርካቶች ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ የተደረገ ቢሆንም አሁንም በርካቶች ወደ ቀዬያቸው አልተመለሱም።
በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮች በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን የፋሲካ በዓል በጥሩ ሁኔታ እንዲያሳልፉ ጥረት እየተደረገ ነው። ምንም አማራጭ የሌላቸውና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች ቀለብ ሳይደርሳቸው በዓሉን እንዳያሳልፉ ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው። የክልሉ መንግስት በየወሩ ለተፈናቃዮች ያቀርብ የነበረው ቀለብ ከበዓሉ ቀደም ብሎ ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ ነው።
በተለይም ከማዕከል ራቅ ባሉና ለትራንስፖርት አመቺ ባልሆኑ ቡኖ በደሌና ሆሮ ጉዱሩ አካባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ አኳኋን የሁለትና የሶስት ወራት ቀለብ ቀደም ብሎ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው።
ከተለያዩ አካባቢዎች ህዝቡ ተፈናቅሎ ችግር ውስጥ ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ በነበሩ በዓላት የክልሉ ህዝብ ተፈናቃዮችን ውጪ ትቶ በዓላትን አሳልፎ አያውቅም ያሉት አቶ ገረመው፤ በበዓላት ወቅት የክልሉ ህዝብ ከተፈናቃዮች ጋር ያለውን ተካፍሎ አብሮ በመብላትና በመጠጣት በዓሉን ሲያሳልፍ እንደነበር አንስተዋል። ሰሞኑን የሚከበረውን የፋሲካ በዓልም አብሮ ለማክበርም ዝግጅት ላይ ነው። ከህዝቡ በተጨማሪ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ባለሀብቶች ድጋፍ በማድረግ በዓላትን በደስታ እንዲያሳልፉ ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁንም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን የፋሲካ በዓል በደስታ እንዲያሳልፉ እየተደረገ ይገኛል።
ሰሞኑን የሚከበረውን የፋሲካ በዓልም አብሮ ለማክበርም ዝግጅት ላይ ነው። ከህዝቡ በተጨማሪ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ባለሀብቶች ድጋፍ በማድረግ በዓላትን በደስታ እንዲያሳልፉ ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁንም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን የፋሲካ በዓል በደስታ እንዲያሳልፉ እየተደረገ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2011
በ መላኩ ኤሮሴ