አዲስ አበባ፡- ደቡብ ምስራቅ አውሮፓን እስያን አፍሪካን ያካትታል የቻይናው ቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት ማዕቀፍ። በዚህ የፕሮጀክት ማዕቀፍ ውስጥ ከ60 በላይ የሚደርሱ አገራት ተሳታፊ ናቸው። እነዚህ አገራት ጠቅላላ አገራዊ ምርታቸው የዓለም ኢኮኖሚን ሲሶ ያህሉን የሚያንቀሳቅሱ ናቸው። በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ከተካተቱት አገራት ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ናት።
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቤጂንግ የመገኘታቸው ምስጢር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ቆይታቸው የተለያዩ የጎንዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል። በዚህም ቆይታቸው ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ተገናኝተው በሁለቱ አገራት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ስኬታማ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱም ሺ ጂንፒንግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን አመራርና ያለፈውን አንድ ዓመት የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት
እንደሚያደንቁ የገለፁ ሲሆን፣ ቻይና ለኢትዮጵያ ዕድገት ትልቅ ቦታ ትሰጣለች ማለታቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከስፍራው ዘግቧል።
ፕሬዚዳንቱ በውይይቱ ወቅትም ኢትዮጵያ እስከ ፈረንጆች 2018 መጨረሻ ድረስ የተጠራቀመባትን የብድር ወለድ ሙሉ በሙሉ እንደተሠረዘላት ዘገባው አስታውቋል።
እንዲሁም የቻይና መንግስት የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክትን ጠቀሜታ ይረዳል ያሉት ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መንግሥታቸው እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የስትራቴጂ አጋርነት እንደምታጠናክር ገልፀዋል።
እንዲሁም እንደ አዲስ ጅቡቲ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ያሉ ዕዳዎችን ለመከለስ የሚረዱ ወሳኝ እንቅስቃሴዎችን ለመተግበር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ነው የገለፁት።
የባቡር ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ተሳታፊ የሆነችበት የቤልት ኤንድ ሮድ ማዕቀፍ ቀዳሚ ውጤት መሆኑ ተጠቁሟል።
ከዚህ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቻይና በአደገኛ እፅ ዝውውር ተጠርጥራ በእስር ላይ የምትገኘው ኢንጂነር ናዝራዊት አበራ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ለፕሬዚዳንቱ አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈ መሪዎቹ በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር በተለያዩ ዘርፎች አጠናክረው ለመቀጠል
ተስማምተዋል።
በተያያዘ ኢትዮጵያና የቻይና መንግስት ግሪድ ኩባንያ የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈራረሙ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከቻይና መንግስት ግሪድ ኩባንያ ሃላፊዎችን ጨምሮ ከተለያዩ ኩባንያዎች የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱን ተከትሎም ለኃይል ማሠራጫና ማከፋፈያ መሥመር ዝርጋታ የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት እንደተፈረመ ተነግሯል።
ይህ ፕሮጀክት ለ16 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኃይል አቅርቦት፣ ለሁለተኛው የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መሥመርና ለተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ የሚያስችል ነው።
ይኸውም ያልተቋረጠ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማቅረብ በተጨማሪ የሥራ እድል ለመፍጠርም እንደሚረዳ ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ከቻይና ሬልዌይ ኮርፖሬሽን (ሲአርሲሲ )ሃላፊዎች ጋር ባደረጉት ምክክር ከቀናት በኋላ በሚካሄደው የቤልት ኤንድ ሮድ ጉባኤና ተያይዘው በሚነሱ ፕሮጀክቶች ዙሪያ መክረዋል።
ኩባንያው ከሚያከናውናቸው ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መካከል የቤልት ኤንድ ሮድ ማእቀፍ አካል የሆነው የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት አንዱ ነው።
ኩባንያው በተጨማሪም በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታና በማእድን ዘርፍ በተለይም የነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ማውጣት ስራ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ይፋ ተደርጓል።
የሲ አር ሲ ሲ ኩባንያ በሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ እንደሚፈልግም አስታውቋል።
ከመሰረተ ልማት ግንባታ አንስቶ እስከ አምራች ዘርፍ ድረስ በተለያዩ ዘርፎች ላይ መሰማራት እንደሚፈልጉ የየኩባንዎቹ ኃላፊዎች ተናግረዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲኖሹር ከተባለው የቻይና የውጭ ንግድና የብድር ኢንሹራንስ ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
ኃላፊዎቹም በተለይም የቻይና መንግስት ግሪድ ኩባንያ ለኃይል ማመንጫ ለገባው የኢንቨስትመንት ስምምነት ትግበራ ሙሉ ትብብር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በፈረንጆቹ 2013 በቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አማካኝነት መተግበር የጀመረ ሲሆን፥ በ2017 የመጀመሪያ ፎረሙን አካሂዷል።
ኢኒሼቲቩ አፍሪካን ጨምሮ፣ ደቡብ ምስራቅ እስያን እና የአውሮፓ ሀገራትን ያካተተና ሀገራትን በመንገድና በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር አላማን ያነገበ መሆኑ ይነገራል።
ከ65 በላይ ሀገራትን ያቀፈው ይህ ኢኒሼቲቭ ለቀጠናዊ ትስስር ቅድሚያ በመስጠት የሚሰራም ነው።
የፖሊሲ፣ መሰረተ ልማት፣ ንግድ ፋይናንስ እና የህዝብ ለህዝብ ትብብርን መሰረት ያደረገ የትብብር ማዕቀፍም ነው። በዘንድሮው ፎረም ላይ ከ1 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈም በተለያዩ መስኮች የትብብር ስምምነቶች ይፈረማሉ ተብሎም ነው የሚጠበቀው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር