በፈረንጆቹ 1990 በአሥርት የሚቆጠሩ ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር ሞክረዋል። የዓለም አቀፍ የሽግግር ፍትሕ ማዕከል ያወጣው መረጃ እንደሚስረዳው የሽግግር ፍትሕ ያለፉ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና ቁርሾዎችን በሽግግር ፍትሕ ትግበራ፣ እውነትን ፍለጋ እና የእርቅ ጥረቶች፣ ካሳና የፀጥታና የፍትሕ ሥርዓትን ተሀድሶ ማስፈንን የሚያካትት ነው። ነገር ግን በፖለቲካ ፈቃደኝነት እና በመንግሥታዊ ተቋማት ድክመት ከላይ የተጠቀሱትን ጥረቶች የመናቅና የማቃለል ሁኔታዎች አሉ። ተጠያቂነት፣ እርቅንና ዘለቄታዊ ሰላም ለሚሹ አፍሪካውያን የሽግግር ፍትሕ ቃልኪዳን አንድም ሳይቀር መሟላት አለበት።
የአፍሪካ አገሮች ያሳለፉትን ጊዜያት ብናስስ ካጋጠማቸው ተግዳሮት መካከል ከነፃነትም ሆነ ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍፃሜ ውጤታማ የዴሞክራሲ ለውጥ ማምጣቱ ሰላም ወይም ብልፅግናን ማበርከት ነው። ይልቁኑም የጨካኝ ቅኝ ግዛት የበላይነት ከነፃነት በኋላ የተከተላቸው አምባገነንነት እና የቅርብ ጊዜያት ሰላማዊ የፖለቲካ ተቃዋሚ ተፅዕኖ ይገኙበታል። ውስብስብ ከሆኑት ክስተቶች መካከል ተከታታይነት ያላቸው ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዑጋንዳ፣ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ በፈረንጆቹ በ1990ዎቹ የነፃነት ተዋጊዎች የፈጠሩት ምናባዊ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ትግበራ መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ጥሰትን ‹‹ አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ›› እንደሚባለው ባለመከሰስ ፈጽመዋል።
በሴራሊዮን እና ላይቤሪያ የጦር አበጋዞችና በሙስና የተዘፈቁ ፕሬዚዳንቶች በበለፀገ የተፈጥሮ ሀብቶች በመፎካከር የአካባቢና የሲቪል ጦርነቶች አነሳስተዋል። በኬንያና ዚምባብዌም ፖለቲካዊ መረጋጋት ያለ በማስመሰል በተቃዋሚዎች አፈና ላይ ተመርኩዘው ሲንቀሳቀሱ ነበር። ይህም ወደ ብጥብጥ ሊያመራ ይችላል የሚሉ ቅሬታዎችን ለመደበቅ ነው። የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ፖሊሲ ለማደራጀት የሚያስችሉ የጥናት ሰነዶች ከሕገ መንግሥቱ፣ አገሪቱ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና አገራዊ ልምዶች በማካተት በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል በተዋቀረ አንድ የሽግግር ፍትሕ ባለሙያዎች ቡድን ተዘጋጅተው ውይይት ተካሂዶ ነበር። ይህም የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር የሚረዳ አንድ እርምጃ ወደፊት ነው ማለት ይቻላል።
ከፍትሕ ሚኒስቴር በብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮች ላይ የወጣ መረጃ እንደሚመለክተው፤ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን መተግበር፣ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ የሚኖረው አስተዋጽዖ እጅግ ከፍተኛ ነው። በአገራችን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ቁርሾዎች እንዲጠገኑ እና ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር እንዲሳካ ከተፈለገ፤ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንዲቻል የተሟላ የሽግግር ፍትሕ ሂደት መተግበር ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አገራዊ ዐውዱ ያመለክታል ሲል የፍትሕ ሚኒስቴር መግለጫ ያስረዳል።
ከመግለጫው ለመረዳት እንደሚቻለው የሽግግር ፍትሕን በአገራችን ለመተግበር ሁሉን አካታች ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት መርሆዎችንና ድንጋጌዎችን ያከበረ እንዲሁም የአገራችንን ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ዐውድን መሠረት ያደረገ የሽግግር ፍትሕ መቀመር እና በግልፅ የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲመራ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። ስለሆነም በአገራችን የነበሩትን ሙከራዎች ልምድና ትምህርት በመውሰድ፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማካተት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች ተለይተው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል። የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጭ ሰነዱ ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ የሽግግር ፍትሕ ታሪካዊ ዳራ እና አገራችን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ያለው አስፈላጊነት ፣ በአገራችን የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ ያሉት አማራጮች እና ምክረ ሀሳቦች፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ሊመራባቸው የሚገቡ መሠረታዊ መርሆዎች እና የማስተባበር እና የአደረጃጀት አማራጮች የተካተቱበት ነው።
በአጠቃላይ የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ ሰነዱን ለማዳበር በርካታ የውይይት መድረኮች በመላው አገሪቱ ማካሄድ እንደሚያስፈል ይጠቁማል። በዚህም የፌዴራል ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች የሲቪልና የፖለቲካ ማኅበረሰቦች የተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች እና የድጋፍ ሰጪ እና አጋር አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ርብርብና ተሳትፎ አስፈላጊነት እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን መግለጫው ያመለክታል። በኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሥርዓት እና ከቆየ የታሪክ ቁርሾና ትርክት በመነጨ ችግሮች ይታያሉ። በጋራ ታሪክ ላይ ለመስማማት አልተቻለም፤ ገሚሱ ጨቋኝ ከፊሉ ተጨቋኝ ሆኖ የቀረበ ትርክት ዜጎችን ሲያነታርክ ይታያል። የገዥው መደብ አባል/ብሔር የሆኑ ሁሉ ከበርቴ፣ ጨቋኝ አድርጎ የመሳል ሁኔታ አለ።
ቢያንስ ከገዥው ብሔር ጭሰኛ እንዳለ እንኳን ለመረዳት ፍቅር እስከ መቃብር ልቦለድ ማሳያ ነው። ደራሲው ሀዲስ ዓለማየሁም ደርግ ከገደላቸው ከ60ዎቹ ሚኒስትሮች ነፃ የወጡት በዚህ አገዛዙን በነቆረ ልቦለድ መሆኑ እሙን ነው። የፊውዳሉን ዘመን ጭቆና በልቦለድ ገመና አሳልፎ የሰጠ ስለሆነ። የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር ይፋ በተደረገው የፖሊሲ ግብዓት ማሰባሰቢያ ሰነድ ውስጥ፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ቁርሾዎችን አግባብነት ባለው ሁለንተናዊ፣ አሳታፊና በተቀናጀ መንገድ፣ ሳይፈቱ ሲንከባለሉ የመጡ የሚባሉ በደሎችና ቁርሾዎች እንዲጠገኑና ወደ ተሻለ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ካስፈለገ፣ የሽግግር ፍትሕ ማስፈን አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤትና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቀደም ሲል ያዘጋጁት የሽግግር ፍትሕን ለማዳበር ያቀረቡት የጋራ ምክረ ሃሳቦች እና ቁልፍ ግኝቶችን ያካተተ ሰነድ ላይ እንደተጠቀሰው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው የሲቪክ ማኅበራትን ጨምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት በሕዝባዊ ምክክር የሚገኙ ግብአቶችን መሠረት አድርጎ እና መደበኛ አገራዊ የፖሊሲ አወጣጥ ሂደቶችን ተከትሎ ሊዘጋጅ እንደሚገባ የሚጠቁም ነው።
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግ ሥትና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የተፈረመው እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲፀድቅ የሚደነግገውን ዘላቂ ሰላም እና ግጭት ማቆም የሰላም ስምምነት፤ የሽግግር ፍትሕ እንዲጸድቅ የሚረዳ ይመስላል። በወቅቱ በተካሔደው የሰላም ስምምነት አንቀፅ 10 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ ‹‹ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት እና ከአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ማዕቀፍ ጋር በተጣጣመ መልኩ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ እውነትን ለማውጣት፣ ማኅበረሰባዊ ዕርቅ እና ፈውስ ለማምጣት እንዲሁም የተጎጂዎችን መፍትሔ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ እንደሚያደርግ›› ይገልፃል።
በያዝነው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በአዲስ አበባ ባደርጉት ጉብኝት በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን ለማስቆም የተደረሰው ስምምነት አተገባበርን እና በሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ላይም ውይይት አድርገዋል። ይህም የሽግግር ፍትሕ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል። ተመድም በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ መሆንን እንደሚደግፍ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ገልጸዋል። በመጪዎቹ ሦስት ወራት በሽግግር ፍትሕ በፖሊሲ ሰነዱ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡን ያሳተፈ ውይይት እንደሚካሔድና ፖሊሲው እንዴት ይዘጋጅና እንዴት ይተግበር ተብሎ ውይይት ተደርጎበት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ የሚቀጥለው አዲስ ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገባ በአዲስ አበባው የመጀመሪያው የሽግግር ፍትሕ ውይይት ላይ ተገልጿል። የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የተከናወኑ ኢፍትሐዊ የሆኑና በቁርሾ የተሞሉ ታሪኮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመዝጋት፣ አዲሲቱን ኢትዮጵያ በአዲስና በተሻለ እሴት ለመገንባት የሚረዳ ነው።
በአገራችን እየተነሱ ያሉት የታሪክ ቁርሾዎች ወደ ኋላ በርካታ ዓመታትን ሊያስቆጥሩ የሚችሉ ሲሆኑ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በቅርቡ ከተከሰተው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር የተገናኙ ናቸው። ቢሆንም በሽግግር ፖሊሲው በዚህ የግብዓት መሰብሰቢያ ሰነድ ውስጥ ዜጎች ውይይት ሲያደርጉ ሒደቱ ከየት ይጀመር? የሚለውንና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ የሚያመቻች ነው። አንዳንዶች፤ ዜጎች በእንቶ ፈንቶ ትርክቶች በዘውጌ እና በጥላቻ ፖለቲካ አራማጆች ግጭቶች እንዲቀጣጠሉ እየጣሩ ነው። ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙሃን እና የማኅበረሰብ ሚዲያዎች የሚያስተላልፉት በሬ ወለደ ዘገባዎችና ጭብጥ አልባ አሉባልታዎች መቃቃርና መናቆር በአገሪቱ ሕዝቦች ለማቀጣጠል ሲፍጨረጨሩ ይታያል፤ በአገሪቱ የነበሩ በርካታ ውጣ ውረዶች እንደመሆናቸው፣ የሽግግር ፍትሕ በሰሜኑ አካባቢ ለተከሰቱ ግጭቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚታዩ መቃቃሮች መናቆሮች ፋይዳ እንዳለው ይናገራሉ።
ከወዲሁ ኅብረተሰቡ ስለ ሽግግር ፍትሕ ፋይዳ ግንዛቤ ይዞ መወያየቱ ለዘለቄታዊ ሰላም ሚና ይኖረዋል። የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው በኢትዮጵያ የተከናወኑ ኢፍትሐዊ የሆኑና በቁርሾ የተሞሉ ታሪኮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመዝጋት፣ አዲሲቱን ኢትዮጵያ በአዲስና በተሻለ እሴት ለመገንባት ያለመ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ የሚደረገው ውይይት ዘላቂ ሰላምና ዕርቅን ለማስፈን፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና ለተጎጂዎች ተገቢውን መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ነው። በዚህ ረገድ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ በሽግግር ፍትሕ መናቆርን አርቀው ለዜጎች ሰላምና እርቅ ፈጥረዋል። ለእኛም የሽግግር ፍትሕ ጸድቆ ቢተገበር እነ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ሰላም ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑና ለፀጥታ አካላት ፋታ ለአገሪቱ ዜጎች ሰላምና እፎይታ ይሆናል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም