በፋሽኑ ዓለም ትልቅ ሚና ከሚጫወቱ አካላት መካከል ዋነኞቹ በሞዴሊንግ ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ናቸው። በሰለጠኑ የዓለማችን ክፍሎች ለሞዴሊንግ ሙያ ትልቅ ቦታ ከመስጠታቸውም ባሻገር ከተቋማት አልፎ በግለሰቦች ደረጃ እንኳን የኑራቸው አካል በማድረግ ዕለት ከዕለት ያዘወትሩታል። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን የቅርብ ጊዜ ታሪክ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጥቂቶች ብቻ የሚሳተፉበት እምብዛም ጎልቶ ያልወጣ ጉዳይ ይሆናል። ለመሆኑ የሞዴሊንግ ሙያ በአገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? በዛሬው የፋሽን አምዳችን ያነጋገርነው ወጣት ሞዴል የሚነግረን አለው፡፡ ሞዴል ልደቱ ብርሃኔ በአዲስ አበባ ከተማ የሌጋሲ ሞዴሊንግና አርት አካዳሚ መሥራችና አሰልጣኝ ነው። እኛም በአካዳሚው በመገኘት ከወጣቱ ሞዴል ጋር ያደረግነው አጠር ያለ ቃለምልልስ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሌጋሲ ሞዴሊንግ የሚሰጠው አገልግሎት ምንድነው፤ አላማውስ?
ሞዴል ብርሃኔ፡- ሌጋሲ ሞዴሊንግ በአገራችን የመጀመሪያው የሞዴሊንግ አካዳሚ ሲሆን ኤጀንሲም አለው። አሁን ለመጡ ተመሳሳይ ተቋማት ሞዴል መሆን የቻለ ተቋም ነው። በሞዴሊንግ ሙያ ላይ ፍላጎት ያላቸውን ወንዶችም ሆኑ ሴቶችን በመቀበል ለሚፈልጉበት አላማ ብቁ እናደርጋቸዋለን። ከመነሻው ጀምሮ ትልቅ አላማና ራዕይ ይዞ የተነሳም ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሞዴሊንግ ሙያ በግለሰብም ሆነ በአገር ደረጃ ያለው ጠቀሜታ ምንድነው?
ሞዴል ብርሃኔ፡-ሞዴሊንግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። በግለሰቦች ደረጃ ስንመለከት በዋናነት ሰዎች በራስ የመተማመን አቅማቸውን ያጎለብታል። በእራሳቸው እግር ቆመው በየትኛውም ቦታ ስኬታማ እንዲሆኑ ሥነ-ልቦናቸውን ይገነባል። ጥሩ ሥነ-ልቦና ያለው ትውልድ ሲፈጠር ተደማምሮ ውጤቱ ለአገርም ጭምር ነው። ለሙያው ትልቅ ፍላጎት ካላቸው ደግሞ ከውስጣዊ ማንነት አልፈው ሕይወታቸውን የሚመሩበት መንገድም ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ሰልጣኞች ወደ ተቋሙ ከመጡ በኋላ ለምን ያህል ጊዜ ነው ስልጠናውን የሚወስዱት?
ሞዴል ልደቱ፡- የምንሰጠው የሞዴሊንግ ስልጠና ቢሆንም በውስጡ በርካታ ዘርፎች አሉት። እናም የስልጠና ቆይታቸው እንደ ዘርፉ የሚለያይ ይሆናል። ትንሹ የስልጠና ቆይታ ስድስት ወር ሲሆን ረዘም ያለ ጊዜ የሚፈጁት ደግሞ እስከ አስር ወራት ይዘልቃሉ።
አዲስ ዘመን፡- ተማሪዎቹ ስልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በእናንተ በኩል የሚመቻችላቸው የተለያዩ ዕድሎች አሉ?
ሞዴል ልደቱ፡- አዎን..በሚገባ እንጂ..የሞዴሊንግ ኤጀንሲ እንደመሆናችን የተለያዩ ተቋማት ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅም ሆነ ለሌላ ሞዴሎችን በሚፈልጉበት ሰዓት ከተቋማቱ ጋር በእኛ የሰለጠኑትን ሞዴሎች በማገናኘት የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን እንፈጥርላቸዋለን።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኛውን ጊዜ ሞዴሊንግና ፋሽን የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፤ እነዚህ ሁለት ነገሮች የአንድን አገር ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ ያላቸው ፋይዳ እንዴት ይገለፃል?
ሞዴል ልደቱ፡- በሚገባ ፋይዳ አላቸው። ሞዴሊንግ ማለት ምርትና አገልግሎትን የምናስተዋውቅበት ሁነኛ መንገድ ነው። ምርት ወይንም አገልግሎት ለማስተዋወቅ ደግሞ ያንኑ የሚመስል ፋሽን እንጠቀማለን። አስተዋዋቂዎቹ ደግሞ ሞዴሎች ናቸው። ስለዚህ ሞዴሎቹ የአንድን ማህበረሰብ ባህላዊ አልባሳት ሊሆን ይችላል፤ የትኛውንም የባህል እሴት የማስተዋወቅ ትልቅ አቅም አላቸው። ሞዴሊንጉ ለባህል ያለው ፋይዳም ከፍተኛ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሞዴል ሲባል አብዛኛውን ጊዜ በአዕምሮአችን የምንስለው ቆንጆ የፊት ገጽታ ያለውና ደመ ግቡ የሆነን ሰው ነው፤ ነገር ግን በሞዴሊንጉ ዓለም ቆንጆ ወይንም ሞዴል ሊባል የሚችለው ምን ዓይነት ሰው ነው?
ሞዴል ልደቱ፡- የሚገርመው ነገር በሞዴሊንግ ውስጥ ተመራጭ ሊያደርግ የሚችለው ያለን የፊት ገጽታ ወይንም መልክና ቁመናችን አይደለም። ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው ለራሱ ቆንጆ ነው። ማንም እሱን የሚመስል የለም። ወደ ሞዴሊንጉ ዓለም ስንመጣም የምንመርጠው ሰው ያለው ማንነትና ገጽታ ምርታችንን ወይም አገልግሎታችንን ለማስተዋወቅ ምን ያህል ምቹ ነው የሚለውን ነው። ለምሳሌ አንድን ቆንጆ የቢሮ ኃላፊ ለመግለጽ የፈለገ ቆንጆና ውብ ቢሆን የ15 ወይም 16 አመት ታዳጊ አንጠቀምም። ምክንያቱም ከዕድሜና ከብዙ መስፈርቶች አንጻር ያንን ኃላፊ መወከል አይችልም። ስለዚህ ሞዴሊንግ የቁንጅና ጉዳይ ብቻ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ሁሉም ሰው ሞዴል መሆን ይችላል?
ሞዴል ልደቱ፡- ትልቁ ነገር የፍላጎት ጉዳይ ነው። ሞዴሊንግ ደግሞ ይሄ ነው የሚባል ወጥ መስፈርት የለውም። ስለዚህ ሁሉም ሰው ለራሱና ለመሰሎቹ ሞዴል መሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ሌጋሲ ሞዴሊንግ የተለያዩ የፋሽን ትርኢቶችን በምን ያህል ጊዜ ያካሂዳል?
ሞዴል ልደቱ፡- ሁሌም በአመት አንድ ጊዜ የፋሽን ትርኢት ዝግጅቶችን ያደርጋል። እንዲያውም በቅርቡ ከሁለት ወራት በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ያሰለጠናቸውንና ከውጭ የሚመጡ ሞዴሎችም ጭምር የሚሳተፉበት የፋሽን ትርኢት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነን።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በአገራችን ያለው የፋሽንና ሞዴሊንግ ቁመናና ተቀባይነቱ ምን ይመስላል?፤ ከድሮውስ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ?
ሞዴል ልደቱ፡- ወደ ውጭው ዓለም ስንሄድ ሞዴሊንግ የተለመደ ነገር ነው። የራስ መተማመናቸውን ለማዳበር ጭምር እንደ ሕክምናም ይጠቀሙበታል። ነገር ግን እንደ እኛ አገር እይታ ስለሞዴሊንግ በደንብ ገብቶናል ለማለት ይቸግራል። ሙያው በአገራችን የቆየውን ያህል ሊያድግ አልቻለም። ቢሆንም ግን ከበፊቱ አንጻር በጣም ብዙ ለውጦች አሉ። አሁን አሁን እኛ ጋር እንኳን ሞዴል የመሆን ህልሙም ሳይኖራቸው ብዙ የተለወጡ ሰዎችን በመመልከት ብቻ መጥተው የሚቀላቀሉን አሉ።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም ተቋማችሁ የዚህ ሙያ ዋነኛ ባለቤት እንደመሆኑ፤ ዘርፉን ለማሳደግ ምን ይሠራል?
ሞዴል ልደቱ፡- የእኛ አካዳሚ በአገራችን የመጀመሪያው እንደመሆኑ ሙያውን የማስተዋወቅና የማሳደግ በርካታ ኃላፊነቶች ነበሩብን፣ እኛም በተቻለን አቅም ይህን ለማድረግ ሞክረናል። የሚታዩትንም ክፍተቶች ለመድፈን ከጊዜ ወደ ጊዜ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- ሞዴል ልደቱ ብርሃኔ ለሰጠኸን ጊዜ ከልብ እናመሰግናለን፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም