ከአስር ቀን በፊት ነው። አራት ኪሎ ከምሠራበት መስሪያ ቤት ወጥቼ ወደ ፒያሳ ለመሄድ ታክሲ መያዣው ጋ ሄድኩ። ስሄድ ብዙ የቆሙ ሰዎች አሉ። የምሄድበት ቦታ ቅርብ ከሆነ ቆሞ ታክሲ የመጠበቅ ልምድ የለኝም። በእግሬ እየሄድኩ እግረ መንገድ ካገኘሁ ነው የምገባ፤ ካጣሁ በእግሬ ለመቀጠል ማለት ነው።
እንደተለመደው በዚህም ቀን ሁኔታውን አይቼ በእግሬ ጉዞ ጀመርኩ። ገና ትንሽ እንደተራመድኩ አንድ ታክሲ መጣ፤ ረዳቱ በሁሉም ታክሲዎች እንደተለመደው አንገቱን በመስኮት አሾልኳል። ገና እሱ ሳይጠይቀኝ ‹‹ፒያሳ?›› አልኩት። አዎ! አለኝና በሩን ከፈተልኝ። ብዙ ጊዜ ታክሲዎች አንድ ሰው ብቻ ከሆነ የሚጨምሩ ሰው የበዛበትን ቦታ አለፍ ብለው ይጭናሉ፤ እና ይሄም እንደዚያ ነው የመሰለኝ። በሩን ከፍቶልኝ ስገባ ጋቢና ከሚቀመጠው ሰው ጀርባ ያለችዋ የአንድ ሰው ቦታ(ፊታችንን ወደ ተሳፋሪ አዙረን የምንቀመጥባት ማለት ነው) ባዶ ናት፤ ረዳቱም እሷ ላይ እንድቀመጥ ጠቆመኝና ተቀመጥኩ።
ገና ከመቀመጤ፤ ጋቢና ካለው ሰው ሒሳብ ሊቀበል ይሁን መልስ ሊሰጥ አላውቅም ረዳቱ በአናቴ ላይ እጁን ሰነዘረ። ሲሰጣጡ ይሁን አውቆ ያርግፈው ባላውቅም ሳንቲሞች ወደቁ። ጋቢና ያለው ሰውና ረዳቱ ጣልከው እየተባባሉ ረዳቱ ‹‹ይቅርታ አባቴ እስኪ አንዴ ብድግ ትይልኝ›› አለኝ። ተነሳሁና የወንበሩ ጫፍ ላይ ሦስተኛ ሆኜ ጠበቅኩት። ተቀምጨበት የነበረውን ምንጣፍ ገለጥ አድርጎ ሳንቲሞችን አነሳ። ልክ እንዳነሳው ልቀመጥ ስል ተቀምጨበት ከነበረው ምንጣፍ ሥር በሩብ ሊትሯ ፕላስቲክ ዘይት ይሁን ጋዝ አላውቅም ተቀምጧል። ወንበር ላይ ካሉት ተሳፋሪዎች(ተሳፋሪ መስለው የሚተውኑት ማለት ነው) ከፊት ያለው ‹‹እየፈሰሰብህ ነው›› አለው ረዳቱን። ምንጣፉን ወደነበረበት ልመልስ ስል ‹‹ቆይ ይቺ ነገር እየፈሰሰች ነው›› አለኝ ረዳቱ። ይህኔ ነገርየው ሿሿ መሆኑን መጠርጠር ጀመርኩ፤ ሰውነቴን ሁሉ በተጠንቀቅ አደረኩ።
በንዴት ጭምር ‹‹ስወርድ ታስተካክዋለህ!›› ብዬ ምንጣፉን መልሼ ተቀመጥኩበት። እንዳልተሳካላቸው ያወቁ ይመስላል። ወዲያውኑ ‹‹አውቶቡስ ተራ ነህ አይደል?›› አለኝ። አሁንም ቆጣ ብዬ ‹‹ፒያሳ ብዬህ አይደል የገባሁ? አምስት ብር እኮ ነው የሰጠሁህ!›› አልኩት። ‹‹የምትጨምርልኝ መስሎኝ ነው›› አለኝ። በአካባቢ ፖሊስ ፈልጌ ለፖሊስ እንዳላሲዛቸው፤ እንኳን በጥርጣሬ በትክክል ሲዘርፉ የታዩትንም ለማስያዝ ጣጣው ብዙ ነው። የእነዚህ ደግሞ ገና ሲዘርፉ ስላላየሁ ‹‹ምን አደረግን?›› ነው የሚሉት። በእርግጥ ሙከራ ስላደረጉ ሌባ ናቸው ማለት እችላለሁ። ችግሩ ግን አሁን አሁን የፖሊስ ነገር ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ ነው። ሌባውን ከመጠየቅ ይልቅ አመልካቹን ነው አፋጠው የሚጠይቁት። ‹‹ምን ሲያደርግ አየኸው? ለምን አስወሰድክ? እሱ መሆኑን በምን አወቅክ?…›› የሚሉ ጥያቄዎችን ነው የሚጠይቁት። ይሄ ደግሞ ለሌቦች የልብ ልብ ይሰጣል።
በዚያች ቅጽበት የወሰንኩት ውሳኔ መውረድ እንዳለብኝ ብቻ ነው። አውቶቡስ ተራ አይደለሁም ፒያሳ ነኝ ብዬው እየተጨቃጨቅን ሳለን፤ የግርምት ሳቅ ፈገግ ብዬ ‹‹እሺ አውርደኝ›› አልኩት። ቶሎ ብሎ ከፈተልኝ፤ ‹‹በሉ ይቅናችሁ!›› ብዬ ሳቅ ስል ከፊት ለፊት ካሉት አንደኛው ሳቀ። መንገዱ ተጋምሶ ነበርና እኔም በእግሬ ሄድኩ። እንዲህ ዓይነት ዝርፊያዎች በተለምዶ ‹‹ሿሿ›› ይባላሉ። ይህን ዓይነት ዝርፊያ ማክሸፍ የምንችለው በመንቃትና በመረጋጋት ነው። በነገራችን ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ሰዎች እየነቁ ነው። ገጠመኞቻቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚጽፉ ሰዎችን እንኳን ስናይ የሚበዛው ሙከራውን ያከሸፉት ናቸው። እንዲህ ዓይነት የዝርፊያ ሙከራዎችን ማክሸፍ የተቻለው የማጭበርበሪያ መንገዶቻቸውን አጀንዳ በማድረግና ለብዙዎች በማሳወቅ ነው። ለምሳሌ፤ ባዶ ታክሲ ውስጥ አትግቡ፣ ‹‹የት ናችሁ›› ብሎ ሲጠይቃችሁ አትናገሩ(ራሱ ሲጠራ ነው ለማለት ነው)… የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች በተደጋጋሚ ይነገራሉ። በእነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ሕጋዊ ባለታክሲዎች ራሱ እየተቸገሩ ነው።
እዚህ ላይ አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ። ከወራት በፊት ነው። ከጉርድ ሾላ ወደ ቦሌ አራብሳ ልሄድ በጠዋት ወጣሁ። አንድ ባዶ ታክሲ የያዘ ረዳት ይጠራል። ወጥቶ እየጠራ ስለሆነ፣ በዚያ ላይ አልዘናጋም በሚል መተማመን ታክሲው ውስጥ ብቻዬን ገባሁና ከፊት ለፊት ካለው ወንበር ተቀመጥኩ። የሚገባ ሰው ጠፋ። በውስጤ ሿሿ እየመሰላቸው ነው የሚል ጥርጣሬ አለ። ለመሆኑ ግን ሾፌሮች ያውቁት ይሆን ብዬ የሚለውን ለመስማት ‹‹ለምንድነው ግን ሰዉ ባዶ ታክሲ እያለ የሞላ ነው የሚጠብቅ?›› የሚል ጥያቄ ገና ከአፌ ሲወጣ ብሶቱ ጎድቶታል መሰለኝ ‹‹ምን ሿሿ እየመሰላቸው እኮ ባዶ ታክሲ ውስጥ አይገቡም!›› አለኝ በብሶት ድምጸት። በዚያው ስለሿሿ እየተጨዋወትን ሰው መግባት ጀመረ። በመንገደኞች ላይ ብቻ ሳይሆን በንጹህ ባለታክሲዎችም ላይ ችግር ፈጥሯል ለማለት ነው።
የማጭበርበሪያ መንገዶቻቸውን በመደበኛዎቹ መገናኛ ብዙኃን ሳይቀር መነገሩ ችግሩን በጥቂቱም ቢሆን ያቀለለው ይመስላል። እርግጥ ነው በየጊዜው የተለያየ አዳዲስ የማጭበርበሪያ መንገዶችን ያመጣሉ፤ ቢሆንም ግን መነገሩ ቢያንሱ ብዙ ሰው እንዳያጭበረብሩበት ያደርጋል። እየተነቃባቸው ሲሄድ ለረዘፋ የሚዘጋጁትም እየቀነሱ ይሄዳሉ። ለዚህም ይመስላል የማጭበርበሪያ መንገዶች አላዋጣ ሲሉ የኃይል እርምጃ መውሰድ የተጀመረው። በድብደባና በስለት ነገር በመውጋት ከባለቤቱ አቅም በላይ በሆነ ኃይል መቀማት ማለት ነው።
ምንም እንኳን ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ መወጣት ይቻላል ባይባልም በተቻለ መጠን ግን ታክሲ ውስጥ ያልተለመዱ ነገሮች ሲከናወኑ ቶሎ መንቃትና መጠርጠር ያስፈልጋል። ከነቃንና ካስታወስነው ቢያንስ በማጭበርበር መንገድ የሚወሰደውን ማዳን እንችላለን። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚቻለው ግን ፖሊስ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ቢሠራበት ነበር። አውቃለሁ ፖሊስ ብዙ ጫና እንዳለበት፤ ዳሩ ግን ይህም ቀላል ችግር አይደለም። እየከፋ ሲሄድ ማህበራዊ ግንኙነትን ሁሉ ያቃውሳል፤ መጠራጠርና መነጣጠል ይበዛል። የከተሞችንም ገጽታ ያበላሻል።
በነገራችን ላይ አንድ ሰሞን የዘመቻ ሥራ ቢሠራበት ይቀንሳል። ፖሊስ ሲቪል ለብሶ አልፎ አልፎ ድንገተኛ ኦፕሬሽን ቢሠራ ደፍሮ የሚሞክረው አይኖርም። በተለይም በበዓል ሰሞን የሚያጭበረብሩበትን መንገድ ተጠቅሞ ብዙዎችን መያዝ ይቻል ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በፖሊስ በኩል ለዚሁ ዓላማ ብቻ የተዘጋጀ የጥቆማ መስመር ቢኖር፤ ቢያንስ መኖሩ ስለተነገረ ብቻ ዘራፊዎች ሊፈሩ ይችላሉ። የተሽከርካሪውን ታርጋ ቁጥር በመያዝ ለሚሰጠው ጥቆማ ተገቢውን ቅጣት መስጠት የሚቻል ቢሆን ኖሮ ዘረፋ እንዲህ በገሃድ አይሆንም ነበር። ዳሩ ግን ምን ዋጋ አለው ‹‹ምንም አያደርጓቸውም!›› በሚል ተበዳዮችም መጠቆሙን እየተውት ነው። ኧረ እንዲያውም እያወቋቸውም ዝም ይሏቸዋል የሚል ሀሜት ሁሉ አለ። ከምንም በላይ ግን ለጊዜው አስተማማኙ ራስን መጠበቅ ነውና ጥንቃቄና መረጋጋት አይለየን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም