አንዳንድ ሆሄያት ይምታቱብኛል። “ን” ለማለት አስቤ “ኝ” ብዬ የምጽፍበት አጋጣሚ ብዙ ነው።ለምሳሌ በዚህ ጽሑፍ ርዕስ ላይ “ሽኝት” ብዬ የጻፍኩት “ሽንት” ለማለት ፈልጌ ነው። ስለዚህ ርዕሱን “ውሃ ሽንት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች” ብላችሁ አስተካክላችሁ አንብቡልኝ። አንተ ያወላገድከውን የምናስተካክልበት ምን እዳ አለብን ካላችሁም “ውሃ ሽኝት” ብላችሁ ብታነቡትም ችግር የለውም። ውሃ ሽንት ማለት ያው የጠጣነው ውሃ ሽኝት ስለሆነ የትርጉም ለውጥ አያመጣም።
የሀገራችን ወግ ጸሐፊዎች ተደራሲያቸውን በተባእት ጾታ የማናገር ልማድ አላቸው። ለምን እንደሆነ እንጃ! እኔም ዛሬ እንደዛ ላደርግ ነው። “Who ማይነስ Who” ተብሎ የለም። እነሆ!
ውዱ አንባቢዬ ሆይ … ለአዲስ አበባ እንግዳ ነህ? ከሆንክ ምክሬ ያስፈልግሃል።ካደርክበት ቤት ስትወጣ መንገድ ላይ ሽንትህ እንዳይመጣ ጸልየህ ውጣ። በተቻለህ መጠን ውሃ አትጠጣ። ጉሮሮህ ደርቆ እረፍት ከነሳህ ግን የታሸገ ውሃ ገዝተህ ጠጣ። ታዲያ የፕላስቲክ ኮዳውን እንዳትጥለው።ይህን ስልህ የአዲስ አበባ ካፌዎች አንድ ብርጭቆ ውሃ ለምነሃቸው ይከለክሉሃል ማለቴ አይደለም። የጠጣሃትን ውሃ እንድትሸኛት ግን ሽንት ቤታቸውን አይከፍቱልህም።
በአብዛኞቹ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች ካልተስተናገድክ በቀር መሽናት አትችልም።ባሮችና ላውንጆች ጋርም የተለየ ነገር የለም። እዚያ እንደውም የማያላውሱ ያልተጻፉ ሕጎች ቢያጋጥሙህ አይግረምህ።አንድ ቢራ አዘህ ሁለት ጊዜ መጸዳጃ ቤት መሄድ ልትከለከል ትችላለህ። አይዞህ! የሁለተኛውን ቢራ አንገት ስትጨብጥ ቁልፉን ያስጨብጡሃል።ለቅይጥ አገልግሎት በተገነቡት የከተማችን ሕንፃዎች ላይ የሚገኙት አብዛኞቹ ሽንት ቤቶች በፌስ ቡክ ቋንቋ ሲገለጹ “ኦንሊ ሚ” ናቸው፤ ፐብሊክ የሆኑት ደግሞ ባለቤት አልባ እስኪመስሉ ድረስ “ጽዱ” ናቸው።ለሱቅ ባለቤቶች ብቻ ቁልፍ ሰጥተው ሽንት ቤቶቻቸውን የሚከረችሙ ሞሎች ይበዛሉ። በእርግጥ እኛ ተጠቃሚዎቹ ዘንድም ችግር አለ። ተገቢ ካልሆነ አጠቃቀም እስከ ስርቆት መፈጸም የሚደርሱ ባለንብረቶችን የሚያስቆጡ ጥፋቶች እንፈጽማለን።
ቦታ ሳንመርጥ ዚፓችንን በምንከፍት ወንዶችና ቀሚሳቸውን በሚሰበስቡ ሴቶች ምክንያት አዲስ አበባ ጉድጓድ ሆናለች። እያንዳንዱ ነገር የራሱ የሆነ ጥቅምና ጉዳት አለው አይደል? በከተማችን በተገኘው ቦታ ሁሉ መሽናት ባህል መሆኑን ተከትሎ አንድ መጥፎ ልማድ ተወግዷል። ይሄውም በያጥሩና በየግድግዳው ላይ “መሽናት ክልክል ነው” ብሎ መጻፍ ነው። እንዲህ እንደዛሬው የትኛውም ቦታ ላይ መሽናት መብት ከመሆኑ በፊት፣ በየሃምሳ ሜትሩ ተጽፎ የሚታየው የከተማዋ ሞቶ “መሽናት ክልክል ነው” የሚል ነበር። እዚህም እዚያም ተለቅልቆ ለዓይን ይሸት የነበረው ጽሑፍ ዛሬ ተፈልጎ አይገኝም፡፡
ጽሑፉ በመቅረቱ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ደስተኛ ቢሆንም መተዳደሪያቸው ለነበረ ወገኖች ግን ትልቅ ጉዳት ነው።ጽሑፉን በመጻፍ ይተዳደሩ የነበሩት “ሙያተኞች” ዋጋ የሚደራደሩት “በሆሄ ይሄን ያህል ይከፈለን” እያሉ ነበር። ለምሳሌ በአንድ ሆሄ 50 ብር ተከፍሏቸው ለመጻፍ ከተስማሙ በዓረፍተ ነገሩ ውስጥ የሚገኙት ሆሄያት ቁጥር በ50 ተባዝቶ ይከፈላቸዋል። በዚህ ምክንያት ሆነ ብለው መሽናት እንደማይቻል የሚገልጸው አረፍተ ነገር እንዲረዝም በማድረግ ሕዝቡን ይበዘብዙ ነበር። ከሽንት ሌላ የሚሸና ነገር እንደሌለ ልቦናቸው እያወቀ “መሽናት ክልክል ነው” ከሚለው ሀረግ በፊት “ሽንት” የሚል ቃል ይጨምራሉ።የሚያጽፈው ሰው የመክፈል ችግር የለበትም ብለው ካሰቡ ደግሞ “ሽንት” ከሚለው ቃል ቀድመው “እዚህ ቦታ” የሚል ሀረግ ያስገባሉ። በጣም ስግብግብ የሆኑት አይንአውጣ ጸሐፊዎች “ቦታ” የሚለውን ባለ ሁለት ሆሄ ቃል አስወጥተው “አካባቢ” በሚል ባለአራት ሆሄ ቃል ይተኩታል። በመጨረሻ “መሽናት ክልክል ነው” የሚለው ሀረግ “እዚህ አካባቢ ሽንት መሽናት ክልክል ነው” ተሰኝቶ እጥፍ ክፍያ ያስገኛል።
እያደር “የትም ይመቸኛል” በሚል ሳውንድ ትራክ ታጅቦ ሽንቱን የሚሸናው ሰው ስለጨመረ ከተማዋ ከዚህ አሰልቺ የክልከላ ጽሑፍ ተላቀቀች። ምን ዋጋ አለው! አዲስ አበባ በየትም ይመቸኛል ሙቭመንት ተደናግጣ ለኗሪዎቿ መጸዳጃ ቤት መገንባት ሲገባት ለሌላ አዲስ ወራሪ ኃይል እጇን ሰጠች። ተረኛው ወራሪ ኃይል ባልዲ ሆነ። የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በሽንት መሽኛ ባልዲዎች አሸበረቁ። እነዚህን ያዋቂ ፖፖዎች በዋና ዋና መንገዶችና አደባባዮች ላይ አስቀምጠን ስናበቃ ደረታችንን ነፍተን አዲስ አበባ ከተቆረቆረች 137 አመታት አስቆጥራለች እንላለን። ከተማችን ነብስ ካወቀ በኋላ እንደ ልጅነቱ ፖፖ ላይ የሚሸና ጎረምሳ ሆና፣ የኛ ዲስኩር ማለቂያ የለውም። የአፍሪካ መዲና… ሸገር… አዱ ገነት… ፊንፊኔ… በረራ …!
እነዚህ ባልዲዎች እየሰጡ ያሉትን አገልግሎት እያጣጣልኩ አይደለም። በበኩሌ “አዲስ አበባ የሁሉም ነች” ከሚለው ፖለቲካ በላይ የሚዋጥልኝ፣ የእነዚህ ባልዲዎች የሁሉም መሆን ነው። ምክንያቱም ፊኛው የተወጠረን ሽንተኛ ሁሉ ያለ ልዩነት ያስተናግዳሉ። አዲስ አበቤ ከባልዲ ቀድቶ የጠጣውን ውሃ መልሶ ለባልዲ ማቀበሉን “የቄሳርን ለቄሳር” ብሎ ያልፈዋል እንጂ አያማርርም።
አዲስ አበባ ላይ በኪራይ ቤት ውስጥ የሚኖር ሰው ቋሚ በሽታ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ነው።እንደ ልቡ መሽናት ባለመቻሉ ምክንያት ውሃ መጠጣት የሚፈራ ተከራይ ብዙ ነዋ! ሽንት ቤት ለመሄድ ተሳቆ ቤቱ ውስጥ ባገኘው ፈሳሽ መያዣ ሽንቱን የሚያቁረውን ቤት ይቁጠረው። በየሰፈሩ የሚቀመጡ የቆሻሻ ገንዳዎች ጢም የሚሉት ሽንት በተሞላ የፕላስቲክ ጠርሙስና ጀሪካን ሆኗል። የ19 ሚሊዮን ብሩ ባስ መጸዳጃ ቤት አለው ሲባል ሰምቼ አዲስ አበባ ነጋላት ብዬ ነበር። በኋላ እንዲህ ያለ ወሬ የሚነዙት ቧልተኞች ናቸው ተባለ። ይህ የሚያሳየው የከተማችን አሳሳቢ ችግር ቧልተኞችን ሳይቀር እንዳሳሰባቸው ነው።እውነታቸውን ነውኮ! ችግሩን መቅረፍ ባይቻል እንኳን ለመቀነስ መንቀሳቀስ ይገባ ነበር።ሌላው ቢቀር የሚጠጣ ነገር አምራች ድርጅቶች ላይ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ አንዳች ዓይነት ግዴታ በመጣል የተወሰኑ መጸዳጃ ቤቶችን እንዲገነቡ ማድረግ ይቻላል።
ለጉዳዩ ትኩረት ያለመስጠትና ሙሰኝነት እንጂ የሕግ ከፍተት ያለ አይመስለኝም። መጸዳጃ ቤት የሌለው ምግብ ቤት ገጥሞኝ ያውቃል። በእጅ ካልተሄደ በቀር መጸዳጃ ቤት አልባ ምግብ ቤት የንግድ ፈቃድ ሊያገኝ አይችልም።ከ50 አመታት በፊት በቅድሚያ መጸዳጃ ቤት ካልተሟላ ምግብ ቤት ቀርቶ መኖሪያ ቤት እንኳን መገንባት አይፈቀድም ነበር። በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ በታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ያገኘሁት አንድ ጽሑፍ ይህን የሚያረጋግጥ ነው። “በቅድሚያ የመጸዳጃ ቤት ያልሠሩ የቤት መሥሪያ ፈቃድ አይሰጣቸውም” በሚል ርዕስ የወጣው ጽሑፍ እንደሚከተለው ይነበባል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ወደፊት ቤት የሚሠሩ ሰዎች አስቀድመው የሽንት ቤት ካልሠሩ የቤት መሥሪያ ፈቃድ የማይሰጣቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።ማንኛውም ቤት ተገቢው የንጽህና ቤት እንዲኖረው አስፈላጊ ነው።በዚህ በኩል ያለውን ችግር ለማሟላት ይረዳ ዘንድ ለወደፊቱ የቤት ሥራ ፈቃድ በሚሰጥበት ጊዜ የቤት ውስጥ የንጽህና ቤት ለመሥራት የማይችሉ ከዋናው ቤት ውጪ የሚሠሩትን የንጽህና ቤት ሠርተው መጨረሳቸው ካልተረጋገጠ የቤት ሥራ ፈቃድ አይሰጥም። ይህም ተግባር በጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት ለቴክኒክ አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤትና ለየክፍል ማዘጋጃ ቤቶች ትዕዛዝ መተላለፉን መግለጫው አስረዳ።በትዕዛዙ መሠረት አነስተኛ ቤተ ሠሪዎች፣ ቤቱን ከመሥራታቸው በፊት ተገቢ የሆነ የንጽህና ቤት እንዲሠሩ ይገደዳሉ። የማዘጋጃ ቤቱም ለሁሉም ቤቶች እንደየአቅማቸው የንጽህና ቤት እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ምክርና ፕላን በመስጠት ስለሚረዳ፤ ሕዝቡ በዚህ ተግባር ከማዘጋጃ ቤቱ ጋር እንዲተባበር የፕሬስና የሕዝብ ኅብረት ማስፋፊያ ክፍል ገልጧል፡፡
እንግዲህ ወደ ኋላ ቀርተናል እንዳንል ኋለኞቻችን በጋዜጣ ያስነገሩት ይህ መግለጫ እጅን በአፍ የሚያስጭን የሥልጣኔ ውሃ ልክ ነው። ወደ ኋላ መመለስም ሆነ ወደፊት መራመድ ተስኖን ቅርቃር ውስጥ ሳንገባ አንቀርም።ምን ተሻለን ?
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም