አዲስ አበባ፦ በዘላቂ የልማት ግቦች የተካተተው ንፁህ የመጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን አገልግሎትን እ.አ.አ 2030 በሁሉም የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ፤ ትናንት ሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወር አፈፃፀም ግምገማ ሲያደርግ እንደተናገሩት፤ የመጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን አገልግሎትን ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡ እ.አ.አ በ2030 በሁሉም የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች ንፁህ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ እቅድ ተቀምጧል፡፡
እንደሳቸው ገለፃ፤ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን በገጠር ንፁህ የመጠጥ ውሃን ለአንድ ሰው በቀን በአማካይ 25 ሊትር ለማቅረብ እየተሰራ ነው። በዚህም በ2007 ዓ.ም 59 በመቶ የነበረውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን በ2012 መጨረሻ ወደ 85 በመቶ ከፍ ለማድረግ እቅድ ተይዟል፡፡ 20 በመቶ የሚሆነው የገጠር ንፁህ የመጠጥ ውኃም በቧንቧ መስመር የሚመጣ መሆን አለበት፡፡
የከተሞች የውሃ አቅርቦትም ደረጃ ከ40 እስከ 100 ሊትር በቀን ለአንድ ሰው ለማቅረብ እየተሰራ ነው። በሁሉም ከተሞች የውሃ መስመር ብልሽቶችን፣ ምጣኔውንና የሚባክን የውሃ መጠንንም ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ ግቦች ተቀምጠው ወደ ተግባር መገባቱን አመልክተዋል፡፡
ዶክተር ነጋሽ እንዳብራሩት በከተማና በገጠር የሳኒቴሽን አቅርቦትን የሚያሳልጡ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ተቀርፀው እየተሰራባቸው ይገኛሉ። ስራዎቹን ለማሳካትም ብሔራዊ ዎሽ ፕሮግራም ተብሎ የሚጠራ ፕሮግራም ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። ውሃ ማቅረብ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅንን አንድ ላይ በመጠመር ወደ ስራ የተገባበት ፕሮግራም ነው።
በዚሁ ፕሮግራም በገጠር ለሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ህዝብ ንፁህ የመጠጥ ውኃን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እስካሁን ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ወይም የዕቅዱን 95 በመቶ በማሳካት ንፁህ የመጠጥ ውሃን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
በተመሳሳይ በከተማ ለሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ንፁህ የመጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ ለአምስት መቶ ሺህ ህብረተሰብ ተደራሽ በማድረግ ዝቅተኛ አፈፃጸም መመዝገቡን አመላክተዋል።
አጠቃላይ የንፁህ የመጠጥ ውኃና የሳኒቴሽን አገልግሎት የመጀመሪያው የአምስት ዓመት ፕሮግ ራም በያዝነው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን የሁለተኛው አምስት ዓመት ፕሮግራም ደግሞ ከሰኔ በኋላ ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑ ተገልጿል። ለዚሁ ፕሮግራምም ከለጋሽ ድርጅቶች አምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቦ ወደ ክልሎች ተላልፏል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2011
በፍሬህይወት አወቀ