አዲስ አበባ:- የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤንጀንሲ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለተለያዩ አገልግሎት የሚውል ከ600 ሄክታር መሬት በላይ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ለታ፤ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ኤጀንሲው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለመኖሪያ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ፣ ለማህበራት እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል ከ600 ሄክታር በላይ መሬት አዘጋጅቷል።
ከተዘጋጀው መሬት ውስጥ 190 ሄክታር መሬት ለተጠቃሚዎች ተላልፏል። ከዚህም ውስጥም 150 ሄክታር መሬት ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለቤቶች ኤጀንሲ የተላለፈ ሲሆን በቀጣይ 105 ሄክታር መሬት ለጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ለማስተላለፍ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ኤጀንሲው የእቅዱን 83 በመቶ ማከናወኑን የተናገሩት ስራ አስኪያጁ፣ በቀጣይም መሬትን ለተለያዩ አገልግሎቶች የማዘጋጀት ስራ ይሰራል ብለዋል። ኤጀንሲው በመልሶ ማልማት በፊት ከነበረው አካሄድ በተለየ ህብረተሰቡን በቦታው ላይ ተጠቃሚ የማድረግ አካሄድ እየተከተለ እንደሆነና አፈፃፀሙም መልካም እንደሆነ ገልጸዋል።
በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ባለሃብቶች የተጀመረው የለገሃር የተቀናጀ የመኖሪያ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ልማት ፕሮጀክት የዚህ ማሳያ ነው። የዚህ ፕሮጀክት ጥናት ተጠናቆ ለከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ የቀረበ ሲሆን በቅርብ ቀን እንደሚጸድቅም ጠቁመዋል። ጥናቱ እንደጸደቀም ወደ ስራ ለማግባት የሚያስችል ሙሉ ዝግጅት በባለሃብቶቹም ሆነ በከተማ አስተዳደሩ በኩል እንዳለም ተናግረዋል። እንደ ስራ አሰስኪያጁ ገለፃ፣ የከተማ አስተዳደሩ ሌሎችም ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድርግ እየሰራ ነው። የህግ ማዕቀፉም ይህን በሚያሳካ መልኩ እየተዘጋጀ ነው።
‹‹በለገሀሩ ፕሮጀክት የሚነሱ ዜጎች ቆጠራ መደረጉንና ከሚካሄደው ልማት ተጠቃሚ ለመሆን ወይም በአካባቢው ምትክ ቦታ ለማግኘት ያላቸውን ፍላጎትም ተቀብለናል። ዝርዝር ስራዎችም ተሰርተዋል›› ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤንጀንሲ የተቋቋመው ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል መሬት ለማዘጋጀት፣ የመንገድና የሌሎች መሰረተ ልማት ግንባታዎች ሲካሄዱ ወሰን ለማስከበር፣ የካሳ ክፍያ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግና ጥናትና ትግበራ አከናውኖ ለሚመለከታቸው አካላት ለመስጠት ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2011
በፍሬህይወት አወቀ