* የመደበኛና የከባድ መንገድ ጥገና ሥራም ዝቅተኛ ነው
አዲስ አበባ፡- በተያዘው በጀት ዓመት የወልድያ ሀራ ገበያ- መቐለ የባቡር ግንባታ ስድስት ነጥብ ሰባት በመቶ ለማከናወን እቅድ ቢያዝም እስካሁን አንድ ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ብቻ መከናወኑ ተገለፀ፡፡ በአገሪቱ የሚደረጉት የመደበኛና የከባድ መንገድ ጥገና ስራም ዝቅተኛ አፈፃፀም ማስመዝገቡም ተመልክቷል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀሙን ሲያቀርቡ እንዳሉት፤ የወልድያ ሀራ ገበያ መቐለ የባቡር ግንባታ ስድስት ነጥብ ሰባት በመቶ ለማከናወን እቅድ ቢያዝም እስካሁን አንድ ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ተከናውኗል፡ ፡ አፈፃፀሙ ሲታይ ከእቅድ በታች የተከናወነ ከመሆኑ ባሻገር አጠቃላይ የግንባታው አፈፃፀም 54 በመቶ ብቻ እንዲሆን አድርጓል፡፡
እንደ ወይዘሮ ዳግማዊት ገለፃ፤ የባቡር መስመር ዝርጋታው ከእቅድ በታች የሆነው የፕሮጀክቱ የፋይናንስ ምንጭ 40 በመቶ ከአገር ውስጥ እንዲሁም 60 በመቶው ከውጭ አገር እንዲሆን ተወስኖ ነበር፡፡ የፕሮጀክት ስራው ከተጀመረ በኋላ 28 በመቶ ብቻ ከአገር ውስጥ ፋይናንስ የተከፈለ ሲሆን ከውጭ አገራት ፋይናንስ ምንጭ እስካሁን የተከፈለ ነገር የለም፡፡ በቀጣይ ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ተጨማሪ በጀት እንዲጨመር ጥያቄ ይቀርባል፡፡
በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ የመደበኛና የከባድ መንገድ ጥገና ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም ዝቅተኛ አፈፃፀም ማስመዝገባቸውን አመልክተዋል፡፡ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 11ሺ 641 ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር ዋና ዋና መንገዶች ማጠናከር፣ የመንገድ ደረጃዎችን ማሻሻል፣ የአገናኝ መንገዶች
ግንባታ፣ የከባድ መንገድ ጥገና፣ መደበኛ ጥገና እንዲሁም ሌሎች የመንገድ ስራዎች ለማናወን ታቅዶ ስድስት ሺ 980 ኪሎ ሜትር ብቻ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
ለአፈፃፀሙ ማነስ የወሰን ማስከበር ችግር፣ በአገሪቱ ያለው የፀጥታ ችግር፣ የግብዓት አቅርቦት ችግር፣ የኮንትራክተሮችና የአማካሪ ድርጅቶች አቅም ማነስ እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮንትራት አስተዳደር አቅም ማነስ በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም የመንገድ ፕሮጀክቶች በተቀመጡላ ቸው የጊዜ ገደብ መሰረት መከናወን አለመቻሉን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በሶስት መቶ ቢሊዮን ብር ወጪ ላለፉት ዓመታት መንገድ የተገነባ ቢሆንም ለተገነቡ መንገዶች ጥገናና ለመንገድ ደህንነት የተመደበው ገንዘብ አነስተኛ መሆን እንቅፋት መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት የተገነቡት መንገዶች በኪሎ ሜትር ሲታይ ከአምናው የተሻለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን የተቀመጡት እቅዶች የተለጠጡ በመሆናቸው ለማሳካት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
በመጀመሪው ሩብ ዓመት በአገሪቱ በነበሩ የፀጥታ ችግሮች ምንም አይነት ስራ አለመከናወኑን የጠቀሱት ኢንጅነር ሀብታሙ፤ በሁለተኛውና በሶስተኛው ሩብ ዓመት በተቻለ አቅም ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ለመንገድ ግንባታዎች መዘግየት የተቋራጮች ችግር፣ የበጀት እጥረትና የወሰን ማስከበር ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2011
በመርድ ክፍሉ