ገቢዎች ሚኒስቴር መረጃው ትክክል አይደለም ብሏል
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ግብር መክፈል ከሚገባቸው ዜጎች 60 በመቶዎች እየከፈሉ አለመሆኑን ጥናቶች እንደሚያመለክቱ በሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የኢኮኖሚክስ መምህሩ አቶ ደጀኔ ማሞ (ረዳት ፕሮፌሰር) አስታወቁ። ገቢዎች ሚኒስቴር በበኩሉ ጥናቱ ስህተት መሆኑን አስታውቋል።
አቶ ደጀኔ ለአዲስ ዘመን በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ በመደበኛው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ግብሩን መክፈል ከሚገባው ዜጋ 60 በመቶ እንደማይከፍል ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር መረጃ እንደሚያሳየው፤ በኢኮኖሚው ውስጥ ካለው እንቅስቃሴ 36 በመቶ የሚሆነው ኢ-መደበኛ ነው። ይህንን ግብር ማስከፈልም አይቻልም።
ግብር ያለመክፈል እና በኢ-መደበኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉት ዜጎች ችግር መንስዔው የግብር ከፋይ ምዝገባ ሥርዓት አለመዘርጋት፤ የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል፣ መንግሥት የሰበሰበውን ገንዘብ ግብር ከፋዩ በትክክለኛ ተግባር ላይ እያዋለ መሆኑን አለማመንና የግልጸኝነት መጥፋት እንዲሁም የግብር አከፋፈሉ ፍትሃዊ አለመሆንና ሌሎች ችግሮች መሆናቸውን አመላክተዋል።
ከኢኮኖሚው መዋቅር ጋር የተያያዘ የግብር አከፋፈል ችግር መኖሩን ያነሱት አቶ ደጀኔ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረት የሆነው ግብርናን ምርታማነቱን መሠረት አድርጎ ግብር መክፈል ሲገባው አርሶ አደሩ የሚከፍለው በያዘው መሬት ስፋት ልክ በመሆኑ ፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት የለም። መንግሥት የግብር አሰባሰብና አሠራሩን ባለመዘመኑና የአሠራር ሥርዓት ባለመዘርጋቱ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ብርም አገሪቱ ታጣለች። ከቀረጥ ነፃ ከሚገቡ ዕቃዎች ብቻ እንኳ አገሪቱ በዓመት ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ እንደምታጣም ምሁሩ ተናግረዋል።
በገቢዎች ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ይርጋ፤ በአቶ ደጀኔ ማሞ ጥናትን ጠቅሰው ባቀረቡት መረጃ አይስማሙም። በተቋማቸው የተጠናው ጥናት ግብር መክፈል ከሚገባው 40 በመቶ የማይከፍል ሲሆን 60 በመቶው ግን እየከፈለ መሆኑን እንደሚያመለክት አረጋግጠዋል። ግብር የማይከፍሉ የትኞቹ ተቋማትና ዘርፎች እንደሆኑ ለመለየት ቡድን ተቋቁሞ ሚኒስቴሩ ጥናት እያካሄደ መሆኑም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2011
በአጎናፍር ገዛኸኝ