የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በግንባሩ እህትና አጋር ድርጅቶች መካከል የሚታየውን መጠራጠር በመፍታት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለማምጣት መምከሩን፤ በሚታረሙና በሚስተካከሉ፣ አገርና ህዝብን ማዕከል ባደረጉ ጉዳዮች ላይም ከመግባባት መድረሱን አስታውቋል።
ድርጅቱ፤ ይህን ይበል እንጂ ምሁራን ከዚህ በፊት የሰጣቸውን መግለጫዎችን በማንሳት በግንባሩ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት አለማምጣቱን ይናገራሉ። ይህን ሀሳብ ከሚያነሱ ምሁራን መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህሩ ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ አንዱ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ኢህአዴግ፤ በጥልቅ ተሃድሶ ወቅትም የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለማምጣት መግባባቱ ገልጾ ነበር። በተግባር ግን አልፈጸመውም። በአመራሩ መካከልም መግባባት አልተፈጠረም ችግሮቹ ቀጥለዋል ይላሉ።
ዛሬም ቢሆነም የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በቀላሉ አይመጣም። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዩተ ዓለምን ፈትሾ ለመቀየር በሌሎቹ እህት ድርጅቶች ሀሳብ ቢነሳም ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አይቀየር የሚል ሃሳብና አመለካከት መያዙን በትግራይ ክልል እየተሰሩ ካሉና በአመራሩ የሚተላለፉት መግለጫዎች ህወሓት ለአንድነትና ለውህደት ፍላጎት እንደሌለው ያመላክታሉ፡ ፡
በትግራይ ክልል ያሉ አንዳንድ አመራሮች በአስተሳሰብ በመለየታቸውና ለውጡን የተቃወሙ በመኖራቸው ሲወያዩ የአሸናፊና ተሸናፊ ግንኙነት ነው ያለው። በድርጅቶቹ መካከል የነበረው የበላይና የበታች አስተሳሰብ መቅረቱን ተከትሎ የተግባር ልዩነት መኖሩን እንደሚያመለክት ይናገራሉ።
ዶክተር ሲሳይ፤ ህወሓት ብቻ ሳይሆን በአማራ ክልል በኩልም ባለፉት ዓመታት የመገፋት ስሜቱ ስለነበረ ይህንን ማስቆም አለብን ብለው የሚንቀሳቀሱ ወጣቶችና ምሁራን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ላይ ጫና እየፈጠሩ ናቸው፡፡ ስለዚህም ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ አማራ ክልል ላይ ለመምራት ሊያስቸግር ይችላል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ቢሆንም ከ10 በላይ ፓርቲዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እየተጠናከሩ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ወደ ተፋጠነ ውህደት ላይገባ ይችላል፡፡ እነዚህ ተደማምረውም የአስተሳሰብ አንድነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን አይሆንም። እውን ካልሆነ ደግሞ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለማምጣት ያስቸግራል፣ በመግባባት ተወያይቶ ለማረምና ለማስተካከል ያዳግታል። በዚህ ሁኔታ በፍጥነት ወደ አንድነት ለመግባት ማዳገቱን ያብራራሉ።
በህግ የመጀመያ ዲግሪ፣ በፌዴራል ጥናት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሰሩት የህግ አማካሪና ጠበቃው አቶ ዝናቡ ይርጋ፤ የዶክተር ሲሳይን ሀሳብ ይጋራሉ። እሳቸው እንደሚሉትም መግለጫው እራሱ በአመራሩና በእህት ድርጅቶች መካከል ልዩነትና መጠራጠር መኖሩን የሚያሳብቅ ነው።
ከአጋር ድርጅቶቹ መካከል ውህደቱን ያልተቀበሉ ድርጅቶች አሉ። ውህደቱን ባልተቀበሉበት ሁኔታ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ማምጣት አይቻልም።አሁን ያሉ ልዩነቶችን ከማንሳት ይልቅ ወደ አንድነት ቢመጣ የተጠናከረች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ይቻላል ሲሉም ያመላክታሉ።
ድርጅቱ፤ወደ አንድ መምጣት ያልቻለው ህዝባዊ ራዕይ ስለሌለው እና ከህዝብ ይልቅ የግል ጥቅሙን የሚያስቀድም፣ ከመርህ ውጭ የሚንቀሳቀስ አመራር መኖሩን በምክንያትነት ያነሳሉ። የልዩነትና መጠራጠር መንግስት መንስዔውም አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ስለነበረ፣ ጸረ ዴሞክራሲያዊነትና ዴሞክራሲያዊነትን እየቀላቀለ መሄድ ስለሚፈልግ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
በዚህ ምክንያትም የግንባሩ አባላት በሙሉ መናበብ አይታይባቸውም፡፡ ኦዴፓና አዴፓ ከቀድሞው በተሻለ መናበብ ይታያል፡፡ በአንዳንዶቹ ደግሞ የመጠላለፍ ሁኔታ አለ ሲሉም አቶ ዝናቡ ይናገራሉ።
ዶክተር ሲሳይ፤ የተፈጠረው ጥርጣሬ በአገር ላይ ትልቅ ተጽእኖ ፈጥሯል፡፡ የህግ የበላይነትን ለማስከበር አዳጋች አድርጎታል፡፡በተሸናፊው ወገን በስሜታዊነት የሚገለጽ አሉታዊ አስተያየት የአገር ገጽታን እያበላሸ ነው። ልማቱ እንዳይፋጠን፣ መልካም አስተዳደር እንዲባባስ፣ አዴፓ ተረኛ ሆኖ ሁሉንም ነገር እንዲቆጣጠር ማድረጉንም ያመላክታሉ።
አቶ ዝናቡ በበኩላቸው፤የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት አለመፈጠሩ በአገር ላይ ችግሮችን ፈጥሯል። በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የህግ ጥሰቶች ከመናናቅ የመነጩ ናቸው፡፡አፍራሽ ክስተቶች እየተቀየሩ እንዲፈጠሩ አድርጓል። ስርዓት አልበኝነት ነግሷል፡፡ በአንዳንድ ክልሎች በሙስና፣ በሰብአዊ መብት ጥሰትና አገርን አደጋ ላይ በመጣል ወንጀል የተጠረጠሩ እንዲሸሸጉ ዕድል ሰጥቷል ባይ ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ባለመፈጠሩ በአንዳንድ አመራሮችና በክልል መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ መረጃዎች ህዝቡን በማደናገር እየፈጠረ ያለው ጫና ቀላል አይደለም። በሚተላለፈው መረጃ ምክንያትም ጉዳት የመድረስ ዕድሉም ከፍተኛ ነው። በፌዴራል ደረጃ የሚሰጡ ሹመቶችም በመግባባት ላይ ተመስርቶ ስላልሆነ ውሎ አድሮ የስልጣን ክፍፍሉ ላይ ቅሬታ ሊያስነሳ እንደሚችሉም ይናገራሉ፡፡
ችግሮቹ መታረምና መስተካከል የሚችሉት መደማመጥ፣ መነጋገርና መግባባት ሲኖር ነው የሚሉት ዶክተር ሲሳይ፤ ተስማምተው፣ ተዋህደው፣ ጠንካራ አመራር ከመሰረቱ ሰላምና መረጋጋት ሊያሰፍን እንደሚችል ያመለክታሉ፡ ፡ ልማቱን ማፋጠን፣ያለውን ሃብት በአግባቡ መጠቀምና ችግሮችን ማስቆም ይቻላልም ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡
ከዚህ በተቃራኒው መጠራጠሩ፣አለመግባባቱና መወጋገዙ ከቀጠለ አገርን በአግባቡ መምራት ያዳግታል፣ ህግ ማስከበር ያስቸግራል። የመንጋ ፍትህ፣ ስርዓት አልበኝነትና ክልሎች የሚፈጥሩት ሳንካ ማቆሚያ ያጣል የሚል ስጋታቸውን ያነሳሉ።
አቶ ዝናቡ በበኩላችው፤ የአስተሳሰብና የተግ ባር አንድነት ሙሉ በሙሉ ይመጣል ተብሎ ባይ ጠበቅም ማጥበብ እንደሚቻል ያመላክታሉ፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለም ኢትዮጵያ ድህነትን ትሻገራለች፣ የህግ የበላይነት ይከበርባታል፣ የህዝቦች አብሮ መኖር፣ ትብብር እና መደጋጋፍ ይጠናከራል። ለዜጎቿም የተመቸች ትሆናለች። ለአፍሪካም ሆነ ለሌሎች አገሮችም መጠለያ መሆኗ ይቀጥላል። ያሸማጋይነት ተምሳሌቷም በዓለም መድረክ ይቀጥላል ይላሉ።
ሂደቱ መስተካከል ካልቻለ ግን መጠራጠር ይነግሳል፡፡ በጋራ ስለአገር ማሰብና መጨነቅ ይጠፋል፡፡ ‹‹እኔ እያለሁ እርሱ እንዲጠቀም ተደርጓል›› የሚል ስሜት ፈጥሮ መጠፋ ፋትን ያነግሳል፡፡ ይህም መንግስት አልባነት ያመጣል፡፡ ኢትዮጵያዊነትንም ያቀጭጫል በማለት ስጋታቸውን ይናገራሉ።
ዶክተር ሲሳይ ደግሞ የለውጡ እንቅስቃሴው የህግ መሰረት ቢኖረው ጥሩ ነው ይላሉ፡፡ ሹመቶች የኢህአዴግ ይሁንታ ባገኘና ህግን መሰረት አድርጎ ማከናወን ይመከራል፡፡ ስልጣንን በፍትሃዊ መንገድ ማከፋፈል መጠራጠርን ለማስቀረት፤ በድርጅቶቹ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ወደ አንድ ለመምጣት ያስችላል፡፡ በጎ ስራዎችን ማጠናከር፣ ክፍተቶችን ማረምና ማስተካከል ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
ምሁራኑ፤ምክረ ሀሳባቸውን ሲያጠቃልሉም የህግ ልዕልናን ማስከበር፣ ሰላም እንዲኖር መስራት፣ ድርጅቱን ወደ አንድ ለማምጣትም ሀላፊነታቸውን መወጣትም ይገባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በድርጅቶቹ መካከል ያለውን መገፋፋት አቁመው የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር ይገባቸዋል።
ተንቀሳቅሶ የመስራት መብት እንዲከበር ማድረግ ያስፈልጋል። ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ጠንካራ አገር አድርጎ ማለፍ ግዴታ ተጥሎበታልና ይህንን ማድረግ የሚያስችል አሰራርና ተግባር ሊይዝ ይገባል። በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የኢህዴግን ሀሳብ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2011
በዘላለም ግዛው