በኢትዮጵያ ፊልም መሠራት ከጀመረ ረጅም ዓመታት ቢያስቆጥርም በፖሊሲና በተቋም የተደገፈ ባለመሆኑ ራሱን ችሎ የሚቆም ዘርፍ ስለመሆኑ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። በተለምዶ ግን የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ ተብሎ ይጠራል።
በ1990ዎቹ ማንሰራራት የጀመረው የኢትዮጵያ ሲኒማ ዛሬም ዳዴ እያለ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። ለዚህ አንድ ማሳያ ተደርጎ የሚቀርበው ደግሞ የኢትዮጵያ ፊልም በወጣቶች ተደራጅቶ፤ ለወጣቶች የእንጀራ ገመድ ከመሆን በዘለለ በኢንዱስትሪው ላይ የሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ነው።
እስከ ቅርብ ጊዜ ለዕይታ የበቁ ፊልሞች በአማካይ አንድ ፊልም ተሠርቶ ለእይታ እስኪበቃ ድረስ ስድስት መቶ ሺህ ብር ገደማ እንደሚፈጅ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በእርግጥ አልፎ አልፎ እስከ 4 ሚሊዮን ብር የወጣባቸው ፊልሞችም አይታጡም። ነገር ግን ከአማካይ ወጪው አልፎ መበጀት የቻለ ፕሮዲውሰር፣ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቁ ፊልሞችንም የጻፈ ደራሲ፤ ገና የፊልም ኢንዱስትሪው ማፍራት አልቻለም። ያም ሆኖ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ ኢንዱስትሪው ከመቀዛቀዙ አስቀድሞ በዓመት በትንሹ ሰማንያ በትልቁ ደግሞ መቶ ፊልሞች ተሠርተው ለእይታ እንደሚበቁ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከወረርሽኙ መከሰት በኋላ እየተቀዛቀዘ የመጣው የፊልም ኢንዱስትሪ ለማንሰራራት ሲጣጣር ቢታይም በበርካታ ምክንያቶች ብዙ መራመድ አልቻለም። ለዚህ አንዱ ምክንያት ደግሞ ከጥራትና ከይዘት ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ሚዛን ይደፋሉ።
የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ራሳቸውን በሙያው ብቁ ለማድረግ በሚጥሩ ወጣት ባለሙያዎች እየተገነባ መምጣቱ አንድ ጠንካራ ጎን መሆኑን አንዳንድ ባለሙያዎች አስተያየት ሲሰጡ ይሰማል። ይህም ከጥራት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ችግሮች አንድ መፍትሄ ሊፈጥር እንደሚችል ተስፋ ተደርጎበታል። ያም ሆኖ ይህን ተስፋ የሚያደበዝዙ ስጋቶችም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢንዱስትሪው እንቅፋቶች ሆነው መታየት ጀምረዋል።
የፊልም ኢንዱስትሪው ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከወረርሽኙ በኋላ የፊልም ዘርፉ የሥራ ውጤቶቹን ለማቅረብ ከሲኒማ ወደ ዩቲዩብ እና የኢንተርኔት አማራጭ መንገዶች ፊቱን አዙሯል። ይህም ለኢንዱስትሪው የራሱ የሆነ በጎ ነገር ቢኖረውም አሉታዊ ተፅእኖው የጎላ እየሆነ ይገኛል።
ባለፉት ሦስት አስርት አመታት ኢንዱስትሪው ባደረገው ጉዞ በ1990ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ዓይነተኛ መነቃቃትአሳይቶ እንደነበር ባለሙያዎቹ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
የኢትዮጵያ ሲኒማ ለዓለም አቀፍ እይታና ተደራሽነት ለመብቃት ረዥም መንገድ እንደሚቀረው ብዙዎች ቢስማሙበትም ከቅርብ አመታት ወዲህ ያለው ጉዞ ግን የኮቪድ ወረርሽኝና ሌሎች ገፊ ምክንያቶች አንፃር በቁልቁለት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ ለማንም ግልፅ ነው።
በፊልም ኢንዱስትሪው የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ ከወረርሽኙ በኋላ የፊልም ዘርፉ የሥራ ውጤቶቹን ለማቅረብ ከሲኒማ ወደ ዩቲዩብ እና የኢንተርኔት አማራጮችን መንገዶች በስፋት እየመረጡ ነው። ይህም የዲጂታል ሚድያው አትራፊና ገንዘብ ማጋበስ የሚቻልበት መንገድ በመሆኑ በፊልም ሠሪዎች ተመራጭ መሆኑ ነው። እነዚህ አዲስ ለውጦች የፊልም ኢንዱስትሪው ለረዥም ጊዜ ሲጠቀምባቸው የነበሩትን የሲኒማ እንዲሁም የሲዲና ዲቪዲ መንገዶችን ከጨዋታ ውጪ እያደረገ ነው።
የፊልም ኢንዱስትሪው ወደ ቴሌቪዥንና በተለይ ደግሞ ዩቲዩብ ፊቱን ማዞሩ በዘርፉ የሚመረቱት የፊልም ሥራዎች ጥራት ላይ አደጋ እየሆነና ሙያዊ ብቃትም ኪሳራ ውስጥ እንዲገባ ትልቅ ምክንያት መሆኑ በግልፅ እየታየ ይገኛል።
ከወረርሽኙ በፊት አንድ በፊልም ኢንዱስትሪው የተሰማራ የፊልም ባለሙያ ፊልም ሠርቶ ጨርሶ ወደተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ከማሰራጨቱ በፊት በአንድ ሲኒማ ቤት በማስመረቅ ለእይታ ያበቃል። ከዚያም በኋላ ወደተለያዩ ሲኒማ ቤቶች አሰራጭቶ ገቢም ያገኝበታል፤ በፊልሙ ድርሻ ያላቸው ሰዎችም የሚገባቸውን ክፍያ ያገኛሉ። ከዚያም የፊልሙ ባለቤት በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ፊልሙን ለእይታ ካበቃ በኋላ ከፈለገ በራሱ ዩቲዩብ ላይ ይጭነዋል፣ ካልሆነም ለቻናል ባለቤቶች (ዩቲዩበሮች) ይሸጥላቸዋል። ይህንን በማድረግ በፊልሙ ለተሳተፉ አካላት የሚገባቸውን ክፍያ እንዲከፍል ከማስቻል ባሻገር አነሰም በዛም ለሙያው የሚመጥንና ጥራት ያለው ሥራ እንዲሠራ አድርጎት ቆይቷል።
ሆኖም ከኮቪድ በኋላ ሲኒማ ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ የፊልም ሥራው ልምድ ለዩቲዩብ የሚሆኑ ፊልሞችን ወደ ማምረት አዘንብሏል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ በተለያዩ በዩቲዩብ ቻናሎች የሚጫኑ ፊልሞች በአነስተኛና ወጪ ቆጣቢ ፕሮዳክሽን እስከ በሁለት እና ሦስት ቀናት ብቻ ባለ ጊዜ የሚሠሩበት አጋጣሚ እየሰፋ ሄዶ የጥራት ጉዳይ ውሃ እየበላው ይገኛል።
በዩቲዩብ ቻናሎቻቸው ላይ ፊልሞችን ለመጫን የሚገዙት የቻናል ባለቤቶች ለፊልሞች የሚያቀርቡት ክፍያ በፍጹም ፊልሞችንም ሆነ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎቹን የሚመጥን እንዳልሆነ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።
ከዚህ ባሻገር ፊልሞች የወረደ የጥበብ ይዘት ያላቸውና ቶሎ እይታ እንዲኖራቸው ብቻ እየተሠሩ፣ እንዲሁም ሰዎች በቀላሉ እንዲቀበሏቸው ብዙ ቁምነገር ሳያዝሉ እንዲመረቱ በር ከፍቷል። ይህም የሙያው እውቀትና ችሎታ የሌላቸው በርካቶች በድፍረት እንዲሳተፉበት እያደረገ ይገኛል።
የዩቲዩብ ፊልም ፊልሞችን ለመሥራት የሚያስፈልጉ ሂደቶችን ስለማይከተሉ፣ በቅናሽ ብር ስለሚገዙ፣ በቸልተኝነትና በለብ ለብ እንዲሁም ለትርፍ ብቻ ታስበው ስለሚሠሩ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሚገባቸውን ክፍያ እንዳያገኙ ከማድረጉ በተጨማሪ የፊልም ኢንዱስትሪው እንዲያሽቆለቁል በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
አሁን አሁን የሚሠሩ ፊልሞች በጥራታቸውም ሆነ በይዘታቸው በጣም የወረዱ እና ለፊልም ኢንዱስትሪው የማይመጥኑ ሥራዎች በብዛት እየተስተዋሉ የሚገኙትም በዚሁ ምክንያት ነው።
በተለይ ከኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ በዩቲዩብ የሚለቀቁ ፊልሞች የድምጽና የምስል ጥራት የሌላቸው፣ የማጀቢያ ሙዚቃዎቻቸው ብዙም የማይጥም፣ ወጥ የሆነ ቃለ ተውኔት እንኳን የማይታይባቸውና ክህሎት የሌላቸው ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የፊልም አሠራርን የተከተሉ ሆነዋል።
በተለያዩ የዩቲዩብ ቻናሎች የሚጫኑ ፊልሞች ብዙ እይታ እንደሚያገኙ ብዙዎች ይስማሙበታል። ሆኖም በእነዚህ ዩቲዩብ ቻናሎች የሚጫኑ ፊልሞች ጥራት ከሌላቸው እንዴት እይታ እንደሚያገኙ አስገራሚ ነው። አንድ ፊልም በዩቲዩብ ብዙ እይታ አገኘ ማለት ጥራት አለው ማለት ግን አይደለም።
በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሙያውን ሥነ ምግባር ተከትለው ኢንዱስትሪው እንዲያድግ እና በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ተግተው የመሥራት ኃላፊነት እንዳለባቸው እሙን ነው። ሆኖም በፊልም ሥራ ላይ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች በተለይ የዩቲዩብ ፊልሞች ከመጡ በኋላ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሥነ ምግባር ክፍተት እንደሚታይባቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ።
በሌላው አገር ላይ ፊልም ሲባል፣ ሕዝብና ባለሙያው አይደለም መንግሥት ራሱ ስለዘርፉ በደንብ አድርጎ ይገነዘባል። የፊልም ዘርፍ ትልቅ ገበያ መሆኑን የተረዱ ብዙ አገራትም ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ትምህርት ቤቶችን፣ ስቱዲዮ እንዲሁም ዕቃዎችን ያሟላሉ። እኛ ጋር ግን የተገላቢጦሽ ነው። ዘርፉን መቶ በመቶ ተሸክመው የሚጓዙት በራሳቸው የሚጥሩ ባለሙያዎች ናቸው። በዚህ መንገድ የተሠራ ፊልም ደግሞ ውጤቱ ውስንና ደካማ እንደሚሆን ግልፅ ነው።
የአገራችን ፊልም ዘርፍ ገብተው ከሚሠሩ ተዋናዮች ብዙዎች የሚሞገሱና የሚወደዱ ባለሙያዎች አይጠፉም። እሱ ወይም እሷ ያለችበት ፊልም ከሆነ ያምራል የሚባልላቸው ተዋናዮች ስለመኖራቸው መካድ አይቻልም። በአንጻሩ ደግሞ በቀላሉ ዕድሉን ስላገኙ ብቻ ወደ ፊልም ሥራው ዘው ብለው የሚገቡ ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው። እንደሌሎች አገሮች እጅግ ትልቅ በሆነ የፊልም ትምህርት ቤት ተምሮና በተደራጀ ሥርዓት ውስጥ ገብቶ የሚሠራ ባለሙያ አለ ብሎ ለመናገር ከባድ ነው። ይህም ተዋናዮች ወደ ዘርፉ የሚመጡበት መንገድ ደካማ እና የፊልም ሳይንሱ በሚጠይቀው መንገድ ከመሄድ ይልቅ በባህላዊ መንገድ መሆኑን ያሳያል። እዚህ ችግር ላይ አሁን ስጋት እየሆነ የመጣው የዩቲዩብ ጉዳይ ሲጨመር ወትሮም ህፀፅ የማያጣው የፊልም ኢንዱስትሪ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲያመራ ይበልጥ ሁኔታዎች ምቹ እየሆኑ እንዲሄዱ ማድረጉ አይቀርም።
ትክክለኛ ፊልም ለመሥራት ቢያንስ ዘጠኝ ወር እንደሚፈጅ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። ይህም ሦስት ወር ለቅድመ ዝግጅት፣ ሦስት ወር ለቀረጻና ሦስት ወር ለአርትኦት የሚጠይቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ ተግባራዊ ሲሆን አይታይም። እንዲያውም አሁን አሁን አንድ ፊልም ካፌ ውስጥ ወይም ኮንዶሚንየም ውስጥ ታስቦ ያልቃል ተብሎ ይታማል። በዚህ ላይ አንድ ተዋናይ በሆነ ምክንያት ቢያቋርጥ አንዱ ብድግ ብሎ የሚቀጥልበት ሁኔታም ከፊልሞች ባሻገር ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ጭምር እንዲስተዋል አድርጓል።
ኢንዱስትሪው ወትሮም በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በአመጋገብና በአለባበስ ውስጥ ያለውን አገራዊ የኪነጥበብ ሀብት ወደ ፊልም በመቀየር ረገድ ያለበትም ክፍተት ሙያው እያደገ ሲመጣ ይቀረፋል የሚል ተስፋ ቢኖረውም በተቃራኒው ሌላ እንቅፋት ከፊቱ ገጥሞታል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ መንግሥትና ባለሙያዎች በአንድ መስመር አብረው መሮጥ ከቻሉ ዘርፉን መታደግ የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው። በዚህም የአገርን ገጽታ ለመገንባት፣ የቱሪዝም ገበያውን ለማስተዋወቅ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ይቻላል።
ባለሙያዎች እንደሚሉትም፣ የአገርን ገጽታ ከፍ አድርገው የሚያሳዩና በዓለም አቀፍ የፊልም መድረኮች ላይ ተገኝተው ለዓለም መታየት የሚችሉ የፊልም ጽሑፎች ይመጣሉ። ነገር ግን፣ በተለይ ጽሑፉን ወደ ፊልም ለመቀየር አስቸጋሪ በሆነው የአገራችን ቢሮክራሲና በወጪው ምክንያት የሚሠራው የታሰበው ሳይሆን የተቻለው ብቻ ነው።
ብዙ ባለሙያዎችም እስኪሰለቻቸው ድረስ ዘርፉ ባለቤት እንዲኖረውና በተቋም እንዲመራ መንግሥትን ሲወተውቱ እንደቆዩ ይናገራሉ። መንግሥት የፊልም ኮሚሽን አቋቁሞ አገሪቱን የሚያስተዋውቁ ሥራዎችን ማበረታታትና የፊልም ወርክሾፖችንና ትምህርት ቤቶችን መደገፍ እንዳለበት አስፈላጊ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
መንግሥት ይህንን ዘርፍ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የአገሪቱን ባህል ለሌሎች ለማስተዋወቅ፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሊጠቀምበት ይችላል። ለዚህ ደግሞ የደቡብ አፍሪካንና የናይጄሪያን ልምድ ማየት በቂ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የፊልም ቁሳቁስ ላይ የሚጣሉ ቀረጦች ላይ ማስተካከያ ቢደረግ የአገር ውስጥ ፊልም ሠሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ባለሙያዎችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሠሩ በማበረታታት የውጭ ምንዛሪ ሊገኝ ይችላል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም