በዛሬው ‹አዲስ ዘመን ድሮ› ዓምዳችን በ1965 በታኅሣሥ ወራት ለንባብ የበቁ ዘገባዎችን መርጠናል። ከመረጥናቸው ዘገባዎች አብዛኞቹ ወንጀል ነክ ናቸው። ግርምትም የሚያጭሩና ጥያቄን የሚፈጥሩ አሳዛኝ ክስተቶች በወቅቱ ተዘግበዋል፡፡
እኅትማማቾች በካቲካላ ሞቱ
ወይዘሪት ብዙነሽ ገብሬና ወይዘሪት እመቤት ገብሬ የተባሉ እኅትማማቾች ፤የእህል አረቄ ጠጥተው ለሞት ያበቃቸው ወላጅ እናታቸው አረቄውን ካወጡ በኋላ አልጋ ሥር አስቀምጠውት ወደ ገበያ ሲሄዱ ከተቀመጠበት ቦታ አንስተው በመጠጣታቸው ነው። ሟቾቹ አረቄውን እንደጠጡ በያሉበት ተዘርረው ወድቀው ነበር፡፡ በኋላ ግን ሰው ደርሶ ለሕክምና ፍቼ ጤና ጣቢያ ተወስደው ሕክምና ቢደረግላቸውም ለመዳን ተስፋ በማጣታቸው በ፲ ሰዓት ልዩነት ሁለቱም ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በሁለቱ እኅትማማቾች ላይ ይህ የሞት አደጋ የደረሰው፤ታኅሣሥ ፬ ቀን ፲፱፻፷፭ ዓ/ም በሰላሌ አውራጃ በግራር ጃርሶ ወረዳ በፍቼ ከተማ ውስጥ ነው። ወይዘሪት ብዙነሽ ገብሬ ዕድሜዋ ፰ ሲሆን ወይዘሪት እመቤት ደግሞ ፮ ዓመት መሆኑን የማስታወቂያ ክፍሉ ባገኘው ሪፖርት መሠረት አስረድቷል፡፡
(ታኅሣሥ 21 ቀን 1965 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ቤት ሰርሳሪ የገደሉት ተቀጡ
ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን ቤታቸውን በመጋዝ ቆርጦና በፋስ መጥረቢያ ሰርስሮ ሲገባ ነቅተውበት በዱላ ደብድበው የገደሉት ሰዎች በወንጀለኝነት ተከሰው እሥራት ተፈረደባቸው፡፡
አቶ ታደሰ መንግሥቱና አቶ ሁንዴ ፈይሳ የተባሉት የገደሉት ተመቸ ቅጣው የተባለው፤በፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል የሌብነት ሪኮርድ ያለው መሆኑ ታውቋል።
ተከሳሾቹ ሌባውን የገደሉት አቶ ቸርነት አርጋው የተባሉትን ሰው ቤት ሰርስሮ ሲገባ ቢነቁበት ባለቤቱን በመጋዝ ሊቆርጣቸው በመሞከሩም መሆኑ ተገልጧል። ሟቹ የሌብነት ወንጀል ሲፈጽም የተያዘው አዲስ አበባ ቀበና ቀበሌ ከአፈ ንጉሥ አረጋ ቤት አጠገብ መሆኑን አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተመስክሯል። ተከሳሾቹ ሌባው ቤት ሰርስሮ ሊገባ ሲል ነቅተው ይዘውት በመተባበር በዱላ መደብደባቸው አምነዋል። በሰው ምስክርም ተረጋግጦ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፪ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው እያንዳንዳቸው በ፪ ዓመት እሥራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፡፡
(ታኅሣሥ 18 ቀን 1965 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ባለ መኪና አስገድደው ቀሙ የተባሉት ፍርድ ቤት ቀረቡ
በሌሊት ከመሐል አውራ ጐዳና ላይ እየቆሙ በማስገደድ ባለተሽከርካሪዎችን ቀምተዋል በመባል የተከሰሱት አቶ ዳኘ ደቻሳ፤ አበበ ነጋሽ፤ ጥላሁን እሸቴና ተስፋዬ ገብሬ ወህኒ ቤት ገቡ፡፡
አራቱም ተከሳሾች መጋቢት ፫ ቀን ፲፱፻፷፭ ዓ-ም ከምሽቱ ፭ ሰዓት ተኩል ሲሆን አዲስ አበባ ፮ኛ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ አቶ ዓለማየሁ ዳምጤ የተባሉት ሰው መኪናቸውን በማስገደድ አስቁመው 791110 የሆነ ሽጉጥ መንጠቃቸውን የቀረበባቸው የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጣል።
እነ ዳኘ ሰላማዊውን ሰው መኪናቸውን ከአስቆሙ በኋላ አባሪ ሆነው ከመኪናው ውስጥ በማንገላታት አስወጥተው ሽጉጣቸውን ከ፫ ጥይት ጋር ቀምተው ወስደው በፖሊስ መከታተል መያዛቸውን የአዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፪ኛ ወንጀል ችሎት ተመስክሮባቸዋል፡፡
አራቱ ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀርበው በሰጡት ቃል ጥፋተኞች አለመሆናቸውንና ወንጀሉንም አለመፈጸማቸውን አመልክተዋል፡፡ የችሎቱ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ አመሠራረት የሚያስረዱ ምስክሮች መኖራቸውን ገልጠው ምስክር መስማት ተጀምሯል።
(ታኅሣሥ 4 ቀን 19 65 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
በጥጃ ምክንያት የ9 ልጆች እናት
ወህኒ ቤት ገቡ
በአንዲት የሞተች ጥጃ ምክንያት በተነሣው የወንጀል ክርክር አንዲት የ፵ ዓመት ሴት ፤ዘጠኝ ልጆቻቸውን ጥለው ወህኒ ቤት መግባቸውን ከአዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተገኘው ዜና ታውቋል፡፡
እመት እልፍነሽ ወልደየስ የተባሉት የልጆች እናት ወህኒ ቤት ለመግባት ዋና ምክንያት የሆነባቸው አንዲት ጥጃ ገዝተው አርደዋል ተብለው ተከሰው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ነው፡፡
በተከሳሿ ላይ የቀረበው የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያመለክተው ፤ጥጃዋ ከታረደች በኋላ ተደርሶበት የቀረቡት ምስክሮች ቆዳዋ የተገኘው ጥጃ እመት ጌጤ የተባሉትን ሴት ጥጃ ትመስላለች በማለት ምስክሮች ባሰሙት ቃል ብቻ መሆኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፫ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ይገልጣል፡፡
እመት እልፍነሽ ፤በሞተች ጥጃ ምክንያት ተከሰው አዲስ አበባ አውራጃ ፍርድ ቤት ቀርበው በ፫ ወር እሥራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸው ወህኒ ቤት መግባታቸውን የተከሳሿ ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የይግባኝ ማመልከቻ ገልጠዋል፡፡
(ታኅሣሥ 18 ቀን 1965 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2015 ዓ.ም