እናንተዬ አውደ አመት ሲመጣ ምን ትዝ ይላችኋል? ዳቦው፣ ጠላው ቀጤማው … የምትሉ እንዳላችሁ አስባለሁ፤ ግን ደግሞ እነዚህ ሁሉ የአብዛኞቻችሁ እንጂ የሁላችሁም መልስ እንዳማይሆኑ እገምታለሁ።
ዓመት በዓል ከእነዚህ ከምናያቸው ባለፈ የራሱ ድባብም አለው፤ በበአሉ አቅራቢያ ሰሞን ያለው የገበያ ግርግር እንዲሁም የእንኳን አደረሳችሁ ሰላምታና ስጦታ የበአል ልዩ ድምቀትና የአውደ አመት ገፀ በረከቶች ናቸው።
መቼም ዓመት በዓል ምን ምን ይሸታል ብሎ የሚጠይቅ አይኖርም። ከድፎ ቅጠል እስከ ዶሮ፤ ከጠላ እስከ ጠጅ፣ ምን ይሄ ብቻ እጣኑ፣ ቀጤማው፣ ጠጅ ሳሩና ሌላውም ተደማምሮ አውደ ዓመት የራሱ መለያ ሽታ እንዳለው አመላካች ነው።
‹‹እና ይሄ ምን አዲስ ነገር አለው፤ ዘመናትን ያሳለፍንበት የኢትጵያዊነት መለያችን ነው›› የሚለኝ አይጠፋም። መቼም ለአንዱ ጥሩ ትዝታ ለሌላኛው ትርጉም አልባ ሊሆን ይችላል። ይሁንና በዓል ሲመጣ እኔን ስለሚያስገርመኝ ነገር ላውጋችሁ።
ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የእኛ ቤት በዓል አከባበር ሁለት መልክን ይዟል። ከዋዜማው እስከ በዓሉ እለት ያለው ሁነት የደስታችን ምንጭ ሲሆን፤ ከበዓሉ በኋላ ያሉት ተከታታይ ቀናት አንዳንዴም ሳምንታት ግን የጭንቃችን ምክንያት ሆነዋል።
ለዚህ የሁለት አይነት ስሜቶች መፈጠር ምክንያት አለው። እህቴ የመተንፈሻ አካል ችግር (ሳይነስ) አለባት። ድሮ ህመሟ ጠንካራ አልነበረም፤ ብዙ ጊዜም እኛም ሆንን እሷ አናስታውሰውም ነበር። ከዓመታት በኋላ ግን ልጅ መውለዷን ተከትሎ ህመሙ እሷ ላይ ጠንከር ሲል የልጇ ደግሞ ይበልጡን ተባባሰ።
የሚገርመው የሁለቱም ዋነኛ የህመም መነሻ ከበዓል በኋላ በየአካባቢው የሚጣሉ የእርድ ተረፈ ምርቶች ሽታ መሆኑ ነው። ታዲያ በዓል በመጣ ቁጥር የእኛ ቤተሰብ ቤትና ግቢ ብቻም ሳይሆን በሰፈሩ መንገድ ዳርቻ የተጣሉ ሽታ አምጪ ተረፈ ምርቶችን ማስወገድ ሆኗል።
ግን ደግሞ ከየት እንደሚመጣ የማይታወቅ ነፋስ ይሄን ጦሰኛ እንግዳ ከየትም ብሎ እቤት ያደርሰዋል። እናም ከአብዛኛዎቹ በዓላት መጨረሻ ሆስፒታል መገኘት ለእኛ ቤተሰብ የግድ ከሆነ ከራርሟል።
ለዚህም ይመስላል ለዓመት በዓል ‹ልብስ ይገዛልሻል› የተባለችው የአምስት ዓመቷ የእህቴ ልጅ ‹ዓመት በዓል መጣ እንዴ? በዓል እኮ መጀመሪያ ደስ ይላል፤ በኋላ ግን ደስ አይልም› ስትል የተደመጠችው።
የዓውድ ዓመት ሁለት መልክ ይሉሃል እንዲህ ነው። ለመሆኑ ስንቶቻችን ነን እንደቀልድ እያወጣን የምንጥላቸው ቆሻሻዎችች ሌሎችን ለችግር እንደሚያጋልጡ የምናውቀው?
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ