በዓለማችን ላይ የሚካሄዱ የቱሪዝም ነክ ስፖርታዊ ሁነቶች ከፍተኛ ምጣኔ ሃብት የሚንቀሳቀስባቸው ናቸው። “ግሎባል ማኔጅመንት ኮንሰልታንት ኤቲ ኬርኒ” የተባለ ተቋም ዘርፉ በዓለማችን ምጣኔ ሃብት ላይ የ620 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ እንዳለው በጥናቴ አረጋግጫለሁ ይላል። ይሄ በጥቅል የቱሪዝም ዘርፍ ካለው 4ነጥብ5 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስድ ንኡስ ዘርፍ እንደሆነም አያይዞ ገልጧል።
መዋለ ነዋይን በማንሸራሸር ከሚኖረው ተፅእኖ ባሻገር የስፖርት ቱሪዝም የአገራትን የመስህብ ስፍራና መዝናኛዎች እንዲሁም ለጉብኝት ተመራጭ የሆኑ አካባቢዎችን ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሆነ “The Impact of Sports Tourism & Future Trends” በሚል ርእስ ስር የወጣው ፅሁፍ ያመለክታል።
ስፖርት ቱሪዝምና ምጣኔ ሃብት
መዝናኛን፣ የጤና መሻሻልንና ውድድርን መሰረት የሚያደረጉ ስፖርታዊ ሁነቶች ማህበረሰቡ ውስጥ በቀጥታ ምጣኔ ሃብታዊ አቅም በመፍጠር ልዩ ድርሻ ያበረክታሉ። በጉዞና በጉብኝት ኢንዱስትሪ ውስጥ ስፖርትን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጉብኚዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እድገት እያሳዩ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለዚህ ነው “የአክቲቭ ሚዲያ” ቡድን አባላት “በሰራነው ዳሰሳዊ ጥናት በየዓመቱ ቢሊዮን ዶላር እንደሚንቀሳቀስ አረጋግጠናል” በሚል ሃሳባቸውን የሚሰጡት።
ፕሉንኬት (Plunkett Research Group) የተባለ አጥኚ ቡድን ዘርፉ ላይ ባደረኩት ዳሰሳዊ ጥናት አገኘሁ ባለው መረጃ መሰረት የዓለም ዋንጫን፣ ኦሎምፒክንና የአውሮፓ ዋንጫን የመሳሰሉ ተወዳጅ ስፖርቶችን ጨምሮ ዓለማችን ላይ በሚካሄዱ ሁነቶች ምክንያት አገራት ረብጣ ገንዘብ ያወጣሉ። በምላሹ ግን በርካታ ቢሊዮኖችን ከስፖንሰር፣ ቱሪስቶችና መሰል አካላት ያገኛሉ።
“አይ ኢ ጂ” የተባለ የስፖርት አማካሪ ተቋም በበኩሉ በስፖርትና ስፖርት ቱሪዝም ላይ በዓለማችን የሚደረገው የስፖንሰር ሺፕ አሃዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው። አሁን ላይ ይህ አሃዝ ወደ አራት ነጥብ ስድስት ተመንድጎ 60 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል።
ስፖርታዊ ሁነቶች በንግድ፣ በጤናና በመዝናኛው ዓለም ላይ ተፈላጊ እየሆኑ በመምጣታቸው ይህንን መሰረት ያደረገ የቱሪዝም ጉዞ በፍጥነት እድገት እያሳየ መጥቷል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በልዩ ልዩ ክፍሎች ስፖርታዊ ሁነቶች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሄም አሁን ካለው መጠን ስድስት በመቶ ጭማሪ ያሳያል።
ይህንን አሃዝ በገንዘብ ቀይረን ስናስቀምጠው የበለጠ ምስል የሚሰጠን ይሆናል።
የብሄራዊ ስፖርት ኮሚሽን ማህበራት (ኤን ኤ ኤስ ሲ) ሰራሁት ባለው የዳሰሳ ጥናት በአሜሪካን አገር ብቻ የስፖርት ቱሪዝምን መሰረት አድርገው ከተጓዙ 25 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ስምንት ነጥብ 96 ቢሊዮን ዶላር እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2015 ዓመት ብቻ ተገኝቷል። ይህ አሀዝ የሚያሳየው በዘርፉ ጠንከር ያለ ሁነት የማዘጋጀትና የማስተዋወቅ ሥራን ማከናወን ከተቻለ አገራት ምጣኔ ሃብታቸውን የሚደግፍ አቅምን ከስፖርት ቱሪዝም ማግኘት እንደሚችሉ ነው። ከዚህ ባሻገር ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ሌሎች የመስህብ ሃብቶቻቸውን ለቀሪው ዓለም በማስተዋወቅ ገፅታቸውን መገንባትም ይችላሉ።
ኢትዮጵያ- የስፖርት ቱሪዝም
ኢትዮጵያ በስፖርቱ ዓለም ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ልምድ አላት። በተለይ በዓለም መድረክ ላይ ባንዲራዋን እያውለበለቡ የሚገኙ ብርቅዬ አትሌቶች የሚገኙባት ነች። አትሌት አበበ ቢቂላ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ማሞ ወልዴ፣ አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረ ስላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ መሰረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባና ሌሎችም ተወዳጅ አትሌቶች በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያ ስም ገኖ እንዲሰማ ምክንያት ከመሆን ባሻገር በአትሌቲክ ስፖርት እምቅ አቅም እንዳላት ያሳዩ ናቸው። ይህ እውነት አሁንም ድረስ የዘለቀና ኢትዮጵያ የአትሌቶች መፍለቂያ መሆኗን ያስመሰከረ ነው።
በዚህ ምክንያት ምቹ የመለማመጃ መልከዓምድር ለማግኘትና የኢትዮጵያውያንን አገር ለመጎብኘት ጥቂት የማይባሉ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የስፖርት ቱሪዝምን መሰረት አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ።
በተጨማሪም በታዋቂው አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ በተመሰረተውና ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” ላይ ከአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እንዲሁም ከመላው ዓለም የሚመጡ ጎብኚዎች፣ በኢትዮጵያ መቀመጫቸውን ያደረጉ ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮችን ጨምሮ ለጤናና ለደህንነት እንዲሁም መዝናናትን መሰረት ያደረጉ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ተሳታፊ ይሆናሉ።
ምንም እንኳን የአትሌቲክስ ስፖርት የአንበሳውን ድርሻ ቢወስድም የስፖርት ቱሪዝምን መነሻ በማድረግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልዩ ልዩ ስፖርቶች እየተስፋፉ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ ውስጥ ተራራ መውጣት (ሃይኪንግ)፣ የብስክሌት ቱር፣ የወንዝ ላይ የጀልባ ቀዘፋ (ራፍቲንግ) ይጠቀሳሉ። በዚህ መነሻ ምክንያት የስፖርት ቱሪዝም ሁነቶች ላይ የሚሳተፉ የአገር ውስጥና የውጪ አገራት ጎብኚዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ መረዳት እንችላለን። የስፖርት ቱሪዝም በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ለማድረግ እየተሰሩ ካሉ የቅርብ ጊዜ ሙከራዎች መካከል አንዱን በምሳሌነት እናነሳለን።
ቱሪዝም ሚኒስቴር
የቱሪዝም ሚኒስቴር የገበያ ልማትና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት መስሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የስፖርት ቱሪዝም አቅም ለመጠቀም የሚያስችሉ የአሰራር ማዕቀፎችን እያዘጋጀ እንደሚገኝ በያዝነው ዓመት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በተካሄደበት ወቅት መግለጻቸው ይታወሳል። ይህ መረጃ የሚያመለክተው ኢትዮጵያ በስፖርት ቱሪዝም ዘርፍ በዓለም ላይ የሚንሸራሸረውን ከፍተኛ ገንዘብ ተጫርታ ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅሙን ለማግኘት ከምታደርገው ጥረት ባሻገር መልካም ገፅታን ለመገንባትና የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ እንደምትሰራ ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት በሃዋሳ ከተማ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ከልዩ ልዩ የአገሪቱ ክፍሎች በስፍራው ከተገኙ የአገር ውስጥ የስፖርት ቱሪዝም ተሳታፊዎች ባሻገር 300 የሚደርሱ የውጪ ዜጎች ተገኝተዋል። ይህንን አቅም ለማሳደግና ማህበረሰቡ ከዚህ መሰል ሁነቶች ተጠቃሚ እንዲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከውድድር አዘጋጁ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል። ሃዋሳን የመሰሉ የቱሪዝም መስህብ በስፋት የሚገኝባቸው መሰል ከተሞች ላይም ተሞክሮውን ለማስፋት በጋራ ይሰራሉ።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ
ዳግማዊት አማረ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ነች። ታላቁ ሩጫ በአዲስ አበባ ከሚያካሂደው ዋናው የጎዳና ላይ ሩጫ በተጨማሪ በሃዋሳ ለ11ኛ ጊዜ ስፖርት ቱሪዝምን መሰረት በማድረግ የግማሽ ማራቶን የአዋቂዎች ሩጫ ውድድርን ማካሄዱን ትናገራለች። የቱሪዝም ሚኒስቴርም ዘንድሮ ይፋ ያደረገውን “ልወቅሽ ኢትዮጵያ” የአገር ውስጥ ቱሪዝምን የማስተዋወቅ ንቅናቄ ምክንያት በማድረግ አብሯቸው እየሰራ መሆኑን ትገልጻለች።
“ስፖርታዊ ውድድሮች ቢስፋፉ እግረ መንገድ ማህበረሰቡ አገሩን እንዲያውቅና የዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨምር እድል ይከፍታል” የምትለው ዳግማዊት፤ ይህንን መሰረት በማድረግ ከቱሪዝም ሚኒስትር ጋር በመሆን በሀዋሳ ከሩጫው ባሻገር በታቦር ተራራ ላይ የእግር ጉዞ መደረጉን፣ የሃዋሳ ሃይቅን በደንብ በሚያሳይ ስፍራ ደግሞ ከነዋሪዎች ጋር የጋራ ባህላዊ ስርዓትን ያካተተ ትውውቅ ማድረግ መቻሉን ትገልፃለች። በውድድሩ ላይ የውጭ ጎብኚዎች፣ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሶስት ሺህ አምስት መቶ የሚደርሱ ተሳታፊዎች እንደነበሩም ተናግራለች።
የቱሪዝም ዋናው ግብ ማህበረሰቡን በምጣኔ ሃብት መጥቀምን ጨምሮ የመስህብ ስፍራዎችን ማስተዋወቅና ተደራሽ እንዲሆኑ ማስቻል ነው የምትለው ዳግማዊት፤ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባሳለፍነው ሳምንት በስፖርት ቱሪዝም ይህንን ልምምድ ለመፍጠር መንቀሳቀሳቸውን ትናገራለች። ከታላቁ ሩጫ ቀጥሎ በዓለም አቀፍ ውድድር የተመዘገበው የሀዋሳ የግማሽ ማራቶን ሩጫ መሆኑን ገልፃም የቱሪዝምን ፍሰት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጨመርም ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ትናገራለች።
“ለአስራ አንደኛ ጊዜ በተካሄደው የሀዋሳ ሩጫ ላይ የዴንማርክና የኖርዌይ አምባሳደሮች ተሳትፈው አገሪቱን በማህበራዊ ገፃቸው ለቀሪው የዓለም ክፍል አስተዋውቀዋል። የአሜሪካዋ አምባሳደር በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ አዲስ አበባ ላይ ተሳትፋለች” የምትለው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ዳግማዊት፤ ይህንን ልምድ ለማስፋት እየሰሩ መሆናቸውን ትገልፃለች። ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጋር በጋራ በመሆን ወደ ሌሎችም አካባቢዎች ለማስፋትና የስፖርት ቱሪዝም ጽንሰ ሃሳብን ለማስተዋወቅ እንደሚሰራም ትናገራለች። ለአሁኑ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ከሃዋሳ ቀጥሎ በበቆጂ ተመሳሳይ ሁነት እየተዘጋጀ እንደሆነም ጠቁማለች።
“የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማነቃቃት የስፖርት ቱሪዝምን መሰረት አድርገን የምናዘጋጃቸው ሁነቶች ወሳኝ ናቸው” የምትለው ዳግማዊት እንደ ታላቁ ሩጫ የሀዋሳን ውድድር “የሀዋሳ ሃይቅ” (lake hawassa) በሚል አዲስ ስያሜ የሲዳማንና የከተማዋን አጠቃላይ የመስህብ ሃብቶች በሚያስተዋውቅና ለማህበረሰቡ ቀጥታ የምጣኔ ሃብት ጠቀሜታን በሚሰጥ አግባብ ለማዘጋጀት እቅድ መያዛቸውን ጠቁማለች። በተመሳሳይ በበቆጂ በቀጣዩ ግንቦት ወር ላይ ተመሳሳይ ውድድር እንደሚያዘጋጅም ነው ያስታወቀችው።
የሀዋሳን የሩጫ ስያሜ መቀየር ያስፈለገው ዓለም አቀፍ ቱሪስቱ በከተማዋና በዙሪያዋ ያለውን ሃይቅ እንዲያውቅና በዚያውም የጉብኝት እቅድ ይዞ ቆይታውን እንዲያራዝም እድል ስለሚፈጥር ነው የሚል ሃሳብ የሰጠችው ዳግማዊት፤ በደቡብ አፍሪካ ቱ ኦሽንስ ማራቶን /“Two Oceans Marathon” /የሚል ስያሜ ውድድር የአገሪቱን የቱሪዝም መስህብ ለማስተዋወቅ ባለመ መልኩ እንደሚካሄድ በተመሳሳይ በዚምባቡዌ ቪክቶሪያ ፎልስ ማራቶን /“Victoria Falls Marathon” /መኖሩ በምሳሌነት በማንሳት ይህን መሰል የስፖርት ቱሪዝም በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁማለች።
“ቱሪዝም ሁነቶችን በማዘጋጀትና በማስተዋወቅ “ወቅት መፍጠር” ነው የምትለው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ፤ የካቲትን በምሳሌነት አንስታ በሀዋሳ በየዓመቱ ይህን ወቅት መፍጠር ከተቻለና ይህንን ልምድ በሁሉም ክልሎች በመውሰድ በተለያዩ ጊዜያት የሚካሄዱ ስፖርታዊ ሁነቶችና ወቅቶችን በማስተዋወቅ ዓመቱን ሙሉ የማያቋርጥ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ መፍጠር ይቻላል የሚል እምነት አላት። የታላቁ ሩጫም በዚህ ዙሪያ የበኩሉን እንደሚወጣም ተናግራለች።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም