የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞው መደበኛ ሥራውን ለማከናወን የሚያስችሉ በርካታ አጋዥ ስኬቶችን መጎናፀፉን አስታወቀ።
የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሳው ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የችግሮችን መንስዔ በመለየት ማስተካከያ ከተደረገ ወዲህ ተቋሙ የውስጥ አሠራሩን በማስተካከል ለሚያከናውናቸው መደበኛ ተግባራት ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አስረድተዋል።
ሚኒስትሯ የምሥራቅ አፍሪካ ግንኙነት መሻሻሉ ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን፣ የመቶ ቀን ዕቅድና ስትራቴጂን ለመተግበር የሚያስችል አሠራር መዘጋጀቱ፣ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ካሉ ተጠሪ ተቋማትና ከክልሎች ጋር ተባብሮ መስራት መቻሉ፣ ተቋማቸው ለውጡን ለማስቀጠል አዋጆችንና ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀቱ፣ ባህላዊ እሴቶችን እንደኪነጥበብ፣ ስፖርትና ቅርሶችን ማስተዋወቅ ለአንድነትና ለሰላም ግንባታ ለማዋል መሰራቱ ለውጡን ለማምጣት ማስቻሉን ተናግረዋል።
ለውጡ ያስገኛቸው ሀገራዊና ታሪካዊ ድሎች ለሰላምና ለቱሪስቱ መጨመር ጥቅም ላይ መዋላቸው፤ ተቋሙ የሆቴል ኮከብ ምደባን በራስ አቅም መፈጸም መቻሉ፣ ከሕዝብ ተጠቃሚነት አንጻርም የአድዋ፣ የሉሲንና የተለያዩ የባህል ፌስቲባሎችን በተለያዩ ቦታዎች በማዘጋጀት የኅብረተሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የማመጣጠን ሥራ መሰራቱን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
ሚኒስትሯ የሠራተኛው የእርስ በእርስ ግንኙነት ጠንካራ መሆን፣ ሪፖርቶች ግልጽና ትክክለኛ መሆናቸው፣ አመቺ የሥራ ሁኔታ መፈጠሩና በተቋሙ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አካሔድ መዘርጋቱ ለውጡ ያስገኛቸው መልካም ጅምሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሯ ባለፉት ጊዜያት የታዩት የዜጎች መፈናቀልና የፓርኮች መቃጠል በዘርፉ ላይ አሉታዊ ጥላን ያጠሉ መጥፎ ክስተቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ መንግሥት ወንጀለኞችን መጠየቅ እንዳለበትና ኅብረተሰቡም ለሕግ ተገዢ ሆኖ መጠቀም እንዳለት አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2011
በኢያሱ መሰለ