ከሥር ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቢሄድም ክርክሩ መቆጫ አላገኘም። ከጉዳዩ መወሳሰብና ባለጉዳዮች ግራ ቀኙን ጠበቃ አቁሞ መከራከር እና የነገሩ መካረር አሁንም ወደ ቀጣዩ የፍርድ ሂደት ሊያመራ ግድ ሆነ። ወደ ሰበር ችሎትም ደረሰ። ጉዳዩም መዝገብ ተከፍቶለታል። የሰነድ መለያ ቁጥር 32899 የተሰጠው ሲሆን ግንቦት 21 ቀን 2000 ዓ.ም ሰበር ችሎት የመጨረሻውን ውሳኔ ሊያሳርፍ ነው።
አብዱልቃድር መሐመድ፣ መስፍን ዕቁበዮናስ፣ መድህን ኪሮስ፣ ዓሊ መሐመድ እና ሱልጣን አባተም የተሰኙት ዳኞች ከችሎት መንበሩ ላይ ተሰይመዋል። አመልካች ወይዘሮ አስካለማርያም ታደሰ እና ተጠሪው አቶ ተሾመ ካሣዬ በአካል ቀርበው ሰበር የሚለውን የሚበይነውን የመጨረሻ ውሳኔ ለመስማት ጓጉተዋል። በዛሬው የዶሴ አምዳችን የምንቃኘው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች በ2001 ዓ.ም ቅፅ 7 ካሰፈራቸው የፍርድ ሂደቶችና ውሳኔ የተመለከተ ይሆናል።
ጉዳዩ
ጉዳዩ የተጀመረው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን አመልካች በመጋቢት 5 ቀን 1998 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ ተከሳሽ በሱሉልታ ሙሎ ወረዳ የማህበር አባል ነኝ በማለት ድርሻዬ ነው ያሉትን ቦታ በብር 18,400 (አስራ ስምንት ሺህ አራት መቶ) ሸጠውልኝ የቦታውን ካርታ አስረክበውኛል። ቦታውን አጥሬ ለመስራት ስሞክር ግን ቦታው የተገኘው በሕገ ወጥ መንገድ ነው በማለት የመሬት አስተዳደር ቦታውን ወርሶብኛል። በመሆኑም ተከሳሽ ገንዘቤን እንዲመልስልኝ ይወስንልኝ የሚል ክስ ነው።
ተጠሪው ሌላ ቤት የገዛባቸው አቶ ኤልያስ ደምሴ የተባሉት ተከሳሽ ደግሞ በሰጡት መልስ ይህ ክስ መቅረብ የሚገባው በቤት ሥራ ማህበሩ እንጂ በእኔ ላይ አይደለም። ከሣሽ ካርታውን የተቀበሉት ከማህበሩ እጅ በመሆኑ ስለቦታው ሕጋዊነት መጠየቅ ያለባቸው ማህበሩ ነው። በክሱ የተጠቀሰውን ገንዘብ ከከሳሽ አልተቀበልኩም በማለት ተከራክረዋል። ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠና ማስረጃም ከሰማ በኋላ ተከሳሽ ገንዘቡን መቀበላቸውንና በውላቸው ደግሞ ቦታውን ለከሣሽ ካላስረከብኩኝ ገንዘቡን እመልሳለሁ በማለት ግዴታ መግባታቸውን በማስረጃ ስለተረጋገጠ በክሱ የተጠቀሰውን ገንዘብ ለከሳሽ ይክፈሉ ሲል ወስኗል።
በመቀጠልም ፍርድ ቤቱ ተጠሪውን በተከሳሽ ስም የተመዘገበው ቤት የገዛሁት በመሆኑ እግዱ ይነሳልኝ በማለት አመልክተውም ነበር። አመልካችም ደግሞ በተከሳሽ ላይ ቀደም ብሎ የወሰዱት ገንዘቤን እንዲመልሱልኝ ያስወሰንኩኝ በመሆኑና ቤቱም ተሸጦ ገንዘቤን የማስመልስበት የተከሳሹ ሃብት በመሆኑ እግዱ መነሳት የለበትም በማለት ተቃውመዋል።
ፍርድ ቤቱም አቶ ተሾመ ካሣዬ ገዛሁት የሚሉትን ቤት የሽያጭ ውል ስልጣን ባለው አካል ያልተመዘገበ በመሆኑ የሽያጭ ውሉ በፍትሐብሔር ቁጥር 2878 መሠረት ውጤት የለውም። እግዱ በቀረበው አቤቱታ መልኩ ሊነሳ የሚችልበት ምክንያት የለም በማለት ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀርቷል።
ይግባኝ ለችሎት
በዚህ የእግዱ ይነሳልኝ ጥያቄ መሠረት ተጠሪው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው ፍርድ ቤቱም ይግባኝ ባይ ቤቱን ከአቶ ኤልያስ ደምሴ መስከረም 19 ቀን 1998 ዓ.ም በተፈፀመ የሽያጭ ውል ገዝተው ስም ለማዛወር በሒደት ላይ መሆኑን ገልጾ ነው ውልና ማስረጃ የእግድ ትዕዛዙን የመዘገበው፤ ሽያጩ በክብር መዝገብ የተመዘገበው የማይንቀሳቀስ ንብረትን ለመመዝገብ ስልጣን ባለው አካል በመሆኑ የሥር ፍርድ ቤት እግዱ አይነሳም ማለቱ በአግባቡ አይደለም በማለት እግዱ እንዲነሳ ሲል ውሣኔ ሰጠ።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ይግባኝ ቀርቦለት ይግባኙን መሠረት በማድረግ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አፀና። በዚህን ጊዜ አመልካች ለዚህ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት አቤቱታ አቀረቡ። የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤትና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጡትን ውሣኔ አግባብ አይደለም በማለትም በመቃወም ነበር። ቅሬታውም አቶ ኤልያስ ደምሴ ገንዘቡን ከንብረታቸው እንዲከፍሉኝ ተወስኖልኛል። አቶ ተሾመ ካሣዬ ቤቱን ገዝቼዋለሁ ቢሉም የሽያጭ ውሉ ስልጣን ባለው አካል አልተመዘገበም። ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሽያጭ ውሉን ለማስመዝገብ ጥያቄ መቼ እንዳቀረበ ሳያጣራ ተመዝግቧል በማለት እግዱን ማድረጉ አግባቡ አይደለም የሚል ነው። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሣኔ ማጽናቱ ተገቢ አልነበረም። ሁለቱም ፍርድ ቤቶች በፍትሃብሄር ቁጥር 2878 የተደነገገውን ሳያገናዝቡ የሰጡዋቸው ውሣኔዎች መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለባቸው በመሆኑ ተሽረው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ሊፀናልኝ ይገባል የሚል መከራከሪያም አቀረቡ።
ውሳኔው ይከበርልኝ
ተጠሪው በበኩላቸው በሰጡት መልስ፤ የሽያጭ ውሉ በፍትሃብሔር ቁጥር 2878 መሠረት እስከተመዘገበ ድረስ ስም ያለመዛወር የሚያመጣው ለውጥ የለም። የሽያጭ ውሉ ከመዝገቡ ጋር አይያያዝም። ቀደም ብሎ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመለያ ቁጥር 16109 ሚያዝያ 12 ቀን 1999 ዓ.ም በሰጠው ውሣኔ የሽያጭ ውሳኔ ከመዝገቡ ጋር መያያዝ በቂ ነው። በመለያ ቁጥር 21448 የተጠቀሰው የፍትሐብሄር ቁጥር 1123 ለዚህ ጉዳይ አግባብነት የለውም። የእግድ ትዕዛዝ የተሰጠው የሽያጭ ውሉ ከተያያዘ በኋላ ነው። በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የሌለበት በመሆኑ ሊፀናልኝ ይገባል በማለት ተከራከሩ፤ ችሎቱም ሃሳባቸውን ማዳመጥ ቀጠለ።
የህግ ድምዳሜ
የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቤቱ ላይ የሰጠው የእግድ ትዕዛዝ በተጠሪው አመልካችነት ሊነሳ ይችላል ወይስ አይችልም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መዝገቡን መርመረ። መዝገቡ እንደተመረመረውም የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 06 የሚገኘው የቤት ቁጥር አዲስ የካርታ ቁጥሩ ኮ/ቁ/ 09/3/መ/00/180/ 6904/00 በሆነው ቤት ላይ የእግድ ትዕዛዝ የሰጠው መጋቢት 29 ቀን 1998 ዓ.ም ነው። ይህ የእግድ ትዕዛዝ ደግሞ በኮልፌ ቀራንዮ መሬት አስተዳደር ባለሥልጣን ተመዝግቧል። እግዱ በተመዘገበበት ጊዜም ቤቱ በአቶ ኤልያስ ደምሴ ስም የተመዘገበ መሆኑን የሽያጭ ውሉ ከማህደሩ ጋር የተያያዘ ቢሆንም የስም ማዞሩ ጉዳይ በሂደት ላይ ያለ መሆኑን የመሬት አስተዳደር ባለስልጣኑ ገልጿል።
ነገር ግን የመሬት አስተዳደር ባለስልጣኑ ከመዝገቡ ጋር ተያይዟል ያለው የሽያጭ ውል መቼ ከመዝገቡ ጋር እንደተያያዘ አልገለፀም። በማስረጃነት ቀርቦ ከፍርድ ቤቱ መዝገብ ጋር ተያይዞ የሚገኘው የሽያጭ ውል ጽሑፍም ስንመለከተው እላዩ ላይ ክብ የውሎችና የክብር መዝገብ ማስረጃ ማህተም ከማረፉ በስተቀር ይህ ማህተም መቼ የውል ጽሑፍ ላይ እንደተደረገ አይታወቅም። በሽያጭ ውሉ ጽሑፍ ላይም ይሁን ጀርባ ላይ ያረፈ አራት ማዕዘን ማህተም የለም።
የሽያጭ ውሉ የክብር መዝገብ ውስጥ የተያያዘው መቼ እንደሆነ ካልታወቀ ደግሞ የተያያዘው የእግድ ትዕዛዙ ከመሰጠቱ በፊት ነው ለማለት ያስቸግራል። በሌላ በኩል ደግሞ የሽያጭ ውሉ የተያያዘው የእግድ ትዕዛዙ ከመሰጠቱ በፊት ነው ከተባለም በፍትሐብሔር ቁጥር 2878 የአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል ንብረቱ ባለበት አገር በሚገኘው በማይንቀሳቀስ ሃብት መዝገብ ካልተፃፈ በቀር በሶስተኛ ወገኖች ዘንድ ውጤትን ሊያስገኝ አይችልም ተብሎ ከተደነገገው ጋር በማዛመድ ስንመለከተው የሽያጭ ውሉ በማይንቀሳቀስ ሃብት መዝገብ ከመፃፉ በፊት የሽያጭ ውሉ መኖር ያለመኖሩ አስቀድሞ መረጋገጥ ይኖርበታል። ይህ በተጠሪውና በአቶ ኤልያስ ደምሴ መካከል ተደረገ የተባለው የቤት ሽያጭ ውል ግን በፍትሐብሔር ቁጥር 1723 በፍርድ ቤት መዝገብ ወይም ውል ለማዋዋል ሥልጣን በተሰጠው አካል ፊት የተሰራ ስለመሆኑ የቀረበ ማስረጃ የለም። በመሆኑም ተደረገ የተባለው የቤት ሽያጭ ውል ጽሑፍ የማይንቀሳቀስ ሃብት መዝገብ የተፃፈው ሳይረጋገጥ በመሆኑ ውሉ በአመልካች ላይ የሚያመጣው ለውጥ ወይም የሚያስገኘው ውጤት የለም።
በተጠሪው በመከራከርያነት የተጠቀሰው ቀደም ብሎ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመለያ ቁጥር 16109 የሰጠውን ውሣኔ ስንመለከተውም ፍርድ ቤቱ የውሉ ከማይንቀሳቀስ ሃብት መዝገብ ጋር መያያዝ በቂ ነው ያለው የሽያጭ ውሉ ግንቦት 9 ቀን 1987 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ምዝገባ መምሪያ አዋዋይነት የተደረገ መሆኑን በመመልከቱ ምክንያት በመሆኑ ጉዳዩ በዚሁ መዝገብ ከሚታየው ጉዳይ ጋር ተመሳሳይ ባለመሆኑ የተጠሪው ክርክር አግባብነት ያለው ሆኖ አላገኘነውም ይላል።
የመሬት አስተዳደር ባለስልጣን የሽያጭ ውሉን ለማዋዋል ስልጣን ባለው አካል ተረጋግጦ የቀረበለትን የሽያጭ ውል ተቀብሎ ከማይንቀሳቀስ ሃብት መዝገብ ላይ ከማያያዝና ከመፃፍ በስተቀር የማዋዋልና የማረጋገጥ ስልጣን ስለሌለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ የመሬት አስተዳደሩ ባለስልጣን የማይንቀሳቀስ ንብረትን የሽያጭ ውል የመመዝገብ ስልጣን አለው፤ የሽያጭ ውሉ በዚሁ ሁኔታ የተመዘገበ በመሆኑ እግዱ መነሳት አለበት በማለት የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበትና መታረም የሚገባው ነው ሲል አስቀመጠ።
በመሆኑም አመልካች ቀደም ብለው ክርክር ባስነሳው ቤት ላይ የእግድ ትዕዛዝ ያሰጡት ከአቶ ኤልያስ ደምሴ የሚፈልጉትን ገንዘብ ለማስመለስ በመሆኑና በዚሁ መሠረትም ያስወሰኑ ስለሆነ ቤቱን በሐራጅ በመሸጥ ገንዘባቸውን የማስመለስ መብታቸው የተጠበቀ ነው። ይህ መብታቸው ቀሪ ሊሆን ይችላል የነበረው የቤቱ ባለቤትነት ከአቶ ኤልያስ ደምሴ ወደ ተጠሪ ዞሮ ቢገኝ ነው። ይሁን እንጂ ቤቱ በአቶ ኤልያስ ደምሴ ስም ተመዝግቦ የሚገኝ በመሆኑና በማይንቀሳቀስ ሀብት መዝገብ የተያያዘው የሽያጭ ውልም ስልጣን ባለው አካል ያልተረጋገጠ በመሆኑ ቀደም ብሎ የተሰጠው እግድ ተነስቶ የባለቤትነቱ ስም ወደ ተጠሪው እንዲዛወር ማድረግ ተጠሪው ያለአግባብ እንዲጠቀሙ አመልካች ደግሞ በፍርድ ያገኙትን መብት የሚያሳጣ በመሆኑ እግዱ በተጠሪው አመልካችነት የሚነሳበት የሕግ ምክንያት የለም። በዚሁ ምክንያትም የሥር ፍርድ ቤቶች ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበትና ሊሻር የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል በማለት የመጨረሻውን ውሳኔ አሳርፏል።
ውሳኔ
1. የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 29717 ሐምሌ 17 ቀን 1999 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ እና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥ 50420 መጋቢት 13 ቀን 1999 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 348/1/ መሠረት ተሽረዋል ሲል ይደመድመዋል።
2. በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 06 የሚገኘው በካርታ ቁጥር ኮ/ቁ/09/3/መ/00/180/6904/00 የተመዘገበው ቤት ላይ በመለያ ቁጥር 32777 የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠው እግድ በተጠሪው አመልካችነት ሊነሳ የሚችልበት ምክንያት የለም። እግዱ ሊነሳ የሚችለው አመልካች ከአቶ ኤልያስ ደምሴ እንዲከፈላቸው የተወሰነላቸው ብር 18,400 ይከፈላቸው ወይም ደግሞ ቤቱን በሐራጅ ለመሸጥ እንዲቻል አመልካች እግዱ እንዲነሳ ሲጠይቁ ነው በማለት ተወስኗል። በዚሁ መሠረትም የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 32777 ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ ፀንቷል ሲል መዝገቡ ተዘግቷል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም