አዲስ አበባ፡- የኤሌክትሪክ ኃይልና የመስኖ ልማት ሥራዎችን ለመደግፍ የሚያስችል የ7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የብድር ስምምነት ከደቡብ ኮሪያው ኤግዚም ባንክ ጋር መፈራረሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የብድር ስምምነቱ ትናንት በገንዝብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተፈረመበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅምና የመስኖ ግንባታ ሥራዎችን ለማሳደግ ሰፊ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል።ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥረቶቹን ለመደግፍ የሚያስችል የ7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የብድር ስምምነት ከደቡብ ኮሪያው ኤግዚም ባንክ ጋር ተፈራርሟል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ የመጀመሪያው የ170 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የብድር ስምምነት ፕሮጀከት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የኃይል አቅርቦት ለማዳረስ፣ ግንባታው እየተካሄደ ለሚገኘው የኦሞ ኩራዝ የስኳር ፕሮጀክት ያልተቆራረጠ የኃይል አቅርቦት እንዲኖረው ለማስቻል፣ በቀጣይ ግንባታው ለሚከናወነው የአርባ ምንጭ ኢንዱስትሪ ፓርክና ለአካባቢው ነዋሪዎች የኃይል አቅርቦት ለማድረስና ለሌሎች የክልሉ ልማት ማስፈፀሚያ ይውላል።ለዚህ ፕሮጀክት የሚውለው ብድር በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ለባንኩ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።
«በሁለተኛው ፕሮጀከት የብድር ስምምነት 94 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ይሆናል»
ያሉት ሚኒስትሩ፤ ብድሩ በዋናነት የግብርና ምርት እድገት ዘላቂነትን ለማሳደግ፣ ያልተቆራረጠ የመስኖ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት ብሎም የአባወራ ገበሬዎችን ገቢ ለማሳደግና ለድህነት ቅነሳ ፕሮግራም የሚውል መሆኑን ገልጸዋል።
በስምምነቱ ወቅት የደቡብ ኮሪያው ኤግዚም ባንክ ተወካይ ሺን ዲኦግ ዮንግ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ ዋነኛ የልማት አጋር አንዷ መሆኗን ጠቁመው፤ ባንኩ እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ በመጨመር ለአምስት ዓመቱ የትራንስፖርትና ኃይል ማስፋፊያ ፕሮጀከት 570 ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካን ዶላር ብድር ማቅረቡን አስታውሰዋል።
«ለሁለቱ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውለው የአሁኑ የብድር ስምምነት የሁለቱን ሀገራት የጋራ ትብብር ከፍ ያደርገዋል» ያሉት ተዋካዩ፤ በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኙ የገጠር አካባቢዎች ላይ የሚታየውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በመቅረፍ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በተመሳሳይም ለመስኖና የገጠር ልማት ፕሮጀክት የሚውለው ብድር በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች ቀደም ሲል በመስኖ ለማልማት ሲያጋጥማቸው የነበረውን የውሃ እጥረት እንደሚቀርፍና የክልሎችን ኢኮኖሚ በማሳደግና የግብርና ምርትን በመጨመር ገቢያቸውን ከፍ እንደሚያደርግ ተወካዩ አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2011
በአስናቀ ፀጋዬ