አዲስ አበባ፡- የፕላስቲክ ጠርሙሶች አካባቢን እንዳይበክሉና ዳግም ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግ የአሰባሰብ ሥርዓቱ ደካማ መሆኑን የአካባቢ፣ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በተለይም ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ጥቅም ከሰጡ በኋላ የሚጣሉ በርካታ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ቢኖሩም በአሰባሰብ ሥርዓት ደካማነት ምክንያት አካባቢን ከመበከል ባለፈ ዳግም ጥቅም እንዲሰጡ እየተደረገ አይደለም።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሯ ገለፃ እያንዳንዱ ተጠቃሚ ከቤት ጀምሮ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን በአግባቡ በመሰብሰብ ለሚመለከተው አካል በአግባቡ አያስረክብም።ተረካቢው አካልም የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ከተጠቃሚዎች በአግባቡ ሰብስቦ ዳግም ጥቅም እንዲሰጡ ለሚያደርገው አካል አያስተላልፍም።በዚህም ምከንያት የፕላስቲክ ጠርሙሶቹ ዳግም ጥቅም ከመስጠት ይልቅ አካባቢን እየበከሉ ይገኛሉ።
የፕላስቲክ ጠርሙሶችን በአግባቡ የመሰብሰቡ ሥርዓት ቢኖር ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል የገለፁት ምክትል ኮሚ ሽነሯ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የፕላስቲክ አሰባሰብ ሥርዓቱ በርካታ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ በሚፈለገው ልክ ለዜጎች የሥራ ዕድል እንዳልተፈጠረ አመልክተዋል።
የፕላስቲክ ጠርሙሶችን በመሰብሰብና ፈጭቶ ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ መጠነኛ ሥራዎች መጀመራቸውን የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሯ፤ በተመሳሳይ በሀገር ውስጥም ያገለገሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ለሌላ አገልግሎት የመጠቀም ሁኔታዎች በመጀመራቸው የፕላስቲክ አሰባሰብ ሥርዓቱን ከአሁኑ ማስተካከል እንደሚገባ አመልክተዋል።የፕላስቲክ ጠርሙሶች አሰባሰብ ሥርዓቱ በሂደት እየተስተካከለ የሚሄድ ከሆነም
የሥራ ዕድል ፈጠራውንም በዚያው ልክ ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል።
የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጁ ሲሻሻል ከግምት ወስጥ መግባት ያለበት አንዱ ጉዳይ የፕላስቲክ ጠርሙሶች አያያዝና አጠቃቀም ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ፤ አዋጁን መነሻ በማድረግ የፕላስቲክ ጠርሙስ ምርት አቅራቢ ድርጅቶች ጥቅም የሰጡ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን የመሰብሰብ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።ይህን ኃላፊነ ታቸውን መወጣት የማይችሉ እንኳን ቢሆን የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ለሚሰበስበው ሌላ አካል ክፍያ መፈፀም የሚጠበቅባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
በዋናነት ሕጎቹ የሚጣሉ የፕላስቲክ ጠሙሶችን ለመቆጣጠር በሚያስችል መልኩ ተግባራዊ የሚሆኑ ከሆነ የአሰባስብ ሥርዓቱን በማስተካከል የፕላስቲክ ጠርሙሶቹ ዳግም ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚቻል ምክትል ኮሚሽነሯ አያይዘው ገልጸዋል። ይህም በየቀኑ የሚጣሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን በመቀነስ የአካባቢን ንፅህና ለመጠበቅ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
በቅርቡ በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ ሀገራት እ.ኤ.አ አስከ 2030 ድረስ የፕላስቲክ ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉና ዳግም ጥቅም ላይ የሚውሉትም ቁጥራቸው መቀነስ እንዳለበት መስማማታቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2011
በአስናቀ ፀጋዬ